ታዋቂዋ ኢትዮጵያዊት የፋሽን ዲዛይነርና የስራ ፈጣሪ ማህሌት አፈወርቅ (ማፊ)፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካላት የፊልም ተዋናይና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አንጀሊና ጆሊ ጋር መገናኘቷንና መወያየቷን አስታወቀች።
ማህሌት በማህበራዊ ትስስር ገጿ ባጋራችው መልዕክት፣ ከአንጀሊና ጆሊና ከሌሎች ስራ ፈጣሪዎች ጋር በኢትዮጵያ የፈጠራ ኢንዱስትሪ፣ በስራ ፈጠራና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ “ጥልቅና ትርጉም ያለው ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጻለች።
በውይይቱ ወቅት አንጀሊና ጆሊ፣ ማህሌት ለብሳው የነበረውን የማፊ ብራንድ (MafiMafi. et) ሰፋ ያለ ጃኬት በጣም መውደዷን መግለጿን የጠቀሰችው ዲዛይነሯ፣ “ይህንን ስትነግረኝ ልቤ በደስታ ቀለጠ” ስትል ስሜቷን አጋርታለች።
ማህሌት አክላም፣ አንጀሊና ጆሊን በዓለም ላይ ካሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አንዷና “በጣም ድንቅ ሰው” ስትል አሞካሽታለች። እሷን ማግኘት “ህልም ሆኖ እውን የሆነበት” አጋጣሚ እንደነበርም ተናግራለች።
ይህንን የውይይት መድረክ ላዘጋጁት ኤ ኤል ኤክስ ኢትዮጵያ (ALX Ethiopia) እና በተለይ ለአዘጋጇ ሚራፌ ምስጋናዋን ያቀረበች ሲሆን፣ አንጀሊና ጆሊን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣትና በአህጉሪቱ ለሚያደርገው የማበረታታት ስራ ፍሬድ ስዋኒከርን አመስግናለች።
ይህ አይነቱ ግንኙነት ለኢትዮጵያ የፈጠራ ኢንዱስትሪና ለወጣት ስራ ፈጣሪዎች ትልቅ መነቃቃትና እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
(ዘ-ሐበሻ ሕይወት)
