በአገራችን በእግር ኳስ ትንተና፣በጋዜጣ አሳታሚነትና በሕግ ባለሙያነቱ ትልቅ አሻራ ያሳረፈው የአዲስ ነገሩ ዐቢይ ተክለማሪያም ልደቱ በማህበራዊ ድረ ገፅ ሊከበር ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በእንግሊዝ አገር በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እያስተማረ የሚገኘው ዐቢይ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን ከ 17 ዓመት በፊት “አዲስ ነገር” ጋዜጣን የጀመረ ሲሆን ከዚያ ቀደም ብሎም “ቶክ ፉት ቦል “የተሰኘውን ስለ እግር ኳስ የሚወራበትን ቅርፅ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀ ነው።
“መዝናኛ” ጋዜጣንም ከመሠረቱት አንዱ የሆነው ዐቢይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሕግ ት/ቤት በ1990 ዓ.ም በከፍተኛ ውጤት ለመመረቅ የቻለ ነው፡፡
የሕይወት ታሪኩ እንዲሰነድ በመዝገበ አእምሮ የዝግጅት ክፍል ውሳኔ ከተደረሰ በኃላ የልደቱንም ቀን ምክንያት በማድረግ የሥራ ታሪኩ በማህበራዊ ድረ ገፆች ይጫናል።
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ የባለሙያዎችን ታሪክ በአማርኛ ኢንሳይክሎፒዲያ የሚሰንድና በመፅሐፍ ለሕትመት የሚያበቃ ድርጅት ሲሆን እስከዛሬም የ 400 ባለሙያዎች ታሪክ በአጫጭሩ ተደራሽ እንዲሆን አድርጓል።
የዐቢይ ተክለማሪያምን ታሪክ በተመለከተ የቤተሰቡ አባላት፣አብሮ አደጎቹ እና ባልደረቦቹ ምስክርነት የሰጡበት ፅሁፍ ከ 24 ሰዐት በኃላ በማህበራዊ ድረ ገፆች መሰራጨት ይጀምራል፡፡ የሕይወት ታሪኩ በሚድያ ሰው ታደሰ ማሞ እና በዕዝራ እጅጉ የተዘጋጀ ሲሆን ለፅሑፉም በቂ የምስልና የሰነድ ማመሳከሪያዎች ቀርበዋል፡፡
ተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን፣ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መከበር እና ታሪካቸውም መሰነድ አለበት የሚለውን መርህ በማንገብ ለበርካታዎች ዕውቅና ሲሰጥ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
