የእስራኤል ጦር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የጋዛ ሰርጥን ክፍል ከተቀረው አካባቢ ለመለየትና በቋሚነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ግዙፍ የአፈር ክልል እና ጉድጓድ እየገነባ መሆኑን ተሰማ። በተጨማሪም ይህንን የሚያሳይ አዳዲስ የሳተላይት ምስሎች ይፋ ተደርገዋል፡፡
ይህ ለወራት ሲካሄድ የቆየ ነው የተባለው የጂኦ ፖለቲካዊ መሰረተ ልማት እንቅስቃሴ ፍልስጤማውያን እስራኤል በቁጥጥሯ ስር ያዋለችውን የጋዛ ክፍል ዳግመኛ አታስረክብም በሚል የገባችበትን ስጋት ይበልጥ ያጠናከረ ነው።
የእስራኤሉ ሀርትዝ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ግንባታው እ.አ.አ በጥቅምት 2025 በአሜሪካ አሸማጋይነት ከተደረሰው የተኩስ ማቆም ስምምነት ጋር ተይዞ በእስራኤልና በፍልስጤም ግዛቶች መካከል እንደ ጊዜያዊ ወሰን የተከለለውን “ቢጫ መስመር” እጅግ አልፎ የገባ ነው።
በካን ዩኒስ አካባቢ ከልሉ ከቢጫው መስመር አልፎ ወደ ፍልስጤማውያን ወገን በ400 ሜትር ገደማ፣ በራፋህ ደግሞ እስከ 1,300 ሜትር ያህል ዘልቆ ገብቷል። የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ እንደሚያሳየው ደግሞ በአሁኑ ወቅት ክልሉ ከ23 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት የያዘ ሲሆን፣ ይህም መላው የጋዛ ሰርጥ ካለው 40 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመት ጋር ሲነጻጸር አብዛኛውን ክፍል የሚሸፍን ነው።
ከለላው የሚያልፈው ደግሞ የመኖሪያ ቤቶቻቸው፣ መሰረተ ልማቶቻቸውና የእርሻ መሬቶቻቸው በጦርነቱ የወደሙባቸውን የፍልስጤም ማህበረሰቦች መሬት አቋርጦ እንደሆነም ተመላክቷል።
በሌላ በኩል፣ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ በሰሜናዊ ጋዛ በነበሩ ቦታዎች ላይ ሦስት አዳዲስ ወታደራዊ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙ የገለጹ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ሰፋሪዎችና የቀኝ ክንፍ አክቲቪስቶች ደግሞ ወደ ጋዛ ድንበር በመግፋት በጋዛ ውስጥ የእስራኤል ሰፈራዎች እንዲመለስ ጥሪ እያቀረቡ መሆኑ ተዘግቧል።
በአሁኑ ወቅት በፍልስጤም በኩል የሚገኙ ነዋሪዎች ከቢጫው መስመር በስተምዕራብ በሚገኙ የባህር ዳርቻ ላይ በጠባብ ድንኳኖች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ አሁንም ለጥቃትና ለመሰረታዊ ቁሳቁሶች እጥረት እንደተጋለጡ ነው።
ይህንን የከለላ ግንባታ እስራኤል በይፋ በቢጫው መስመር አካባቢ የሚደረግ የአጥር ግንባታ ነው ብትልም ድንበሩን የሚቀርቡ ወይም የሚያቋርጡ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ኃይሎች ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ተገልጿ።
