በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን ለመከላከል ጥሪቀረበ

Date:

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የ2019 ዓ.ም. የ16ቱ ቀናት የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ንቅናቄ ዘመቻን በይፋ ጀምሯል። ዘመቻው በሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ የተጎጂዎችን መብት ለማስጠበቅና የተቋማት ተጠያቂነትን ለማጠናከር ያለመ ነው።

«ለተጎጂዎች ፍትሕ፤ ለወንጀለኞች ተጠያቂነት፤ ለሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ደህንነት» በሚል ሀገር አቀፍ መሪ ቃል የተጀመረው ዘመቻ፣ ከኅዳር 16 እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን 2019 ዓ.ም. የሚቆይ ሲሆን፣ «ትሰማ» በሚል መሪ ቃል የሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ደህንነት ብሔራዊ አጀንዳ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳባ ገ/መድህን፣ ዘመቻው የሴቶች ድምጽ እንዲሰማ፣ የተቋማት ተጠያቂነት እንዲጠናከርና ጥቃትን መከላከል የሁሉም የጋራ ኃላፊነት እንዲሆን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ሴቶች ለአካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲጂታል ጥቃቶች፣ ለልጅነት ጋብቻና ለሴት ልጆች ግርዛት ተጋላጭ መሆናቸው ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በፍርሃት፣ በማኅበራዊ መገለልና በቂ የድጋፍ አገልግሎቶች ባለመኖር፣ ብዙ ጥቃቶች ሪፖርት ሳይደረጉ እንደሚቀሩና ተጎጂዎች ፍትሕ ለማግኘት እንደሚቸገሩ ተገልጿል።

            የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ፌቨን አርአያ፣ ሴት ተኮር ግድያን በይፋ የሚያሳይ የዲጂታል መረጃ ሥርዓት እንዲዘረጋና ጥቃቶቹን በሕግ ለይቶ የሚቀጣ ማሻሻያ እንዲታሰብ ጥሪ አቅርበዋል።

የጥቃት ጉዳዮችን በተገቢው ሁኔታ ለመመዝገብ፣ ለመከታተልና የተጎጂዎች ፍትሕ እንዲረጋገጥ የተቋማት ተጠያቂነት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑም ተጠቁሟል።

         ለጥቃት ተጎጂዎች የመጠለያ፣ የሕግ ድጋፍ፣ የሕክምናና የሥነ ልቦና አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል ተቀናጅተው እንዲሰጡና አገልግሎቶቹ እንዲስፋፉ በቂ በጀት እንዲመደብ ጥሪ ቀርቧል።

የጥበቃ ማዘዣዎች በተገቢው ሁኔታ እንዲተገበሩ፣ የፍትሕና የጸጥታ አካላት የጥቃት ሪፖርቶችን በፍጥነት ተቀብለው ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡ አስፈላጊነቱ ተገልጿል።

               መገናኛ ብዙኃን የተጎጂዎችን ክብርና ግላዊነት ጠብቀው በኃላፊነት እንዲዘግቡ፣ የትምህርትና የሥራ ተቋማት ከጥቃት ነጻ የሆኑ አካባቢዎች እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።

የሃይማኖትና የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ወንዶች፣ የልማት አጋሮችና መላው ማኅበረሰብ ጥቃትን በማውገዝ፣ ለተጎጂዎች ድጋፍ በማድረግና የመከላከል ጥረቶችን በማጠናከር ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠይቀዋል።

          ሴቶችና ሴት ልጆች በደህንነት፣ በክብርና በእኩልነት የመኖር መብት ያላቸው መሆኑን በማስገንዘብ፣ ጾታዊ ጥቃትን መከላከል የመንግሥት፣ የሲቪል ማኅበረሰብና የእያንዳንዱ ዜጋ የጋራ ኃላፊነት መሆኑ ተጠቁሟል።

ዘመቻው የሴቶችና ታዳጊ ሴቶች ድምጽ እንዲሰማ፣ ለተጎጂዎች ፍትሕ እንዲረጋገጥ፣ የጥቃት ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑና ሴቶች ከጥቃት ነጻ በሆነ ማኅበረሰብ እንዲኖሩ የጋራ ጥረት እንዲጠናከር ጥሪ አቅርቧል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በዩሮፓ ሊግ አምስተኛ ጨዋታ

በዩሮፓ ሊግ አምስተኛ ጨዋታ ጁቬንቱስ ኦሞኑያ ኒኮስያን 4ለ1 በሆነ...

ኢራን አዲስ ጥቃት ቢፈጸምባት መጠነ-ሰፊ የሚሳኤል አጸፋ ልሰነዝር እንደሚችል አስጠነቀቀች

ኢራን በአሜሪካ ወይም በእስራኤል አዲስ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ፣ ከዚህ...

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎችን በስፖርት ለማሳተፍ የትብብር ውይይት ተካሄደ

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎች በስፖርት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና...

በአዲስ አበባ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ሊጠናከር ነዉ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና የንግድ ስርዓቱን...