የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የፋይናንስ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ የኢትዮጵያ ልዑክ፤ በአዲሱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የፋይናንስ ድጋፍ ዙሪያ ከቻይና ባንክ ጋር መነጋገሩን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ልዑኩ በውይይቱ ስለ ፕሮጀክቱ ቴክኒካዊ ንድፍ፣ የአፈጻጸም ጊዜ እና አጠቃላይ የፋይናንስ መዋቅር ማብራሪያ መስጠቱ ተጠቁሟል።
“ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ያላትን መሪነት የሚያጠናክር ከመሆኑም ባለፈ ለንግድ፣ ለቱሪዝም እና ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል” ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዑክ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
የቻይና ባንክ በበኩሉ በፕሮጀክቱ ላይ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት በመግለጽ፤ የፋይናንስ መዋቅሩን ለመረዳት ከፕሮጀክቱ አስተባባሪ የአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ንቁ ግንኙነት መፍጠሩን አረጋግጧል።
