ዲሞክራስያዊ ስምረት ትግራይ – ስምረት ፓርቲ በትግራይ ክልል የከፋ ፖለቲካዊ እና ሰብዓዊ ቀውስ መፈጠሩን ገልጾ፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ስምምነቱን በመጣስ የክልሉን ሰላም እና ደኅንነት አደጋ ላይ ጥሎታል ብሏል።
የአሁኑ የክልሉ አስተዳደር የሕዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ የቡድን ጥቅሙን ለማስጠበቅ ወደ ጦርነት መግባቱን በትላንትናው እለት ባስራጨው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተሰጠ መግለጫው ጠቁሟል።
አስተዳደሩ በውጭ ኃይሎች ተልዕኮ በመመራት ትግራይን ለከፋ ችግር ዳርጓል ያለው ፓርቲው፤ በክልሉ እየታየ ያለው ሰብአዊ ቀውስ እንዳሳሰበው ገልጿል።
በክልሉ እየተካሄደ ያለው ሕገ-ወጥ የንብረት ሽያጭ እና ዘረፋ ሌላው የድርጅቱ ስጋት ነው።
በተለይም በሕግ የተጠበቁ ቅርሶች እና ሕንፃዎች ለይስሙላ ጨረታ ቀርበው መሸጣቸው ተቀባይነት እንደሌለው ገልጾ፣ ባለሀብቶች ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ መክሯል።
ወጣቶች ከፍላጎታቸው ውጭ ወደ ጦር ግንባር እየተወሰዱ መሆኑን የጠቀሰው ፓርቲው፣ ይህ ድርጊት የትግራይን አንድነት የሚፈታተን መሆኑን አስታውቋል።
በደቡብ ትግራይ በደረሰ የድሮን ጥቃት እና ግጭቶች ለደረሰው ጉዳት የጦርነት ቀስቃሽ አካላት ተጠያቂ መሆናቸውንም ገልጿል።
ዲሞክራስያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ በክልሉ የተፈጠረውን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከሌሎች ለውጥ ፈላጊ ኃይሎች ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ፌዴራል መንግሥት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።
