የትግራይ ትምህርት ቢሮ የራሱን ፈተና አዘጋጅቶ ተማሪዎችን ሊፈትን መሆኑን አስታወቀ

Date:



​የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ባለመስማማት በራሱ አሠራር በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈተና አውጥቶ ተማሪዎችን ሊፈትን መሆኑን የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ ገለጹ።

​ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ ይህንን የገለጹት የ2018 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መውጫ ፈተና አሰጣጥን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፣ በክልሉ በወረቀት ፈተና ለመውሰድ ተመዝግበው ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ 15 ሺህ 349 ተፈታኝ ተማሪዎች ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ ፈተናቸውን እንዲወስዱ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር ግን እስካሁን ድረስ የፈተና ወረቀቶችን ወደ ክልሉ አላከም።

ፈተናው በአውሮፕላን ተጓጉዞ በፌደራል ፖሊስ ጥበቃ የሚደረግለት በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት የፈተና ወረቀቱን ወደ ትግራይ ክልል ላለመላክ ምንም ዓይነት አሳማኝ ምክንያት የለም ሲሉ ኃላፊው ወቅሰዋል።

​የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ ለችግሩ እልባት እንዲሰጥበት ለትምህርት ሚኒስቴር ደብዳቤ ቢልክም እስካሁን ይፋዊ ምላሽ አላገኘም።

ሐምሌ 1 ቀን ለሚጀምረው ፈተና ተማሪዎች በሰኔ 29 ቀን ወደየዩኒቨርሲቲዎቹ መግባት የነበረባቸው ቢሆንም፣ በትምህርት ሚኒስቴር ምክንያት በመቅረቱ ተማሪዎች ጉዟቸውን እንዲያቋርጡ ተደርጓል።

በትምህርት ሚኒስቴር የተላለፈው ይህ ውሳኔ የፖለቲካ ውሳኔና የጦርነቱ ቀጣይ አካል በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ያሉት ዶክተር ኪሮስ፣ በትግራይ ክልል በኦንላይን (በኢንተርኔት) እና በወረቀት ሳይፈተኑ የቀሩ በአጠቃላይ 29 ሺህ 755 ተማሪዎችን ክልሉ የራሱን ፈተና በአጭር ጊዜ ውስጥ አዘጋጅቶ እንደሚፈትን አስታውቀዋል።

​በመጨረሻም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የራሱን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ወስኖ ተማሪዎችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚያስገባ የገለጹት ኃላፊው፣ ፈተናው የሚሰጥበት ትክክለኛ ጊዜ ወደፊት ይፋ እንደሚደረግና ተማሪዎች ይህንን አውቀው ዝግጅታቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጉምሩክ ኮሚሽን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ገለጸ

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በ2018 በጀት ዓመት 725.25 ቢሊዮን ብር...

ከ1.5 ሚሊዮን ዶላር የአፍሪካ ንፁህ ኢነርጂ ፈንድ አምስቱ አቅኚ የኢትዮጵያ ድርጅቶች ተመረጡ

በምስራቅ አፍሪካ የንፁህ ኢነርጂ አቅርቦትን በማሳደግ የስራ እድልን ለመፍጠርና...

ታላቅ የምስጋና እና የስጦታ መርሃ-ግብር ጥሪ!

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ባለፉት 5 ዓመታት ላበረከቱት ከፍተኛና ታላቅ...

የቀድሞዉ የኢራን ላዕላይ መሪ አያቶላሕ ዓሊ ኻምኔይ ተቀበሩ

ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል ባለፈዉ የካቲት ማብቂያ ላይ የገደሏቸዉ የኢራን...