ኢትዮ-ጅቡቲ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የባቡርና የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ፍላጎቱን ገለፀ
የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ከቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ሲሲኢሲሲ ጋር የፈጠረውን ስትራቴጂያዊ ሽርክና ተጠቅሞ፣ በቅርቡ ወደሚገነባው ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚያመሩ ወሳኝ የባቡርና የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረጉ ተሰማ።
ይህ እርምጃ ኩባንያው ከወትሮው የባቡር ኦፕሬተርነት ሚናው አልፎ ወደ አጠቃላይ የመሠረተ ልማት ግንባታ ኃይልነት ለመሸጋገር ያለውን ምኞትን የሚያመለክት መሆኑ ተጠቁሟል።
ከዚህ የ12 ቢሊዮን ዶላር ግምት ካለው ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ሁለት መስመር ያለው የባቡር ሐዲድ እና ተጓዳኝ ፈጠን መንገድ የመገንባት ዕድል ያለው ተወዳዳሪ መሆኑን ካፒታል ያገኘዉ መረጃ ያመለክታል።
የባቡር መስመሩ ብቻውን 47 ኪሎ ሜትር የሁለትዮሽ ትራክ ዝርጋታን እንደሚያካትት ታውቋል።
