አሜሪካ እና ሳዑዲ አረቢያ የተፈራረሙት ግዙፍ የኒውክሌር ስምምነት ተግባራዊነት የሚወሰነው፤ ሪያድ ለእስራኤል የአገርነት ዕውቅና እንድትሰጥ የሚያደርገውን ‘የአብርሃ አኮርድስ’ ስትቀላቀል እንደሆነ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ “ወታደራዊ ላልሆነ ጥቅም ብቻ የሚውለው… የሲቪል ኒውክሌር ስምምነቱ (ዩራኒየም ማበልጸግ አይኖርም).. ይጽድቃል” ብለዋል።
የስምምነቱ መጽደቅ “ግን ሳዑዲ አረቢያ እጅጉን የተከበረው እና ስኬታማውን የአብርሃም ስምምነቶችን መቀላቀሏ ላይ የተመሠረተ ነው” ሲሉ ቅድመ ሁኔታውን ይፋ አድርገዋል።
ትራምፕ ይህንን ያሉት፤ የተፈረመው ስምምነት ቀድሞውኑም አለመረጋጋት ውስጥ ባለው ቀጣና ውስጥ ወደፊት የኒውክሌር መሣሪያ መስፋፋትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ወቀሳ ከተሰማ በኋላ ነው።
ከዚህ ቀደም ሳዑዲ አረቢያ ፍልስጤም አገር ሆና ሳትመሠረት ለእስራኤል ዕውቅና እንደማትሰጥ ገልጻ ነበር።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2020 እንዲፈረም ያደረጉት አብርሃም አኮርድስ፣ በታሪካዊ ሁኔታ እስራኤል አረብ አገራት ከሆኑት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ባህሬን ጋር ግንኙነት እንዲኖራት ያደረገ ነው።
ቀጥሎም ሱዳን፣ ሞሮኮ እና ካዛኪስታን ስምምነቱን ተቀላቅለዋል። እስካሁን ድረስ ሳዑዲ ለትራምፕ አስተያየት ምላሽ አልሰጠችም።
ፕሬዝዳንቱ ይፋ ያደረጉት የአብርሃም አኮርድስን የመቀላቀል ቅድመ ሁኔታ ከሳዑዲ ጋር በተፈረመው ስምምነት ውስጥ በጽሑፍ ተካትቶ፣ ሪያድ ለቅድመ ሁኔታው ተስማምታ አልያም ስምምነቱን ለመቀበል ትገደድ እንደሆነ አልታወቀም። የአሜሪካ እና የሳዑዲ ስምምነት እስካሁን ይፋ አልሆነም።
እስራኤል በበኩሏ የትራምፕን መግለጫ በበጎ እንደምትቀበለው አስታውቃለች። የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ ሳዑዲ አረቢያ ስምምነቱን መቀላቀሏ “በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማስፈን ትልቅ ታሪካዊ እርምጃ ይሆናል” ብሏል።
የእስራኤል መግለጫ ላይ ስለ ኒውክሌር ስምምነቱ አልተጠቀሰም። የእስራኤል የኢኮኖሚ ሚኒስትር ኒር ባርካት ከዚህ ቀደም፤ ሳዑዲ አረቢያ ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል ኒውክሌር ኃይል አገራቸው ጉዳዩን “ማስተዳደር እንደምትችል” ተናግረው ነበር።
እስራኤል ራሷ የኒውክሌር መሣሪያ እንዳላት በሰፊው የሚታመን ቢሆንም አገሪቱ ግን ማረጋገጫ ሰጥታም ይሁን አተስባብላ አታውቅም።
BBC
