በኢትዮጵያ ከ10 ሚልዮን በላይ ሰዎች ከሄፓታይተስ ቢ እና ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከሄፓታይተስ ሲ ቫይረስ ጋር እንደሚኖሩ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በተቋሙ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ፍቃዱ የዴታ እንደገለጹት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባካሄደው ጥናት የሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ አጠቃላይ ብሔራዊ የስርጭት መጠን ከ5.7 እስከ 6.9 በመቶ አካባቢ መሆኑ ተረጋግጧል።
ይህ ስርጭት መካከለኛ እና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ ሀገሪቱ በዓለም የጤና ድርጅት መሥፈርት መሠረት ቫይረሱ በስፋት ከሚታይባቸው ቀጠናዎች ተርታ እንድትገኝ አድርጓታል።
ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሄፓታይተስ ቀን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማከናወኑን ዶክተር ፍቃዱ አንስተዋል።
በሽታው መጀመሪያ ላይ ምንም ዓይነት ምልክት ሳያሳይ የሚቆይ ዝምተኛ ገዳይ በመሆኑ፣ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያስተላልፉ አድርጓቸዋል ብለዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሽታውን በ2030 ከወረርሽኝ ደረጃ ለማውረድ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፣ አዲስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር 90 በመቶ ለመቀነስ ማቀዱን ተናግረዋል።
ለአሐዱ ሬዲዮ
