ኢትዮጵያና ኖርዌይ በመስከረም 2019 ዓ.ም በአይነቱ ትልቅ የሆነውን የኖርዲክ-አፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን እና በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ስቲያን ክርስቲሰን በጋራ አጽድቀውታል። ይህ መድረክ በዘርፉ በየዓመቱ ከሚካሄዱ ዓለም አቀፍ መድረኮች አንዱና ቀዳሚው መሆኑ ተገልጿል።
ኖርዌይ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ትግበራ ከአውሮፓ ሀገራት ቀዳሚ መሆኗን የጠቀሱት አቶ በርኦ ሀሰን፣ ኮንፈረንሱ በአዲስ አበባ መካሄዱ በዘርፉ በተሰማሩ አመራሮች፣ ኢንቨስተሮችና ሙያተኞች መካከል ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
በተጨማሪም የአውሮፓ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በስፋት እንዲሰማሩና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር ትልቅ ዕድል እንደሚከፍት ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።
አምባሳደር ስቲያን ክርስቲሰን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዙሪያ ያወጣቻቸውን ሕጎችና የጀመረቻቸውን ሥራዎች አድንቀዋል። ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ግንኙነት ወደ ንግድ ትብብር እንደሚያሳድገው የገለጹት አምባሳደሩ፣ ኖርዌይ በዘርፉ ያላትን ሰፊ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
