ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አንድን የውጭ ሀገር ባለሀብት ወደ አርባ ምንጭ በመጋበዝ እዚያ ያለውን ማራኪ ተፈጥሮ አሳይተውት የነበረ ቢሆንም፣ ባለሀብቱ ግን “አርባ ምንጭ ለዚህ ኢንቨስትመንት ገና አልደረሰችም፤ ሱፐርማርኬትና ሆስፒታል በሌለበት ከተማ ኢንቨስት አላደርግም” በሚል ንቀት የተሞላበት ምላሽ ሰጥቷቸው ነበር።
ይህንን ምላሽ ወደ ሀገራዊ ቅናትና ቁጭት የቀየሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ያኔ “አልደረሳችሁም” ያላቸውን ሰው ዛሬ በራሳችን አቅም የተሰራውን ተዓምር እንዲያይ ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በአርባ ምንጭ ሐይቅ ላይ እውን የሆነው አዲሱ ግዙፍ ፕሮጀክት ያ የውጭ ባለሀብት ከሰራው እጅግ የላቀና የከተማዋን አቅም ለዓለም ያሳየ ነው።
ማዕከሉ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽን ያካተተ ሲሆን፣ ከምንም በላይ ደግሞ በሐይቁ ላይ ተገንብቶ 360 ዲግሪ ሙሉ በሙሉ በመሽከርከር የተፈጥሮን ውበት የሚያሳይ አስገራሚ ሬስቶራንት ባለቤት መሆን ችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከማንም የሚያንስ ተፈጥሮና ብቃት እንደሌለን ለዚያ ሰውዬና መሰል እሳቤ ላላቸው ሰዎች በንግግር ሳይሆን በተግባር አሳይተናል” ሲሉ የኢትዮጵያን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ አብስረዋል
