በራሳቸው ተነሳሽነትና በጎ ፈቃደኝነት የተሰባሰቡ የሚዲያ ባለሙያዎች “የሚዲያ የሙያ አባቶችን ቤታቸው ድረስ በማቅናት ጎበኙ።
አራት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ባልደረቦች እሁድ ሐምሌ 20 ቀን 2017 ጥየቃ የተደረገላቸው ሲሆን አንጋፋዎቹም በመጎብኘታቸው ደስ ተሰኝተዋል።
ጥየቃ የተደረገላቸው አንጋፋ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋዜጠኛ ይንበርበሩ ምትኬ፣ ጋዜጠኛ ሁሴን በዳሶ፣ አቶ ዳኜ እምቢአለ እና አቶ ካሳ ምህረቴ ናቸው።
ጋዜጠኛ ይበርበሩ ምትኬ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ለ19 ዓመታት በስፖርት ጋዜጠኝነት ያገለገለ ሲሆን፤ ጋዜጠኛ ሁሴን በዳሶ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ለ34 ዓመታት በኦሮምኛ ዜናና ፕሮግራም ላይ የሠራ ባለሙያ ነው።
አቶ ዳኜ እምቢአለ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና በማስታወቂያ ሚኒስቴር ከቴክኒክ እስከ ይዘት ድረስ ከባለሙያ እስከ መምሪያ ኃላፊ ሆነው የሠሩ ሲሆን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ1957 ዓ.ም ሲቋቋም የቴክኒክ ባለሙያ ሆነው ያገለገሉም ናቸው።
አቶ ካሳ ምህረቴም፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መጀመሪያ ላይ ከነበሩ ሁለት የካሜራ ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ ናቸው።
ለአራቱ ባለሙያዎችም ለእያንዳንዳቸው ጋቢ በማልበስና ከባልደረቦቻቸው ለጥየቃ ተብሎ የተሰበሰበ የ10 ሺ፣ የ10 ሺ ብር ድጋፍ ተደርጓል።
የገንዘብ ድጋፉ የተሰበሰበው የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የቀድሞ ሠራተኞችን መጠየቂያ በሚል በተከፈተ የቴሌግራም ግሩፕ ሲሆን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ 29 የሙያ አጋሮቻቸው ድጋፍ አድርገዋል።
“የሚዲያ የሙያ አባቶችን ጥየቃ” የሚለው አሁን ለመጀመሪያ በቡድኑ የተደረገ የተደራጀ ድጋፍ ሲሆን በ3 ወር አንዴና እንደየሁኔታው በበዓላት ወቅትም ጥየቃ እንደሚደረግ ከአስተባባሪዎቹ ለማወቅ ተችሏል።
የእነዚህ ባለሙያዎች የሙያ አበርክቶ “መዝገበ አእምሮ “በተሰኘ የሚድያ ሰዎች ታሪክ በሚሰነድበት ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ የሚሰነድ ሲሆን በተወዳጅ የዲጂታል አውታሮች ላይም ሚናቸው በዝርዝር ይቀመጣል፡፡
