የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በተደጋጋሚ የአካባቢ ብክለት በሚያደርሱ 3 ሺህ 249 ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ ፤ የከተማዋን የአካባቢ ብክለት፤ የድምፅና የፍሳሽ ብክለት ከተሽከርካሪ የሚለቀቀውን ጭስ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
የአካባቢ ህግ መከበርን ለማሣደግ 13 ሺህ 4 መቶ 85 አገልግሎት ሰጪና አምራች ተቋማትን ለመቆጣጠር መታቀዱን ጠቅሰው፤ 14 ሺህ 8 መቶ 72 ተቋማት ላይ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከድምጽ ብክለት ጋር በተያያዘ በመዲናዋ 102 ጭፈራ ቤቶች ከአንድ እና ከሁለት ማስጠንቀቂያ በኋላ በአግባቡ ማስተካከያ ባለማድረጋቸው እንደታሸገባቸው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በህግ ማስከበር ሒደቱ ከ1.6 ሚሊየን ብር በላይ ከቅጣት እንዳገኘም አስታውቋል፡፡
በተደጋጋሚ የአካባቢ ብክለት በሚያደርሱ 3 ሺህ 2 መቶ 49 ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል ያሉት አቶ ዲዳ፤ 3 ሺህ 66 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውና 183 ተቋማት መታሸጋቸውን ተናግረዋል።
