በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በደረሰ አደጋ ሁለት ሠራተኞች ሞቱ
በሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በደረሰ የማሽን ፍንዳታ አደጋ ሁለት ሠራተኞች ወዲያውኑ ሲሞቱ ሌሎች ሁለት ሰዎች ቀሰሉ ፡፡
አደጋው በፓርኩ ከሚገኙ የምርት ማዕከላት መካከል በአንደኛው ውስጥ ትናንት መድረሱን የፓርኩ የሥራ ሃላፊ አስታውቀዋል ፡፡ አደጋው ሊደርስ የቻለው በምርት ክፍሉ ውስጥ የሚገኘው ማሞቂያ በመፈንዳቱ መሆኑን የፓርኩ ዋና ሥራ ሥራአስኪያጅ አቶ ማቴዎስ አሸናፊ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡
በአደጋው የሁለት ሠራተኞች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አቶ ማቴዎስ ተናግረዋል ፡፡
ዶቼ ቬሌ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል አስተዳዳሪ አቶ ዝናው ሳርሚሶ በበኩላቸው ትናንት ሁለት ሰዎች በእሳት ቃጠሉ ተጎድተው ወደ ሆስፒታል መድረሳቸውን አረጋግጠዋል ፡፡ ተጎጂዎቹ አንደኛው ከባድ ሌላኛው ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የጠቀሱት የሆስፒታሉ ዋና አስተዳዳሪ “ አሁን የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል “ ብለዋል ፡፡
