የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ ባንኩ በጠንካራ ቴክኖሎጂ እና ብቁ ሠራተኞች የታገዘ የ24 ሰዓት ጥብቅ የሳይበር ደህንንተ ጥበቃ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
በየቀኑ በርካታ የሳይበር ጥቃቶች ባንኩ ላይ እንደሚሞከሩ የገለፁት አቶ አቤ፣ በባንኩ የተዘረጋው ሲስተም በአግባቡ የሚከላከል እና ሥርዓቱን ሰብሮ ለመግባት የሚፈልግ የትኛውም አጥቂ አልፎ መሔድ የማይችለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ አቤ የሳይበር ደኅንነት በብዙ ባለድርሻዎች በጋራ የሚሠራ መሆኑን ገልፀው፣ የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት ጀምሮ ከኢንሳ፣ ከብሔራዊ ባንክና ከባንኮች የተውጣጣ የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የባንኮችን ደኅንነት ለመጠበቅ በጋራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአስር ዓመት በፊት ጀምሮ የሳይበር ደኅንነቱ ላይ ኢንቨስት በማድረግ የጠንካራ ቴክኖሎጂ ባለቤት ሊሆን መቻሉን ነው አቶ አቤ የገለፁት፡፡
አቶ አቤ እስካሁን ማንም የባንኩን ሲስተም ሰብሮ የገባ እንደሌለ ገልፀው፣ ባንኩ የመከለላከያ ሥርዓቱን በየጊዜው በማዘመን በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመጣ ጥቃትን ጭምር መቋቋም የሚያስችል የጠነከረ ሥርዓት ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
