በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ወጣቶች ላይ የተደረገ ጥናት፣ ወጣቶች ስለ ህገ-ወጥ ስደት አደጋና ስለ ህጋዊ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ያላቸው ግንዛቤ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን አመለከተ።
በንጋት ግሎባል ኢኒሼቲቭ የቀረበው የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው፣ ጥናት ከተደረገባቸው ወጣቶች መካከል 27.4 በመቶዎቹ ብቻ ስለ ህገ-ወጥ ስደት ተጋላጭነት በቂ እውቀት ያላቸው ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ግንዛቤያቸው ዝቅተኛ ነው።
ይህም ወጣቶች በደላሎች በቀላሉ እንዲታለሉና ለአደጋ እንዲጋለጡ እያደረጋቸው መሆኑ ተገልጿል።
በጥናቱ ከተሳተፉት ወጣቶች መካከል ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት ቀጥተኛ የሆነ የደላላ ግንኙነት ያላቸውና ለመሰደድ ገንዘብ የከፈሉ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
ይህን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፣ “Mag MT” የተሰኘ የስደትንና የሰዎች ዝውውርን የተመለከተ የሚዲያ አማካሪ ቡድን መቋቋሙም ታውቋል።
ይህ ቡድን የሚዲያ ባለሙያዎች ስለ ስደት የሚሰሩ ዘገባዎች ክስተት ተኮር ብቻ ሳይሆኑ፣ ቀጣይነት ያላቸውና ግንዛቤ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሚሰራ ተገልጿል።
ወጣቶች ህጋዊውን መንገድ በመከተል መብታቸው ተከብሮ እንዲሰሩና መረጃዎችን ከትክክለኛ የመንግስት ምንጮች ብቻ እንዲያገኙ ማሳሰብ የቀጣይ ስራዎች ትኩረት እንደሚሆን ተመልክቷል።
