✍️✍️የጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የ2026 የፊፋ የአለም ዋንጫ ፍፃሜ የጉዞ ማስታወሻ (ክፍል 1)
📌እንደ መንደርደሪያ
የ2026 የአለም ዋንጫ አርጀኔቲናን 1ለ0 ያሸነፈችውን ስፔንን ሻምፒዮን አድርጎ የመጨረሻው ፊሽካ ተነፍቶ ቢጠናቀቅም፣ በዚህ ረጅሙ የአለም ዋንጫ ጉዞ ያሳለፍኩት ታሪክ ግን ገና አልተጠናቀቀም፤አሁንም በአእምሮዬ በግልጽ ታትሞ ተቀምጧል፤
የአለም ዋንጫን ለመዘገብ ያደረኩት ጉዞ በደስታና በስኬት ብቻ የተሞላ አልነበረም፤ ብዙ ያልተጠበቁ ፈተናዎች በጉዞዬ ገጥመውኛል፤ በተለይም በፍፃሜው ዕለት ያሳለፍኩት ውጣ ውረድ ከእስከዛሬዎቹ ሁሉ የማልረሳው ተሞክሮ ነው፤ በብዙ ፈተናዎች መካከል ተቋቁሜ በዚያ ታሪካዊ የፍፃሜ ጨወታ ዕለት መገኘቴ ለእኔ ከሙያ ስኬት በላይ የሕይወት ትምህርት ሆኖልኛል፤
ከዛሬ ጀምሮ ይህን የጉዞ ማስታወሻዬን በተከታታይ ክፍሎች አጋራችዋለሁ፤ከመነሻው እስከ ፍፃሜው ቀን ድረስ ያጋጠሙኝን ፈተናዎች፣ ያልተጠበቁ አጋጣሚዎች፣ የደስታና የጭንቀት ቅጽበቶች፣ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ክስተት የተማርኩትን፣በተለይ ከሜዳ ውጪ ያሉትን በተከታታይ ለእናንተ አካፍላለሁ፤
አብራችሁኝ ቆዩ፤ ይህ የአለም ዋንጫ የጉዞ ማስታወሻዬ በሜዳ ላይ ስለነበረው ኹነት ብቻ ሳይሆን፣ ወደዚያ ለመድረስ ስለተጓዝኩበት ጉዞም ጭምር የሚተርክ ነው፤ተከታተሉኝ።
🔴ፈተናና መሰናክል (1)
አንዳንድ ጉዞዎች በእግር ሳይሆን በልብ ይጀምራሉ፤የአለም ዋንጫ ፍፃሜ ላይ በመገኘት ህያው ምስክር ለመሆንና ሌላ አዲስ ታሪክ የማፃፍ ዕቅድን ይዤ ወደ ኒው ጀርሲ ስታዲየም የጀመርኩት ጉዞም እንዲሁ በዚሁ ስሜት የታጀበ ነበር።
የዓለም ዋንጫ ፍፃሜን ለመዘገብ ወደዚያ እያመራሁ የነበረው እንደ ማንኛውም ተመልካች ጨዋታ ለማየት ብቻ አልነበረም፤ እንደ ስፖርት ጋዜጠኛ በሙያዬ የተለየ ስፍራ ያለውን ህልሜን ለማሳካት እንጂ።
ከዚህ ቀደም በሁለት የዓለም ዋንጫ ፍጻሜዎች ተገኝቼ ዘግቤያለሁ፤ይህ ግን ሦስተኛ የአለም ዋንጫ ተሳትፎዬ ሆኖ እንዲመዘገብ ወደ ታሪክ እየተንደረደርኩ ነው፤እሁድ ጁን 19/5026 ለእኔ ልዩና ምንአልባትም ታሪካዊ ቀኔ ነበረች፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀ ጥረት የገነባሁትን የሙያ ጉዞ የሚያሳካ፣በሕይወቴም የማይረሳ ታሪካዊ ቀን።
🔴ፍርሃት፣የመረበሽ ስሜት፣ሰጋት(2)
ያ ታሪካዊ ይሆናል ያልኩት ቀን ከወትሮ በተለየ አንዳች ባዕድ የሆነ ስሜትም እንዲሠማኝ ያደርግ ነበር፤ታሪክ ለማፃፍ፣ ጉጉቴን የሚበልጥ ያልታወቀ የጭንቀት፣የመረበሽ ስሜት ውስጤን አጥለቅልቆታል።
ምክንያቱን ባላውቀውም፣ ልቤ እንደማስጠንቀቂያ ደወል የፍርሃት ደውል ደጋግሞ ያለማቋረጥ ይመታ ነበር።
🔴138 ዶላሬና የገጠመኝ ፈተናና ጭንቀቴ(3)
ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ ኒው ጀርሲ የሚወስደኝን የFlixBus ትኬት 138 ዶላር ከፍዬ ከህልሜ ለመድረስ
ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ በፍቅር፣በእንክብካቤ እንቅልፉን ሠውቶ፣አብልቶ አጠጥቶ እስከ ዩኒየን ስቴሽን አደረሰኝ፤
ነገር ግን በውስጤ ያለው መረበሽ ከመቀነስ ይልቅ ስለበረታ፣ጭንቀቱና የመረበሽ ስሜቱ አእምሮዬን በመቆጣጠሩ በአግባቡ እንኳን ሳልሰናበተው ከመኪናው ወርጄ ወደ ጣቢያው ሮጥኩ።
ወደ ጣቢያው(Station)እንደገባሁ የመጀመሪያው ፈተና ጠበቀኝ፤ረጅም ሰልፍ ነበር፤ገና በማለዳ ረዥሙን ሠልፍ ሳየው አደከመኝ፤በዚህ መሃል ከፊቴ የቆመውን አንድ አሜሪካዊ “ይህ ወደ ኒው ጀርሲ የሚሄደው ነው?” ብዬ ስጠይቀው አንገቱን ጭምር በመነቅነቅ”አዎ፣ በትክክለኛ ቦታ ላይ ነህ” አለኝ።
በለበስኩት የኢትዮጵያ ባንዲራ ያለበት ጀግኖች አትሌቶቻችን የሚለብሱት የአሸናፊነት ምልክት ተደርጓ በሚወሠደው ቱታ መደነቁን አይንቹና ፊቱ እያሳበቁበት ብዙም ሳይቆይ “ከየት ነህ?” የሚል በጣም የማልወደው ቀፋፊ ጥያቄ ጠየቀኝ፤ንዴቴን ዋጥ አድርጌ ከኢትዮጵያ ብዬ መለስኩለት፤እሱ ግን በዚህ አላበቃም አስከተለና “ትኬትህን በስንት ገዛኸው?በጣም ተወዷል አይደል ” ሲል ጠየቀኝ።
“አዎ በጣም ተወዷል፤እኔ ግን ትኬት አልገዛም፣በትኬትም አልገባም፤ ከ16 ሺህ በላይ ከመላው ዓለም ከተመረጡ ጋዜጠኞች አንዱ ሆኜ በሚዲያ ባጄ ነው የምገባው ብዬ ደረቴ ላይ ያለውን ባጄን አሳየሁት፣ በመደነቅ ስሜት ቃና ያለው በሚመስል ድምፅ “ዋው! በጣም ዕድለኛ ነህ” አለኝ፤ይሄን ሁሉ እሱ ሲጠይቅና እኔ ስመልስ የነበረው ከቀልቤ ነበር ለማለት ይቸግረኛል፤ቀልቤ አብሮኝ አልነበረም፤
ምክንያቱን በማላውቀው ነገር አእምሮዬ አንዳች መግኒጥሳዊ ኃይል ተቆጣጥሮታል፤ከመረበሼና የስጋቴ መጠን በድንገት እንደ ዶላር ዋጋ ከፍ በማለቱ ለሁለተኛ ጊዜ “እርግጠኛ ነህ?ይሄ ወደ ኒውጀርሲ ስታዲየም ነው?” ብዬ ስጠይቀው ሳቅ በተሞላበትና ፌዝ በሚመስል መልኩ “አታስብ በጣም በትክክለኛ ቦታ ላይ ነህ” አለኝ።
ቃሉን አምኜ ወደ ውስጥ ገባሁ፤ውስጥ ስገባ ግን ከፊቴ የቆመው አውቶቡስ ሳይሆን ባቡር ነበር።
ዞር ብዬ ሰውየውን ፈለግሁት፤ ግን ጠፍቷል፤አረ እንደውም በቅፅበት ተሠውሮብኛል፤ያኔ አንድ ነገር እንዳለ ወይም እንደተሳሳትኩ ገባኝ። በ”FlixBus ነው የምሄደው የት ነው ባሱን የማገአው?” ብዬ ስጠይቅ “እዚህ አይደለም ከላይ ነው፤ በፍጥነት ሂድ!” አሉኝ።
🔴ለሪከርድ እንደሚሮጥ አትሌት ወደ አውቶብስ ሩጫ (4)
ሰዓቴን እያየሁ ለሪከርድ እንደሚሮጥ አትሌት በዛ ሠውነቴ ሮጥኩ፤ ኤስካሌተሩን ወጥቼ የአውቶብስ መሳፈሪያው ጋ ደርሼ ሠዓቴን ሳይ የሰዓት መቆጠሪያው 6፡04 ይላል፤ አውቶቡሱ በ6፡00 ተነስቶ ሄዷል፤አራት ደቂቃ ነገሮቼን፣ታሪኮቼን የማበላሸት እርምጃ ውስጥ እንደገቡና አለም ሁሉ በጉጉት ከሚጠብቀው ታሪካዊ የፍፃሜ ጨዋታ ውጭ ሊያደርገኝ እንደነበር ተሠማኝ፤ፈረንጆች ለጊዜ ያላቸውን ዋጋ እንኳን በዚህ ደረጃ ተቀጥቼ ይቅርና ቀድሜም አውቅ ስለነበር በአራት ደቂቃማ ህልሜ አይገታም ብዬ ወደ ሁለተኛ አማራጭ ገባሁ፤
🔴የአራት ደቂቃ ዋጋው ስንት ነው?(4)
እጅግ ውድ ነው፤ይህንን ደግሞ አትሌቶች ለማይክሮ ሰከንድ የሚሠጡትን ዋጋ በቅርቡ ስለማውቅ አራት ደቂቃ ዋጋዋ እጅግ ከፍ ያለ እንደሆነ ለመረዳት ምርምር አይጠይቅም፤ትንሽ የምትመስለው አራት ደቂቃ ጉልበት ኖሯት የወራት ዝግጅቴን እና የዓመታት ህልሜን ለማፍረስ ተቃርባ ነበር፤ዩኒዮን ስቴሽን ውስጥ ወደሚገኘው ትኬት ቢሮ ሄጄ ሁኔታውን ለትኬት ኦፊሠሯ ስገልጽ እሷም “በጣም አዝናለሁ፤ አውቶቡሱ ሄዷል” አለችኝ፤በምላሿ ውስጤ ተሠበረ፤የተሰበረው 138 ዶላር የከፈልኩበት የማለዳ ጉዞዬ ብቻ አልነበረም፤ የሦስተኛ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜን በቦታው ተገኝቼ የመዘገብ ህልሜም እንጂ።
ሆኖም በዚያ ቅጽበት ልቤና አእምሮዬ አንድ ነገር ተስማሙ፤ “ይህ ጉዞ በአራት ደቂቃ አያበቃም፤የሦስተኛ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታን ሳልዘግብ፣በሙያዬ አዲስ ታሪክ ሳላፅፍና ህያው ምስክር ሳልሆን አልመለስም ብዬ ለራሴ ቃል ገባሁ።
🔴የአውቶብስ ትኬት ስለመወደዱና በየሠከንዱ መሸጡ(Sold out)(5)
ወደ መዳረሻዬ ለመድረስ የያዝኩት የመጀመሪያው FlixBus አመለጠኝ፤ያን ጊዜ የተሰማኝ ብስጭት በቀላሉ የሚገለጽ አልነበረም፤ትኬቴ እንደማይመለስ ሲነገረኝ 138 ዶላር ከእጄ እንደወጣ ተሰማኝ፤ በተለይም ዶላር ለመቆጠብ የሚታገልና ዋጋዋን ጠንቅቆ ከሚረዳ ሀገር ለመጣ ሰው ያ ኪሳራ ከገንዘብ በላይም የህልም መደናቀፍ መስሎ ተሠማኝ።
“መፍትሄው ምንድነው?” ብዬ ስጠይቅ አዲስ ትኬት መቁረጥ እንዳለብኝ ተነገረኝ፤ሪፈንድ(ተመላሽ) እንዲደረግልኝ ስጠይቅም “የተቋሙ ፖሊሲ ነው፤አይመለስም” የሚል ድፍን ያለ መልስ ብቻ አገኘሁ፤በዚያ ቅጽበት ብስጭቴና ጭንቀቴ ተቀላቀሉ፤ቀጣዩን አማራጭ ስፈልግ ዋጋው በፍጥነት ጨምሮ ነበር፤ከትኬት ኦፊሰሯ ጋር እየተከታተልኩ ሳለሁ በ183 ዶላር አንድ ቦታ እንዳለና ትኬት እየተወደደና Sold Out (ተሸጦ እያለቀ)በመሆኑ መፍጠን እንዳለብኝ ነገረችኝ።
ለመወሰን ጥቂት ጊዜ ወሰድኩ፤ ስመለስ ግን ያ እድልም ጠፍቶ ጠብቀኝ ፤እንደተፈራው “Sold out ሆኗል” የሚለውን ቃል በዚያ ቅጽበት ስሠማ ሌላ ከባድ ጫና ሆኖብኝ ፤
በዚያ ሁኔታ ቆሜ “ምንድነው የሚከታተለኝ?” ብዬ ራሴን እስከመጠየቅ ሁሉ ደረስኩ፤ የሚቀጥለው ጉዞ 9፡30 እንደሆነ ሲነገረኝ ደግሞ ሌላ ጭንቀት መጣ፤ ጉዞው አምስት ሰዓት የሚፈጅ በመሆኑ ለጨዋታው የመድረስ እድሌ አስፈሪ ሆነ፤
በዚያ ጊዜ አንገቴን ወደ ላይ ቀና አድርጌ ከፈጣሪዬ እርዳታ ተማፀንኩ፤በባቡርና በአውሮፕላን ብሎም በኡቨር ጭምር ለመጓዝ ስጠይቅ ዋጋቸው ክፉኛ ወደላይ ተስፈንጥሯል፤ባቡር ከ300-500 ዶላር፣አውሮፔላን እስከ 700 እና ከዚያ በላይ ኡበር እስከ 400usd መጠየቃቸው ነገሮችን ይበልጥ አወሳሰቡት ልክፈል ብልም ከኪሴ ጋር የሚመጣጠንም አዬደለም፤
በዚህ የተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ ወድቄ እየተሠቃየሁ ባለሁበት ሠዓት የእኔን ጭንቀትና ጋዜጠኛነቴን የተረዳ ሌላ የትኬት ኦፊሰር 8፡30 ላይ የሚያደርሰኝ ፈጣን የአውቶብስ አማራጭ እንዳገኘልኝ ነገረኝ፤ መጀመሪያ ከገጠመኝ ችግር በመነሳት ሁለቴ እንኳን ሳላስብና ሳላመንታ ዶላሬን መዥርጬ ከፈልኩ፤ ግን የሁለት ዓመት ያህል የረዘመ ሁለት ሰዓታትን በጭንቀት የመጠበቅ ግዴታም ወደቀብኝ
🔴ጉዞ ወደ Brooklyn 38th st እና ወደ ፔን ስቴሽን(5)
የሁለት ዓመት ያህል የረዘመው የሁለት ሰዓት ቆይታ ወይም ጥበቃ መድረሱ አይቀርም ደረሠ፤በመጨረሻ አውቶብሱ እንደ ነፋስ በሮ Brooklyn 38th st ደረሠ በመቀጠል ወደ ኒውጀርሲ ፔን ስቴሽን ሠተት ብዬ ገባሁ፤ወደ ስታዲየሙ የሚያመለክቱ ምልክቶችን በቮሎንተርሶች እጅ ሳይ የተሰማኝ እፎይታ ልዩ ነበር፤ከፔን ስቴሽን የያዝኩት ባቡር ከአንድ ስቶፕ ከተጓዝን በኋላ Secaucus Junction ስቴሽን ስንደርስ ትራንዚት በማድረግ በሌላ ባቡር ተሳፍሬ ወደ መጨረሻው መድረሻዬ ኒውጀርሲ ሴታዲየም ደረስኩ፤በስታዲየሙ በር ላይ ቆሜ የተሠማኝን ስሜት ለመግለጽ ቃላት ያንሠኛል፤ ግን በአንድ ነገር ላይ በጣም እርግጠኛ ሆንኩ፤የዘመናት ህልሜ በእጄ እንደገባ ተሰማኝ፤ከዚህ በላይ የማይረሳው ደግሞ በተገኘሁበት በዚያው ስታዲየም እኔና የዓለማችን አወዛጋቢው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በአንድ መድረክ ላይ ያንን ታላቅ የእግር ኳስ ታሪክ በመመልከት ፈተናዎቼንና ብስጭቶቼን በደስታ ቀየረልኝ።
የአውቶብስ ማምለጥ፣የትኬት መጥፋትና ዋጋ መናር፣ ከብዙ ጭንቀትና ከፍርሃት በኋላ የደረስኩበት ያ ቦታ ለእኔ የድል ስፍራ ሆነ፤ያ ቀን በህይወቴ ውስጥ የማይረሳ ታሪክ ሆኖ ተመዘገበ።
ለአንድ ሰው ቀላል የሚመስለው ጉዞ ለሌላ ሰው የህይወት ትልቅ ትዝታ ሊሆን ይችላል፤የእኔም ያ ጉዞ እንደዚህ ነበር፤ ከፈተና በኋላ የተገኘ ደስታ፣ ከጭንቀት በኋላ የተሰጠ ሽልማት፣ እና በህልም የተጻፈ የማይረሳ ታሪክ።
….(ይቀጥላል)….
📌በመጨረሻ:-
ከዛሬ ጀምሮ ይሄንን የጉዞ ማስታወሻዬን በተከታታይ ክፍሎች አጋራችዋለሁ፤ከመነሻው እስከ ፍፃሜው ቀን ድረስ ያጋጠሙኝን ፈተናዎች፣ ያልተጠበቁ አጋጣሚዎች፣ የደስታና የጭንቀት ቅጽበቶች፣ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ክስተት የተማርኩትን፣በተለይ ከሜዳ ውጪ ያሉትን አዳዲስ የዓለም ዋንጫ ክስተቶችን በተከታታይ ለእናንተ አካፍላለሁ፤መልካም ቆዬታ
🙏🙏ታላቅ ምስጋና:ይህ የአለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት የትራንስፖርትና የሆቴል ወጪን በመሸፈን በሠው ሀገር ባይተዋር እንዳልሆን ስልክ እየየደወለ የሚያበረታታኝ፣ቃሉን ጠብቆ ያገዘኝን ወደ ዳላስ እንድመጣም ግብዣ ያደረገልኝን በዳላስ ነዋሪ የሆነው ደጉን፣ቀናውንና ቸሩን የቀድሞ ወዳጄን አሠፋ ከበደን የፍፃሜ ጨዋታው አጋር በመሆኑ በተከበሩ አንባቢዎቼ ስም ለማመስገን እወዳለሁ፤ያለ እሱ ድጋፍ ይሄን ፈተና ለመወጣት እጅግ ይቸግረኝ ነበርና አሴ ወንድሜን ከነመላ ቤተሠቦቹ ከልብ አመሠግናለሁ።🙏🙏
