ከትላንት በስቲያ ረቡእ ነሃሴ 14 በተደረገው የግምጃ ቤት ጨረታ ከፍተኛ ገንዘብ ቢቀርብም ብሄራዊ ባንክ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለመግዛት ሳይፈቅድ ቀረ፡፡
ይህ ሁኔታ ሲደገም በ15 ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ረቡዕ በነበረው ጨረታ መንግስት ለመግዛት አስቦ የነበረው 19.7 ቢሊየን ብር መሆኑን አስታውቆ የነበረ ቢሆንም በጠቅላላው 41.9 ቢሊየን ብር (ከእቅዱ የ113 በመቶ ጭማሪ ያለው) ገንዘብ ለግምጃ ቤት ግዥ ቀርቦ ነበር፡፡
በጨረታው መንግስት 19.6 ቢሊየን ብር የሚሆነውን የገዛ ሲሆን ይህም የበጀት አመቱ ሲጀመር እስከ መስከረም በሚደረጉ ጨረታዎች እገዛዋለው ብሎ ካስቀመጠው እቅድ ከፍ ያለ ነው፡፡
መንግስት ለነሃሴ 14 ለመግዛት አቅዶ የነበረው 14.7 ቢሊየን ብር ነበር ሆኖም እሮብ በተደረገው ጨረታ የገዛው ወደ 20 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ነው፡፡
ከወለድ አንፃር መቶኛው መቀነስ አሳይቷል፡፡ በጉዳዩ ላይ በቅዳሜ ገበያ የሬድዮ ጥንቅር ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንደጠቀስነው መንግስት ለግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ የሚሰጠው ወለድ እየቀነሰ እንዲሄድ ፍላጎት እንዳለው ከፍተኛ የመንግስት ባላስልጣን ምንጮቻችንን ጠቅሰን መግለጻችን አይዘነጋም::
