በጎንደር ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ካምፓስ ትላንት ምሽት የአርሴናል እና ፒኤስጂ የቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ በሚተላለፍበት ወቅት በተከሰተ “ፍንዳታ” የተማሪዎች ህይወት ማለፉና ጉዳት መድረሱን የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ ፍንዳታው “ቦንብ” ነው ሲሉ የገለጹ ሲሆን “ዲ.ኤስ ቲቪ ውስጥ ጭንቅንቅ ብሎ ስለነበር ከቦንቡ በተጨማሪ ተረጋግጦ የተጎዳም አለ ትክክለኛው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ አልቻልንም” ብለዋል።
አደጋው ስለተከሰተበት ሰዓትም ሲያስረዱ ፥ “የአርሰናል ጨዋታ የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ሊያልቅ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው ነው ፍንዳታውን የሰማነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የጤና ሳይንስ ተማሪ ፤ ” አሁን ላይ በካምፓሱ ፖሊሶች ገብተው የፍንዳታውን መንስኤ እያጣሩ ነው ” ያለ ሲሆን ” አሁን ካምፓሱ ሰላም ነው፣ ግን ከዚህ በፊት ከነበረው ሁኔታ የተወሰነ ነገር ተቀይሯል። ጠዋት ላይ የሞቱ ልጆችን አስክሬን ወደቤተሰቦቻቸው ሸኝተናል። አሁን የተወሰነ የሀዘን ድባብ አለ። ግን ተረጋግቷል ” ብሏል።
” በትክክል የሟቾች ቁጥር ባይታወቅም በእርግጠኝነት ሁለት ተማሪዎች ሞተዋል። ጠዋት የአስክሬን ሽኝት አድርገናል። አሁንም ቢሆን ሌላ የሞተ ተማሪ ይኖራል። ማታ ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ በርካቶች በአንቡላንስ ወደ ጤና ተቋማት ተወስደዋል። ፍንዳታው ያስከተለው ጉዳት ከባድ ነው ” ሲል አክሏል።
አብዛኞቹ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በካምፓሱ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቁሟል።
በሰዓቱ ጨዋታውን ከፊት ወንበር ላይ ሁኜ እያየሁ ነበር ያለን አንድ ተማሪ ደግሞ ” የመጀመሪያው የጨዋታ ስዓት አልቆ ለእረፍት ልንወጣ ስንል ነው ፍንዳታው የተከሰተው ” ሲል ተናግሯል።
” በጣም ትልቅ አዳራሽ ነው ኳስ የምናይበት፣ ግን በጣም ሰው ሞልቶት ተጨናንቋል፣ መግቢያ መውጫ የለውም። እያየን የነበረው በፕሮጀክተር እና በቴሌቪዥን ነበር ” ሲል ገልጿል።
” መጀመሪያ ላይ የሆነ የሮኬት አይነት ድምጽ ተሰማን፣ ከዛ ስንነሳ እንደመብረቅ ድፍን ነው ያደረገን። ከፊታችን ብረት ስለነበር በድንጋይ መተውት ነው ብለን ነበር ያሰብነው። ግን ጭሱ በጣም አፈነን፣ በጣም ብዙ ተማሪ ነበርን እየተረጋገጥን በድንጋጤ ወጣን ” ሲል አስረድቷል።
” ውጪ ከወጣን በኋላ ብዙ ተማሪ መመታቱን አየን፣ እኔም መጀመሪያ ደህና ነበርኩ፣ ከወጣሁ በኋላ ሳይ እግሬን ተመትቻለሁ። ምን እንደፈነዳ እንኳ አላውቅም። እኔ ያየሁት የሞቱ ሁለት ናቸው። ሌላ አላየሁም። ግን ለሞት የሚያሰጋቸው አሉ ” ሲል አክሏል።
” ሁለቱንም እግሬን ነው የተመታሁት፣ እስካሁን እግሬ ላይ የገባው የፍንዳታው ፍንጥርጣሪ አልወጣልኝም። ግንባሬንም ተመትቻለሁ” ሲል በስዓቱ የተፈጠረውን ገልጿል።
የትላንት ምሽቱን ፍንዳታ ለዩንቭርስቲው ቅርበት ያላቸው የከተማው ነዋሪ ያረጋገጡ ሲሆን ተማሪዎች መጎዳታቸውንና ህይወታቸው ያለፉ “ተማሪዎች” መኖራቸውንም ገልጸዋል።
የሞቱት ተማሪዎች ቁጥር 3 እንደሆነ፤ 3 ሌሎች ተማሪዎች ከባድ አደጋ እንደደረሰባቸውና ከ30 ያላነሱት ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን እኚሁ ቅርበት ያላቸው ሰው አረጋግጠዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሌላኛው የጎንደር ነዋሪም ” በዩኒቨርሲቲ የምትማር አንድ ልጅ አለች ብዙ ተማሪ መጎዳቱን ገልጻልኛለች እኛም መረጃውን ሰምተናል። ምን ያህል ተማሪዎች እንደተጎዱ እና ስለፍንዳታው አይነት ግን አላውቅም ” ሲሉ ገልጸዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ የተማሪዎች ህብረት አመራሮችን አነጋግሯል ፤ የቦምብ ፍዳታ መከሰቱንና የተማሪ ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።
” ፍንዳታው በቦምብ ነው የተከሰተው፤ ተማሪዎች የዲኤስቲቪ ኳስ ጨዋታ እየተከታተሉ ባሉበት ሰዓት ነው የተከሰተው ” ሲሉ ነው የገለጹት።
የተጎዱ ተማሪዎችን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው አመራሮቹ ” የተጎዱ ተማሪዎች የህክምና ክትትል እያደረጉ ነው ያሉት፤ በርካታ ተማሪዎች ነበሩ የተጎዱት ግን የተወሰኑ ተማሪዎች ናቸው። ውስጡ ያሉ ተማሪዎች ሙሉ አልተጎዱም ” ሲሉ አክለዋል።
ህይወታቸው ያለፉ ተማሪዎች ስለመኖራቸው ጥያቄ ያቀረብንላቸው የተማሪዎች ኅብረት አባላት ” ሁለት ተማሪዎች ለህክምና ከገቡ በኋላ ህይወታቸው አልፏል። ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ነው ህይወታቸው ያለፈው ” ብለዋል።
የተማሪዎቹ አስክሬንም ለቤተሰቦቻቸው መላኩን አክለው ገልጸውልናል።
@tikvahethiopia
