ኢትዮ ፊደሊቲ ሴኪዩሪቲስ የመጀመሪያውን የባለአክሲዮኖች ጉባኤ አካሄደ

Date:

ኢትዮ ፊደሊቲ ሴኪዩሪቲስ አ.ማ የመጀመሪያውን የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱን ዛሬ ይፋ አደረገ። ኩባንያው በዚህ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሴኪዩሪቲስ ዲለር (የመዋለ ንዋዮች ገበያ ሰነድ አከናዋኝ) ፈቃድ ማግኘቱንና በቀጣይ አገልግሎት በመስጠት ወደ ትርፋማነት ለመሸጋገር ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

የኩባንያው የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበባው ዘውዴ እንደገለጹት፣ ኢትዮ ፊደሊቲ ሴኪዩሪቲስ በ50 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታልና ከ14.2 ሚሊዮን ብር በላይ በተከፈለ ካፒታል የተመሠረተ ነው። መስራቾቹም በፋይናንስው ዘርፍ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውና በተለያዩ የባንክ፣ የኢንሹራንስና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሰሩ እንዲሁም በርካታ ተቋማትን የመሰረቱና በቦርድ አመራርነትም ልምድ ያላቸው 40 ባለአክሲዮኖች ናቸው።

አቶ አበባው አክለውም የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ለሴኪዩሪቲስ ዲለርነት የሚያስፈልገው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን 10 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ ኢትዮ ፊደሊቲ ከዚህ መጠን በላይ በማስመዝገብ ገበያውን መቀላቀሉ የኩባንያውን የፋይናንስ አቅምና ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

ኩባንያው በአዲሱ የካፒታል ገበያ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁንና የባለሥልጣኑን ሕግና መመሪያዎች በመከተል ሙያዊ ሥነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ የግብይት ሥርዓቱን ለማሳለጥ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።

በተጨማሪም ኩባንያው የአገልግሎት ተደራሽነቱን በመላ አገሪቱ ለማስፋፋትና ይበልጥ የተቀላጠፈ ለማድረግ ከተለያዩ የግል ባንኮች፣ ኢንሹራንሶችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር የቅድመ መግባቢያ ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል። የደንበኞችን ምዝገባና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት ለመዘርጋትም እየሰራ መሆኑን ጠቁሟል።

በቀጣይነት በካፒታል ገበያው ውስጥ ሊሰጡ የሚችሉ አዋጭ የሆኑ የአገልግሎት ዓይነቶች በዝርዝር ተለይተው ለባለአክሲዮኖች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የኩባንያው ቦርድ የአይቲና የስትራቴጂ ንዑስ ኮሚቴዎችን በማቋቋም የአመራር ቡድኑን ለመምራትና ለመደገፍ የሶስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ በመንደፍ ላይ ይገኛል።

ኢትዮ ፊደሊቲ ሴኪዩሪቲስ ቀደም ሲል የነበረውን የአክሲዮን ግብይት ሂደት ጠንቅቆ እንደሚያውቅ በመግለጽ፣ አዲሱ የካፒታል ገበያ ለሁሉም ተሳታፊዎችና ተጠቃሚዎች እኩል ዕድል የሚፈጥር እንደሚሆን ገልጸዋል ። ኩባንያው ከመረጃ አቅርቦት ጀምሮ ገበያው እንዲዳብር ከባለሥልጣኑና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል።

አዲሱ የካፒታል ገበያ ለነባርና ለሚቋቋሙ ኩባንያዎች ምቹ የገበያ አማራጭ በመሆኑ ግንዛቤን መፍጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆኑን ኩባንያው አፅንኦት ሰጥቷል። በተጨማሪም ወደፊት ቦንድና ሌሎች የፋይናንስ ሰነዶች በገበያው ላይ ሲቀርቡ ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክቷል።
ከጌጡ ተመስገን ገፅ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አለሁ እኔ ለወገኔ የድጋፍ ጥሪ

እሺ ምን እናድርግ? አርሲ ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊነት ወንጀል የሆነባቸው አካባቢዎች...

በኢትዮጵያ ከ1.6 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ከፍተኛ የእይታ ችግር አለበት

በኢትዮጵያ ከ1.6 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕብረተሰብ ከፍተኛ የእይታ ችግር...

3ኛው የሩሲያ – አፍሪካ ጉባኤ በሞስኮ ይጀምራል

ጥቅምት 28 እና 29 እ.ኤ.አ.3ኛው የሩሲያ - አፍሪካ ጉባኤ...

ዳሸን ባንክ  “ዳሸን ኤር ፔይ” የተሰኘ  የክፍያ አገልግሎት አስተዋወቀ

  ዳሸን ባንክ ለንግድ ተቋማትና ለደንበኞች ግብይትን በተቀላጠፈ መልኩ ለማከናወን...