በአፍሪካ የጤና ስርዓት ላይ የሚፈጠረው ጫና ከበሽታዎች መስፋፋት ብቻ የሚመነጭ አይደለም ተብሏል።
ከዓለም አቀፍ የጤና ድጋፍ መቀነስ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ከተደጋጋሚ ወረርሽኞች፣ ከጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች እና ከሰብዓዊ ቀውሶች ጋር ተያይዞ አህጉሪቱ እየተፈተነች እንደሆነ ተነግሯል።
ይህ የተነገረው ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ ላይ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ታዬ አስቀስላሴ፣ ዓለም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቀውሶች እየተፈተነች ነው ብለዋል።
በተለይም በጤናው ዘርፍ ለረጅም ጊዜ የነበረው የውጭ ፋይናንስ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነሱ በአፍሪካ የጤና ስርዓት ላይ ተጨማሪ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
አፍሪካ ከዚህ በተጨማሪ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በቀላሉ ከሚጋለጡ አህጉራት አንዷ ነች፤ የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ የውሃና የምግብ ዋስትናን ከማወክ ባለፈ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እንዲስፋፉ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም አፍሪካ በውጭ ድጋፍ ላይ ብቻ የተመሠረተ የጤና ስርዓት ከመከተል ይልቅ የራሷን የፋይናንስ አቅም ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ምርትን ማጠናከርና በጤናው ዘርፍ ራሷን መቻል ይኖርባታል ብለዋል።
የውጭ ድጋፍ መቀነስ በጤና ስርዓቱ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ጫና ለመቋቋም ኢትዮጵያም በጤና ዘርፉ የሚመደበውን የመንግሥት በጀት በማሳደግ ከውጭ ድጋፍ በሚመነጭ የፋይናንስ ክፍተት ላይ ምላሽ ለመስጠት እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ግን በበጀት ጭማሪ ብቻ የሚገደብ እንዳልሆነና በጤናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ መድኃኒቶች፣ ክትባቶችና ሌሎች የጤና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም መገንባትም የራስን አቅም ለማጠናከር ወሳኝ ነው ተብሏል።
የአፍሪካ ሀገራት በዓለም አቀፍ የጤና መድረኮች የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማጠናከር ለአህጉሪቱ የጤና አጀንዳ ወሳኝ መሆኑም በመድረኩ ተነግሯል።
በተለይም የመድኃኒትና የክትባት ምርትን በሀገር ውስጥ ማሳደግ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ እና በወረርሽኝ ወቅት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ይረዳታልም ተብሏል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፣ ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ ያለፈችበትን ረጅም ጉዞ ለመመልከት፣ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና የሚቀሩ ችግሮችን ለመለየት እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ይህን ጉባኤ ለአራተኛ ጊዜ ማስተናገዷም ለሀገሪቱ የጤና ዲፕሎማሲ ትልቅ አቅም የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ወረርሽኞች፣ የአየር ንብረት ለውጥና ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት የጤና ስርዓቶች በተለመደው መንገድ ብቻ እንዳይቀጥሉ እያስገደዷቸው መሆኑንም ሚኒስትሯ አንስተዋል።
ኢትዮጵያም ከተለያዩ ወረርሽኞች የተገኘውን ልምድ በመጠቀም የበሽታ ክትትልና የምላሽ አቅሟን እያጠናከረች መምጣቷን ዶ/ር መቅደስ ተናግረው፣ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ መድኃኒትና ክትባት ምርት መጠን እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በጉባኤው መክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ኤችአይቪ፣ ቲቢና ወባ አሁንም በአፍሪካ የጤና ስርዓት ላይ ትልቅ ጫና የሚፈጥሩ በሽታዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህ ላይ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ያገረሸው የኢቦላ ወረርሽኝና በአንዳንድ የአህጉሪቱ ሀገራት የተከሰቱ የኮሌራ ወረርሽኞች ተጨማሪ ፈተናዎችን ይዘው መጥተዋልም ብለዋል።
ይህ ሁኔታ የሚያሳየው አፍሪካ በአንድ በኩል ከድሮ የጤና ችግሮች ጋር ስትታገል፣ በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስና የሚያገረሹ ወረርሽኞችን መቋቋም የሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን ነው ሲሉም ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል።
የአፍሪካ የጤና ዘርፍ በበሽታዎች ብቻ እንዳልተፈተነ ያነሱት ዶ/ር ቴድሮስ፣ የፋይናንስ እጥረትም የጤና ስርዓቶች በሚፈለገው ደረጃ እንዳይጠናከሩ እያደረገ ነው ብለዋል።
የውጭ ድጋፍ ሲቀንስ በቀጥታ የሚጎዱት የጤና ፕሮግራሞች ብቻ አይደሉም፤ የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ የመድኃኒት አቅርቦትን ማረጋገጥ፣ የበሽታ ክትትልን ማጠናከርና የወረርሽኝ ምላሽን ማዘጋጀት ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል ተብሏል።
በመሆኑም አገራት የራሳቸውን ሀብት የማመንጨት አቅም ማሳደግና በጤና ላይ የሚደረገውን የሀገር ውስጥ ወጪ ማሳደግ እንደሚገባቸው ዶ/ር ቴድሮስ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ የጤና ስርዓት ከአሁኑ የተሻለ የመቋቋም አቅም እንዲኖረው ቋሚና ዘላቂ የሆነ የፋይናንስ ምንጭ መፍጠር ወሳኝ መሆኑ በጉባኤው ተነስቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መሃመድ ጃናቢ በበኩላቸው፣ የፋይናንስ ጫናን፣ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረትንና ሰብዓዊ ቀውሶችን ተቋቁሞ የሚቀጥል የጤና ስርዓት መገንባት የአህጉሪቱ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
የበሽታ ቅኝትን ማጠናከር፣ የጤና አገልግሎትን ማስፋፋትና ለወረርሽኞች ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅምን ማሳደግ ከመጪው የጤና ስርዓት ግንባታ ዋና ስራዎች መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በአፍሪካ የሚከሰቱ ወረርሽኞች አህጉሪቱ የምላሽ አቅሟን ብቻ ሳይሆን የመከላከልና የቅድመ ዝግጅት አቅሟንም እንድታጠናክር እያስገደዷት ነው ያሉት ፕሮፌሰር መሃመድ ጃናቢ፣ በተለይ የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ኢትዮጵያ ያደረገችውን ጥረትና ያገኘችውን ውጤት በጉባኤው ፊት አድንቀዋል።
የአፍሪካ የጤና ስርዓት በውጭ ድጋፍ ላይ ብቻ እንዳይመሰረት ማድረግ በጉባኤው ከተነሱት ዋና ሃሳቦች አንዱ ሲሆን፣ ይህ ማለት የልማት አጋሮችን ድጋፍ ማስቆም ሳይሆን፣ አፍሪካ የጤና ስርዓቷን በራሷ ሀብት፣ በራሷ የሰው ኃይል፣ በራሷ ምርምርና በራሷ የምርት አቅም ላይ በተጨማሪ እንድትገነባ ማድረግ ነው ተብሏል። የመድኃኒትና የክትባት ምርትን ማሳደግ፣ የሕክምና ቴክኖሎጂን ማሻሻል፣ የጤና ምርምርን ማጠናከርና የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ማስፋፋት የዚህ ሂደት ዋና አካላት እንደሆኑም ተነስቷል።
የቀጣናዊ ኮሚቴው ስብሰባ የጤና ሚኒስትሮች በጋራ የሚመክሩበት ብቻ ሳይሆን፣ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የጤና መድረኮች የምታቀርበውን የጋራ አጀንዳ የምትወስንበት ነው ተብሏል።
ይህም አፍሪካ በዓለም የጤና ውሳኔ ሂደት የተሻለ ድምፅ እንዲኖራትና የአህጉሪቱ ልዩ የጤና ችግሮች በዓለም አቀፍ የጤና አጀንዳ ውስጥ በተገቢው እንዲካተቱ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ ኃላፊዎቹ ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ የአፍሪካ የጤና ስርዓት የሚጠናከረው በአንድ ተቋም ወይም በአንድ ሀገር ጥረት ብቻ አይደለም የተባለ ሲሆን፣ የሀገራት የጋራ ትብብር፣ ዘላቂ ፋይናንስ፣ የሀገር ውስጥ ምርት፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ አቅም እንዲሁም የተቀናጀ የወረርሽኝ ዝግጁነት ያስፈልገዋል ተብሏል።
ከ800 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት ይህ ስብሰባ የአፍሪካ የጤና ዘርፍ ያለበትን ሁኔታ በመገምገም፣ የተገኙ ስኬቶችን በማጠናከር እና አህጉሪቱ የሚገጥሟትን ችግሮች ለመፍታት የጋራ መፍትኤ የሚቀመጥበት እንደሆነ ተነግሯል።
76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ እስከ ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚቆይ ሲሆን፣ የቀጣናውን የጤና ፖሊሲዎችና ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች በተመለከተ ውሳኔዎች እንደሚቀርቡበት ሰምተናል።
ሸገር 102.1
