በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ ‘መጋቢት 2’ በግዛቱ የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን እንዲሆን የቀረበን የውሳኔ ሐሳብ በከፍተኛ ድምጽ አፀደቀ።
ይህ ‘ኤችአር 441’ የተሰኘው የውሳኔ ሐሳብ የፀደቀው ባለፈው ሳምንት በግዛቲቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገ የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ነው።
በአሜሪካ የግዛቶች ምክር ቤት አሠራር መሠረት፣ ይህ ውሳኔ በግዛቲቱ የሕግ መዝገብ ላይ የአድዋ ድል በይፋ ዕውቅና ያገኘበት ታሪካዊ ሰነድ ሆኖ በቋሚነት ይቀመጣል።
ይህ የውሳኔ ሐሳብ ረቂቅ፣ የአውሮፓውያኑ ‘ማርች 2 ቀን 2026’ የ130ኛ ‘የአድዋ ድል ቀን’ ሆኖ በፔንሲልቬኒያ ግዛት ዕውቅና እንዲሰጠው የሚደነግግ ነው።
ውሳኔው በሪፐብሊካን እና በዲሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴዎች በተሰጠ 195 ከፍተኛ የድጋፍ ድምጽ እና በ6 ተቃውሞ ብቻ ነው የፀደቀው።
ረቂቁ የቀረበው ከወራት በፊት ቢሆንም የምክር ቤቱን የውስጥ አሠራሮችን አልፎ፣ ውይይቶች ተደርገውበት ከቆየ በኋላ የውሳኔ ድምጽ የተሰጠበት ግን ባለፈው ሳምንት ነው።
”ኤችአር 441” ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡን ለፔንሴልቬኒያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የሰሜን ፊላደልፊያ ሜንገመሪ ካውንቲ፣ የሕዝብ ተወካይ የሆኑት ሴናተር ቤንጃሚን ሳንቼዝ ናቸው።
ቢቢሲ የፀደቀውን የውሳኔ ሐሳብ አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡት ሴናተሩን በኢሜይል ጥያቄ አቅርቦላቸው የነበረ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስኪጠናቀር ድረስ ምላሽ አልሰጡም።
ተጠይቀው በግዛቲቱ ቀን መቁጠሪያ (ካላንደር) ውስጥ ‘የአድዋ ቀን’ ተብሎ ተካትቶ ታስቦ ይውላል። ይህም ትልቅ ትርጉም ያለው ተዕምርታዊ (ሲምቦሊክ) ነው’ ብለዋል።
ሆኖም ውሳኔው በዚያው ግዛት ተፈፃሚ የሚሆን እንጂ ወደ ፌደራል የሚያመራ እንዳልሆነም አክለዋል።
ይሁንና አድዋ በበርካታ ግዛቶች ዕውቅና እያገኘ ከመጣ፣ ወደፊት ኢትዮ- አሜሪካውያን፣ ጥቁር አሜሪካውያን እና የተለያዩ አደረጃጀቶች ጉዳዩን በጊዜ ሂደት ወደ ፌደራል ይዘውት እንዲሄዱ አንዳች ዕድል ሊፈጥረ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
አድዋ ኢትዮጵያ በአፄ ምንሊክ እና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ አመራር ሰጪነት የጣሊያን ወራሪዎችን ድል በመምታት ሉዓላዊነቷን አስከብራ የቆየችበት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቁር ሕዝቦች ነፃነት እና ፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ምልክት የሆነ ታሪካዊ ድል ነው።
ከአድዋ ድል በኋላ በርካታ አገራት የፀረ-ቅኝ ግዛት ተጋድሏቸውን በማጠናከር ለዓመታት በዘለቀ ትግል ነፃነታቸውን መቀዳጀት ችለዋል።
በአፍሪካ ሁለት አገራት ቅኝ አለመገዛታቸውን ታሪክ የሚያስረዳ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ራሷን ያስከበረችው አርበኞቿ ባደረጉ ትግል ነው።
በአድዋ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ የጣሊያን ሠራዊት አባላት ሲገደሉ ሌሎች ሺህዎች ደግሞ ተማርከዋል። መድፎችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያዎችም መማረካቸውን ታሪክ ያስረዳል።
በተጨማሪም የጣሊያንን ሠራዊት ከመሩት መኮንኖች መካከል ጄነራል አልቤርቶኒ ሲማረክ ዋና አዛዥ ጄነራል ባራቴሪ ሸሽቶ አምልጧል።
ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ድል የተጎናፀፈችበትን የካቲት 23 ቀንን በየዓመቱ በደማቅ ታሪካዊ ሁነቶች ታከብራለች።
ባለፈው የካቲት ወርም 130ኛው የአድዋ ድል በዓል ተከብሯል።
bbc
