✌️ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው

Date:

✌️ከዕድሜው የገዘፈው የታሪኩ ጁዋር ጀግናውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር የጀግንነት በጎ ስራ

✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)ከካናዳ ቶሮንቶ

ታሪኩ ጁዋር፤ ይህ ስም በተለይ ለስፖርት ቤተሠቡ አዲስና እንግዳ አይደለም፤ይልቁንም ከደግነት፣ለባለውለተኞች ራስን አሳልፎ ከመስጠት፣ባለውለተኞችን ከማክበር ጋር ተያይዞ የሚነሳ የቤተሠባችን ያህል በጣም የቀረበ ታላቅ ስም ነው።

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጎ ስራዎች፣ባለውለተኞች በሚከበሩበት፣በሚዘከሩበት መድረክ ይሄ በዕድሜው ትንሽ በስራው እጅግ ግዙፍ የሆነው ታሪኩ ጁዋር የሚለው ስም በእርግጠኝነት ከፊት አለ።

በዕውነተኛ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊነቱ፣በህይወት የሌሉትን ብቻ ሳይሆን በህይወት ያሉትን ባለውለተኞችን በማስታወስ፣ለሀገር የዋሉትን ውለታ በማስታወስና በመዘከር ተለይቶ የሚታወቀው ታሪኩ ጁዋር

ከዚህ በፊት የሶስተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ባለውለተኞች ሸዋንግዛው አጎናፍርና ፍስሀ ወልደአማኑኤል፣ ለታላቁ አሠልጣኝ አስራት ኃይሌ(ጎራዴው)፣ለታላቁ ተጫዋች ሙሉጌታ ወ/የስ(ቡና ገበያ) እና የ10ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ባለውለተኞችን እነ ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ፣አለማየሁ ኃይለስላሴ(ፊኛ)፣ፍቃዱ ፎሌን በህይወት እያሉ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የፈፀሙትን ገድል ከፍ አድርጎ እንደዘከረ፣በአደባባይ እንዳከበረና ዕውቅና እንደሠጠ ሁሉ

አሁን ደግሞ በ1980ዎቹና 90ዎቹ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ደምቆ ያንፀባረቀውን፣ዛሬም ድረስ ምትክ አልባ ነው በሚል የሚመሠከርለትን፣ከአንድ ዓመት በፊት በጨካኙ ሞት የተነጠቅነውን የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ብ/ቡድን ባለውለተኛ የነበረውን ሙሉጌታ ከበደን በሞት ብትለየንም ለሀገር በከፈልከው ውለታ ስምህን ከፍ አድርገን ስናነሳ እንኖራለን በማለት ባለፈው ቅዳሜ እሱን የሚዘክር ፕሮግራም በዋሽንግተን ዲሲ በልዩ ድምቀት አከናውናል።

ከመታሠቢያ ፕሮግራሙ መጠናቀቅ በኋላ የሃሳቡ አመንጪና ዋና አዘጋጅ የሆነው ታሪኩ ጁዋርን ጀግናን ማክበርና መሸለም ጀግንነት ነው በሚል ሃሳብ አነጋግረነው ከዚህ በታች ባለው መልኩ አጠናክረን አቅርበነዋል፤መልካም ቆይታ።

♦️ሃሳቡ እንዴት ሊጠነሠስ ቻለ?

“ሁሌም ባሠብኩት ቁጥር የሚያመኝ አንድ ነገር አለ፤የሀገር ባለውለተኛ ተጫዋቾችን በአግባቡ ያለማክበርና ያለመዘከር፤በህይወት እያሉ ለሀገር ላበረከቱት አስተዋፅኦ”እግዚአብሔር ይስጥልን፤እናመሠግናለን”እንኳን በቅጡ ሳንላቸው ያመልጡናል፤በሞት ከተነጠቅን በኋላም አናስታውሳቸውም፤በዚህ መልኩ ብዙዎችን በአደባባይ ሳናከብራቸው አጥተናቸዋል፤በህይወት ያሉትንም ሳናከብር፣በአደባባይ ዕውቅና ሳንሠጣቸው መኖራችን እጅግ ያበሳጨኝ ስለነበር ለምን አንድ የዕውቅና፣የሽልማትና የክብር መድረክ አላዘጋጅም ከሚል የቁጭት መንፈስ ነው ወደዚህ ሃሳብ የገባሁት፤እግዚአብሔር ይመስገን ደጋግና በጎ ስራ የሚያስደስታቸው ሠዎች ከጎኔ ሆነው ባለውለተኞችን እያከበርን፣እየሸለምን፣ለበጎ ስራችሁ እናመሠግናለን እያልን እዚህ ደርሠናል”

♦️ለሙሉጌታ ከበደ ስለተዘጋጀው የመታሠቢያ ውድድር

“ከዚህ በፊት በህይወት ላሉም ህይወታቸው ላለፉ ባለውለተኞች ተመሳሳይ ፕሮግራም አዘጋጅተናል፤የ3ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ታላላቅ ባለውለተኞቻችን ሸዋንግዛው አጎናፍርና ፍስሀ ወልደአማኑኤል፣ለታላቁ አሠልጣኝ አስራት ኃይሌ፣ለታላቁ ተጫዋች ሙሉጌታ ወልደየስ፣እንዲሁም ለ10ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ባለውለተኞች እነ ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ፣አለማየሁ ኃይለሴላሴ(ፊኛ)፣ሙሉጌታ ብርሃኔ፣ፍቃዱ ፎሌን የመሳሰሉ የሀገር ባለውለተኞችን ዘክረናል፤ዘንድሮ ደግሞ ተተኪ እስከ አሁን ያልተገኘለትን ከ13 ዓመታት በላይ አቋሙ ሳይዋዥቅ በመጫወት ደማቅ ታሪክ ያፃፈውን ሙሉጌታ ከበደን የመዘከር፣የማስታወስ ስራን ሠርተናል፤ጀግና በዚህ ልክ ውለታው ሲታወስ፣ሲዘከር ከማየት በላይ ምንም የሚያስደስት ነገር የለም፤ደስታችንን ይበልጥ የጨመረው ደግሞ አድናቂዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ባለቤቱና ሁለቱ ልጆቹ በተገኙበት የተደረገ በመሆኑ ልዩ ስሜት እንዲሠማን አድርጓል”

♦️ለሙሉጌታ ከበደ ስላለው ፍቅር

“ከላይ እንዳልኩህ የእግር ኳሱ ባለውለተኞች በሚገባቸው ልክ አልተከበሩም፤ገብረመድህን ኃይሌ፣ሙሉጌታ ከበደ፣ዳኛቸው ደምሴ፣ተካበ ዘውዴና ለመሳሰሉት ተገቢ ክብርና ዕውቅና አልሠጠንም፤እነ ሙሉጌታ ለሀገር በከፈሉት ዋጋ ልክ ሳይሆን 400 ብር በማይሞላ ደሞዝ ነው ያንን ታሪክ ሠርተው ያለፉት፤ያ ጥበበኛ ሙሉጌታ ከበደ በዚህ ዘመን ቢኖር ሚሊዮኖች የሚከፈለው ተጫዋች ይሆን ነበር፤ቀእግሩ ብቻ ሳይሆን በጭንቅላቱም የሚጫወት በጣም የሚወደድ ጥበበኛ ተጫዋች ነበር ሙሌ፤የእሱን ችሎታ በእኔ አንደበት መግለፅ የማይታሠብ ነው፤እስከአሁን ሙሌ በትክክል ተተክቷል ብዬ አላስብም፤ይሄን ተዓምረኛ የእግር ኳስ ኮከብ አለማክበር፣ዕውቅና አለመስጠት ንፉግነትም፣ውለታ በል መሆንም ነው ለእኔ”

♦️የእሁዱ የመታሠቢያ ውድድር መጠናቀቅ

“ዕውነት ለመናገር ለሙሉጌታ ከበደ ያዘጋጀነው የመታሠቢያ ውድድር ካሠብነውና ከጠበቅነው በላይ ደሞቆ ነው የተጠናቀቀው፤ከሌሎች ታላላቅ ሠዎችና አብረውት ከተጫወቱት ሌጀንዶች በተጨማሪ ባለቤቱና ሁለቱ ልጆቹ መገኘታቸው ፕሮግራሙን ይበልጥ ታሪካዊ አድርጎታል፤የመታሠቢያው ውድድር ለ43 ጊዜ በሠሜን አሜሪካው የኢትዮጵያዊያን ውድድር ላይ የሚወዳደሩት 4 ቡድኖች የተሳተፉበት ደማቅ ውድድር ነበር፤በመጨረሻም ዲሲ ስታር በታላቁና ጀግናችን በነበረው በሙሉጌታ ከበደ ስም የተዘጋጀው የመታሠቢያ ውድድር አሸናፊ ሆኖ ተጠናቋል”

♦️በሙሉጌታ ወልደየስ ዙሪያ በአንድ ወቅት ተነስቶበት ስለነበረው ቅሬታ

“ምንም የሚደበቅ ነገር የለም እኔ በኢትዮጵያ ምድር ስደግፍ የኖርኩት አሁንም የምደግፈው ቅዱስ ጊዮርጊስን ነው፤ሙሉጌታ ወልደየስን በተመለከተ በክለብ ደረጃ ለኢትዮጵያ ቡና ቢጫወትም ታሪክ የማይረሳው ትልቅ ባለውለታ ነው፤ሙሉጌታ ወልደየስን ሳንጠግበው ነው ድንገት ከኳስ የተለየው፤ሙሉጌታ ተጎድቶ እንጂ ፈልጎ ኳስ አላቆመም፤በሚያስቆጭ ሁኔታ ከእግር ኳሱ የተለየን ባለውለታ ማክበር፣ዕውቅና መስጠት ሊያስመሠግን እንጂ ሊያስወቅሠኝ አይገባም፤ሙሌ አመለሸጋና ምሳሌ የሚሆን በጣም የምወደው ተጫዋች በመሆኑ ሽልማቱ የሚያነሠው ካልሆነ የሚበዛበት ነው ለማለት ይቸግረኛል ደግሞም ይገባዋል”

♦️በመጨረሻ

“በመጨረሻ የሌጀንዱ ተጫዋቻችን ሙሉጌታ ከበደ መታሠቢያ በድምቀት እንዲጠናቀቅ የረዳንን ፈጣሪን በቅድሚያ ማመስገን እወዳለሁ፤በመቀጠል ለውድድሩ መሳካት የተረባረቡትን በተለይ አራቱ ክለቦች ዲሲ ስታር፣ሚካኤል፣የዩኒቲና የሜሪላንድ ቡድኖች ከመሳተፍ በዘለለ ወጪውን በመሸፈናቸው ከፍ አድርጌ አመሠግናቸዋለሁ፤ሌጀንዶቻችን ተካበ ዘውዴ፣ሠለሞን መኮንን(ሉቾ)፣ሙሉጌታ ወልደየስ እና ዳኛቸው ደምሴን የመሳሳሉ የቀድሞ ተጫዋቾች ፕሮግራሙንም እኔንም አክብረው ስለተገኙ ማመስገኛ ቃላት የለኝም።

DNV እና ሜሪላንድ አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ሙሉጌታ ከበደን የሚወደው የብርሃን ጋራዥ ባለቤት ሁላችሁንም ከጎኔ ስለቆማችሁ ከልብ አመሠግናለሁ፤በቀጣይ ግን አሁን በያዙኩት መንገድ ስለማይችልና ከባድ ጫና ስላለው ቦርድ በሚቋቋምበት ዙሪያ እየሠራንበት ነው፤እነዚህ የምናከብራቸው ታላላቅ ተጫዋቾች ሲጫወቱ ማየት አይደለም ላልወለድ ሁሉ እችላለሁ፤ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ አይደል ያለው ድምፃዊው የትናንት ባለውለተኞችን እንደ ሸንኮራ መጦ ከመጣል በተደራጀ መንገድ ማክበር ውለታ በል ከመሆን ያድናል፤እኔ በህይወቴ በበጎ ነገር ከምጠቅሳቸው ነገሮች አንዱ በመሆኑ ስደሠትበት እኖራለሁ፤ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያሎችም ለሠጣችሁኝ ዕድል ከልብ አመሠግናለሁ”

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንግሊዝ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አገደች

የእንግሊዝ መንግሥት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትና ታዳጊዎች...

አሜሪካ 300 ሚሊዮን ዶላር ለኢራን ልትሰጥ ነው መባሉን ትራምፕ አስተባበሉ

አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ...

ደህና ሁን! ሰሜ…ስሜ!

“ከልጅነታችን ጀምሮ ጥበብ አገናኝታን ፣ በግሽ አባይ የባህል ቡድን...

የአህጉሪቱን የርስ በርስ ንግድ ልውውጥ 250 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቀደ

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ፀሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ...