ሆስፒታሉ በቀን ከ300 በላይ ታካሚዎችን ያስተናግዳል
የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ከሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ነፃ የክረምት የጤና ምርመራ፣ የጤና ምክር እና የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።
የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም እሸቱ ከብስራት ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ በቀን ከ300 በላይ ታካሚዎች አገልግሎቱን ያገኛሉ።
አገልግሎቱ ከህፃናት እስከ አዋቂዎች ድረስ ለሁሉም የዕድሜ ክልሎች የሚሰጥ መሆኑን በመግለፅ በስፔሻሊስት እና በሰብስፔሻሊስት ሀኪሞች ይከናወናል።
የመርሃ ግብሩ ዋነኛ ዓላማ የጤና ምርመራን ማበረታታት ነው የተባለ ሲሆን በተለይም አቅም ለሌላቸው ዜጎች የሕክምና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በነፃ ከሚሰጡት አገልግሎቶች ውስጥ የውስጥ ደዌ፣ የማህፀንና ፅንስ ሕክምና፣ የመለስተኛ ቀዶ ህክምና፣ የጥርስ ፣ የሥነ አዕምሮ ሕክምና፣ የልብ ምርመራ እና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አገልግሎቱ በየቀኑ ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት እስከ ቀኑ 10:00 ሰዓት ድረስ በቁስቋም በሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ የጤና ምርመራ ወይም ሕክምና የሚፈልጉ ዜጎች በተጠቀሰው ቦታ በመገኘት አገልግሎቱን መጠቀም እንደሚችሉ ዶክተር አብርሃም እሸቱ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
