ደራሲና ፀሀፊ ዲናው መንግስቱ በኒውዮርክ የሚገኘውን ፔን አሜሪካን በፕሬዘዳንትነት እንዲመሩ ተመረጡ

Date:



እሮብ ታህሳስ 8 2018 ዓ.ም የፔን አሜሪካ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በተደረገ ምርጫ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዲናው መንግስቱ ድርጅቱን በፕሬዘዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል።

የ103 ዓመት እድሜ ያለው ታዋቂው ተቋም “ፔን አሜሪካ” ዋና መቀመጫውን በኒውዮርክ ያደረገና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡

ተግባሩም ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን መደገፍ ፣ ለስነ ፅሁፍ እድገትና ነፃነት መታገል፣እንዲሁም በአጠቃላይ በአለም ዙሪያ ሰብአዊ መብት እንዲከበር መስራት መሆኑ ይነገራል፡፡

ፔን በመላው አለም ለተመሳሳይ ዓላማ የቆሙ ከ100 በላይ ድርጅቶችን የያዘና በጋራ አሰባሳቢ ጥላው ፔን ኢንተርናሽናል በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ትልቅ ተቋም ነው፡፡

በአሜሪካ ኒውዮርክ ዋና ቢሮውን ያደረገው ፔን አሜሪካም በሎስ አንጀለስ ፣ ዋሽንግተን ዲሲ እና በፍሎሪዳ ተጨማሪ ቢሮዎች አሉት፡፡

ፔን አሜሪካ በተጨማሪም በመገናኛ ብዙሃን ነፃነት ፣ የደራሲያንና ፀሐፊያን ደህንነት ፣ በከፍተኛ ት/ት ተቋማት ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ፣ በድረ ገፅ ጥቃት፣እንዲሁም የኪነ ጥበብ ስራዎች ነፃነት ዙሪያ በስፋት የሚሰራ እና የሚታገል እንደሆነ ይነገራል፡፡

ይህንን ግዙፍ ተቋም በፕሬዘዳንትነት እንዲመሩ ነው ትውልድ ኢትዮጵያዊው ፀሐፊና ደራሲ ዲናው መንግስቱ የተመረጡት።

ዲናው መንግስቱ በኒውዮርክ የሚገኘውና የኪነ ጥበብ ኮሌጅ የሆነው ባርድ ኮሌጅ የሪትን አርት ፕሮግራም ዳይሬክተር ሆነውም ይሰራሉ።

ኢትዮጵያ አሜሪካዊው ደራሲ ዲናው መንግስቱ ትውልዳቸው በአዲስ አበባ ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ መፅሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል።

ሰም ዋን ላይክ አስ፣ ኦል አወር ኔምስ፣ ሀው ቱ ሪድ ዘ ኤይር፣ እንዲሁም ዘ ቢውቲፉል ቲንግስ ዛት ሄቨን ቢርስ መፅሐፎች ብዙ የተነበቡና እውቅና የተሰጣቸው ናቸው፡፡

እንዲሁም በአሜሪካ ታዋቂ በሆነው ጂን መፅሔት ላይ ስለ ሰሜናዊ ዩጋንዳ ግጭት ፣ እንዲሁም በሌላኛው የአሜሪካ ወርሃዊ መፅሔት ሮሊንግ ስቶን ስለ ሱዳኑ የዳርፉር ጦርነት ባቀረቧቸው ፅሁፎችም ይታወቃሉ።

በእነዚህና በሌሎችም በርካታ ስራዎች የ47 ዓመቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ደራሲና ፀሀፊ ዲናው መንግስቱ የተለያየ አለም አቀፍ እውቅናን አግኝተዋል።

የታዋቂው ፔን አሜሪካ ተቋም ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውንም ኒውዮርክ ታይምስን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበውታል፡፡

ከዲናው መንግስቱ ስራዎች አንዱ የሆነውና ባለፈው አመት ለንባብ የበቃው ሰም ዋን ላይክ አስ መፅሐፍ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የአመቱ ምርጭ 10 መፅሐፍት ዝርዝር ውስጥ ተካቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህ መፅሐፍ ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ከ15 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞም ለንባብ በቅቷል፡፡

ሸገር 102.1

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በቬንዝዌላ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ የ32 ሰዎች ህይወት አልፏል

በቬንዙዌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን 7.2 እና 7.5...

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ “ሉሲ” ላገኟት ፕሮፌሰር የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጠ

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፥...

የሳህለወርቅ ዘውዴ አዲሱ አለም አቀፍ ሹመት በተመድ ልዩ ተልእኮ ተሰጣቸው

የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በተመድ ዋና ፀሀፊ...

በሳዑዲ በምሕረት የተለቀቁ 320 ኢትዮጵያውያን

በሳዑዲ አረቢያ የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ የምህረት አዋጅ ከተሰጣቸው 1...