ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትግራይ ክልል እየተባባሰ የመጣውን ሰብአዊ ቀውስ ለመፍታት የአፍሪካ ሕብረት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠሩ ጥሪ አቀረበ።
ህወሓት ለአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በጻፈው ደብዳቤ፤ በክልሉ በሚገኙ የተፈናቃይ ማዕከላት ውስጥ ያለው ሁኔታ በእጅጉ እያሽቆለቆለ መሆኑን በመግለጽ፣ ሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል።
ተፈናቃዮች ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውንና የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የጠቀሰው ድርጅቱ፤ “ሁኔታው የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የሚጥስ ነው” ሲል አፅንዖት ሰጥቷል።
ህወሓት በደብዳቤው፤ የአፍሪካ ሕብረት እና አጋሮቹ ለሁሉም የተፈናቃይ ማዕከላት አስቸኳይ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲፈቀድ እንዲጠይቁ፣ እርዳታ ተቋርጧል በሚል በቀረበው ክስ እና በተመዘገቡ የሞት አደጋዎች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂዱ፣ እንዲሁም የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
“ጥበቃ ሊደረግላቸው ቃል የተገባላቸው ወገኖች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት እየሞቱ ባለበት ሁኔታ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተተግብሯል ሊባል አይችልም” ያለው የህወሓት ደብዳቤ፤ እርምጃ አለመውሰድም ተባባሪነት መሆኑን አስጠንቅቋል።
ድርጅቱ አክሎም፤ የሰብአዊ ቀውሱ በታኅሳስ 2018 ዓ.ም ተባብሶ መቀጠሉንና የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር ህዳር 2013 በጀመረው ጦርነት ወቅት ከተመዘገበው በላይ መሆኑን ገልጿል።
በተለይም በ #ህጻጽ፣ #ሽሬ፣ #አድዋ፣ #ዓቢ_አዲ፣ #ዓዲግራት እና #መቀለ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ለመሰረታዊ ፍላጎቶች እጥረት መጋለጣቸው ፓርቲው አክሎ ገልጿል።
በተጨማሪም ህወሓት የፌዴራል መንግሥትን ሰብአዊ እርዳታ በማደናቀፍ ከሷል። ፓርቲው፤ ለተፈናቃይ ማዕከላት የሚደረገው የእርዳታ አቅርቦት ያለምንም መቆራረጥ እየቀረበ ነው በማለት የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ያቀረበውን መረጃ ውድቅ አድርጎታል። “ትርጉም ያለው እርዳታ ወደ ተፈናቃይ ማዕከላት እየደረሰ በሌለበት ሁኔታ የተነገረ የፕሮፓጋንዳ መግለጫዎች ናቸው’ ሲል ፓርቲው ገልጿል።
“መግለጫው፤ በማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና በዳያስፖራው የሚሰበሰቡ የእርዳታ ገንዘቦችን ጨምሮ በማህበረሰቡ የሚመሩ የእርዳታ ጥረቶች ገደብ ተጥሎባቸዋል፣ እንዲሁም ወደ መንግሥት ቁጥጥር ስር ባሉ የባንክ ሂሳቦች ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል ሲልም ከሷል።
በተጨማሪም ህወሓት የሰብአዊ ቀውሱን ምዕራብ ትግራይ ካለው ያልተፈታ ሁኔታ ጋር በማያያዝ፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ አራት መሰረት አሁንም ወደ ቀያቸው አልተመለሱም ብሏል።
