በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የማለፊያ ውጤት 50% ሆኖ መወሰኑን የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
የአጠቃላይ ካውንስል አባላት ባደረጉት ስብሰባ ያጸደቋቸው የማለፊያ ነጥቦች ፡-
• 🔹 ለመደበኛ ተማሪዎች፡ 50%
• 🔹 ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች፡ 45%
• 🔹 ለኦቲስቲክ፣ ዳውን ሲንድረምና ኢንተሌክቹዋል ዲሴቢሊቲ ላለባቸው ተማሪዎች፡ 40%
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ እንደገለጹት፤ በ2018 ዓ.ም 84,257 ተማሪዎች በ199 የፈተና ጣቢያዎች ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን፣ የዘንድሮው ውጤት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዓመታት የተሻለ እድገት አሳይቷል።
የቢሮው ኃላፊ ክቡር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው፤ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ከመደበኛ ትምህርት ውጪ የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱንና በተለይም በሒሳብና እንግሊዘኛ ትምህርቶች ላይ ልዩ ስትራቴጂ ተነድፎ መተግበሩ ለዚህ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
ኃላፊው ውጤቱ በአጭር ጊዜ ታርሞ ይፋ እንዲሆን ቀን ከሌት ለደከሙ የፈተና ክፍል ባለሙያዎችና አመራሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
