እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያውያን በታሪካችን መታሰቢያ ማቆየት ላይ ያን ያህል የምንታማ አይደለንም፡፡ ችግሩ ያስቀመጥነውን መታሰቢያ ምን ያህል እንዘክረዋለን የሚለው ነው፡፡ አንዳንዴ እንደውም ለመታሰቢያ ተብለው የሚቆሙ ሐውልቶችና ልዩ ልዩ መዘክሮች የጸቦቻችን መነሻ ሲኾኑ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ማስረጃው ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት ሐረር ላይ የፈረሰው የራስ መኮንን ሐውልትና መሰሎቹ ማሳያ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ሐውልት ወይም መታሰቢያ በማኖር በኩል ችግር የሌለብን ሕዝቦች ነው፡፡ ሌላውን ትተን በቅርብ እንኳን የደርግ መንግሥት አደረጋቸው የተባሉ ግፎችን ለማሰብ በርካታ ሐውልትና መታሰቢያዎች ቆመዋል፡፡ በትግራይ ልዩ የሰማዕታት ሐውልት ቆሟል፤ በአማራና በሌሎች ክልሎችም እንዲሁ የተለያዩ መዘክራን ቆመዋል፡፡ ከሁሉም የሚልቀው ግን በአዲስ አበባ የተገነባው የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሐውልት ነው፡፡ እዚህ መታሰቢያ ኪነ ሕንጻ ውስጥ በቀይ ሽብር የተጨፈጨፉ የበርካታ ወገኖች አጽምና ማንነት ይገኛል፡፡ መንግሥትን ተጻራችኋል በሚል በአብዮተኞች ጥይት የተቀጠፉ በርካታ ለግላጋ ወጣቶች፣ ምሁራኖች እና ውድ ዜጎች በአጽም ደረጃ ተቆልለው ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን መማሪያ ሊኾነን አልቻለም፡፡
በወቅቱ ይህን መዘክር ሲሠራ የነበረው ገዥ መንግሥት አዲስ አበባ ይህን እየገነባ በቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ግን ንጹሐንን እየገደለ በጅምላ ሲቀብር ነበር፡፡ የማይማርበትንና ያላመነበትን መዘክር ነበር ሲያቋቁም የቆየው፡፡ መማር ቢቻል ኖሮ የቀይ ሽብር ሰማዕታት መዘከሪያ ማዕከል ብቻውን ሀገር መገንባት አይሳነውም ነበር፡፡ ገዢዎቹ ወይም ገንቢዎቹ ከዚህ ተምረው ቢኾን ኖሮ ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭትን የሚጸየፍ ትውልድ መፍጠር በቻሉ ነበር፡፡ ነገር ግን አልኾነም፤ ዛሬም ቀይሽብርን በእጥፍ የሚያስከነዱ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች በሀገራችን እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ ዜጎች በጥይት ሳይኾን በእሳት እየጋዩ ሰብዓዊነት በማያቁ የነውር ጌጠኞች እየተቀጠፉ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ ይህን መሰል ሐውልት መገንባት መዘክር መገንባት ወይም ማዘጋጀት ትርጉሙ ምንም ነው፡፡ ምክንያቱ ዜጎች በልባቸው ያለው በቀል እንጅ ምሕረትና ይቅርታ ባለመኾኑ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ታሪኩን በተገቢው መንገድ አጥንቶ ትውልድ እንዳደግመው በአዕምሮው ላይ መሥራት ይሻላል፡፡
ወያኔ ከታሪክ የሚማር ቢኾን ኖሮ የቀይሽብር ሰማዕታት መዘክርን እንደገነባ ቡድን በምንም መልኩ የሰሜን ዕዝ ሠራዊትን በዚያ ልክ አይጨፈጭፍም ነበር፤ የማይካድራ፣ የጭና፣… ወዘተ ንጹሐን ነዋሪዎችን በዚያ ልክ አያርድም፤ አይከተክትም ነበር፡፡ ሃያ ሰባት ዓመታት ሙሉ በተለይም አንድን ማኅበረሰብ ብቻ በዚያ ልክ ለይቶ ሁለ ገብ የግፍና የሰቆቃ ናዳ አያወርድበትም ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር መዘክር ብቻውን ትውልድን አይቀርጽም አያስተምርም፡፡ እንደውም በዘመን አጋጣሚ ጠባብ አመራሮች ወደመንግሥተ መንበሩ ከወጡ ለበቀልና ለአተካራ ያመቻቸዋል፡፡ በሁነቱ ላይ ከግነትም በላይ ግነት ደርበው የሐሰት ትርክተን ለመንዛት እድል ይሰጣቸዋል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የኾነኝ ሰሞነኛው የወልቃይ ጸገዴ የጅምላ መቃብር ቁፋሮና የአጽም ማሰባሰብ ሥራ ነው፡፡
ሰሞኑን የትግራይ ወራሪ ቡድን ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች ላይ የዘር ፍጅት የፈጸመበት “ሀለዋ ወያነ” በመባል የሚታወቁ የጅምላ እስር እና የጅምላ ቀብር የሚፈጸምባቸው ቦታዎችን ማግኘቱን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን አስታውቋል። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ በርካታ የትህነግ የጉድጓድና የዋሻ ድብቅ እስር ቤቶች ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ ከተጠቆሙት የጅምላ መቃብሮች መካከል ለሙከራ አምስቱን አስቆፍሮ ጭካኔ በተሞላበት ግፍ የተረሸኑ ንጹሃንን አፅም አስወጥቷል። በዚህ አሰቃቂ እስር ቤት የታሠሩ ንጹሃን በሚደርስባቸው ሰቆቃ ምክንያት ራሳቸውን ማጥፋታቸውን፣ የትህነግ ታጣቂዎች በየቀኑ ታሳሪዎችን እየወሰዱ ይገድሉ እንደነበርና የብዙዎቹ አስከሬን በአካባቢው የሚገኝ ቃሌማ ወንዝ ላይ ይጣል እንደነበር ከሞት የተረፉት አዛውንቶች ለጥናት ቡድኑ ቃላቸውን መስጠታቸው ተመላክቷል።
ይህ እንግዲህ የቀይ ሽብር መታሰቢያ ሐውልትን ያሠራ ድርጅት የፈጸመው ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር አጽምን ሰብስቦ መዘክር መሥራት ብቻ ሳኾን መማርና ስሕተቱ እንዳይደገም መጣር ነው፡፡ ርግጥ ነው የሰው ሥጋ እርም ነው፤ የሰው አጽምም ክቡር ነው መሰብሰብ አለበት፡፡ በአንድ ማረፊያም እንዲጠለል ማድረግም ግድ ነው፡፡ ነገር ግን ዜጎች በዚህ ታሪካቸው ቂምና ጥላቻን አንግበው እንዳይሄዱ ማድረግ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ልንማርባቸው እንጂ ቂም ልንቋጥርባቸው አይገቡም፡፡ በዚህ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት የተፈጸመው በወልቃይት ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ክልል ከዚህ የላቁ ተግባራት ተፈጽመዋል፡፡ በቅርቡ አይናችን እያየ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ንጹሐን ተጨፍጭፈው በግሬደር ሲቀበሩ አይተናል፤ አስከሬናቸው በአይሱዙ ተጭኖ ሲጓጓዝም ታዝበናል፡፡ የእነርሱንም አስከሬን መሰብሰብ ይገባል፡፡ በጋራ ሙለታ ወደ ጥልቁ ገደል የተወረወሩ ወገኖችም አጽም ይህ ክብር ይገባዋል፡፡
በዚህ ሂደት ግን ከፍ ሲል እንደተባለው ታሪኩን በአግባቡ ሰንዶ ለመማማሪያ ይውል ዘንድ ማድረግ ይገባል፡፡ ተሻጋሪ ቀውሶች እንዳይፈጠሩ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ነው፡፡ አሁን ላይ በየትኛውም የኢትዮጵያ ጥግ በየዘርፉ ተሠማርተው የሚኖሩ ጨፍጫፊው ህወሓት ከወጣበት ማኅበረሰብ የወጡ ዜጎች የዚህ ጥቃት ሰለባ እንዳይኾኑ ማደረግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ያለፉትን ዘመናት ይህ ችግር ሲፈጸም ያልደረሰበት አካል ቀላል መስሎ ቢታየውም የበርካቶችን ሕይወት አጨልሟል፡፡ በበርካታ እናቶች ላይ ዘግናን ግፍ ተፈጽሟል፤ በበርካታ ሕፃናት ላይ አጸያፊ ተግባር ተፈጽሟል፤ ዜጎች በማንነታቸው ተደፍጥጠው የውርደትን ሕይወት እንዲኖሩ ተደርገዋል፡፡ ይሄ ነገር በተለይ እንደ ሕዝብ ወደ ንግግር ተሄዶ መፈወሰ ያለበት ቁስል ነው፡፡ የተፈጸመው ነገር እንኳን ማስታወሻ ተቀምጦለት እንዲሁም ከልቦና ቶሎ የሚወጣ አይደለም፡፡ የትኛውንም ዘመን ያህል የተራዘመ መናቆር ብናደርግ መጨረሻ ላይ ወደ ንግግሩ መኬዱ ላይቀር ግፎች ባይደራረቡ መልካም ነው፡፡ በአጠቃላይ ስለ አሁኑ ሳይኾን ስለወደፊቱ ማሰብ ይገባል፡፡ ይህ ትውልድ የዚህ አጸያፊው ተግባር ተቋዳሽ ቢኾንም ቀጣዩም ትውልድ የዚህ ታሪክ ተጋሪ እንዳይኾን ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም በኃላፊነት መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ዛሬ ላይ አጽም በማሰባሰብ ላይ የሚገኘው የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ይህን ከግምት አስገብቶ ሊሠራ ይገባዋል፡፡ የታሪክ ምሑራንም ይህን ድርጊት ቀምረው ሲያስቀምጡ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ሊኾን ይገባል፡፡ ዘመነኛው መንግሥታችንም ቢኾን የትላንቱን ግፍ እያወራ እርሱ የሚፈጽመውን ሰቆቃዊ ግፍ በአፋጣኝ ማስቆም ይጠበቅበታል፡፡ ያ ካልኾነ ግን ሁሉም ነገር እንዘጭ እምቦጭ ከመኾን አያልፍም፡፡
