የአቡሻህር ሊቃውንት ‹‹የዘመን ትርጓሜ በልብ ውስጥ ያለ የወሰን አምሳል ነው›› ካሉ በኋላ ይህ ዘመን የሚባለው የዕድሜ ቀጠሮ ከስያሜው አንጻር ለሦስት ወገን ይከፈላል፡፡ ያለፈው፣ ያሁን እና የሚመጣው ዘመን ነው ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ወደ አምስት መስፈሪያ ወይም መቁጠሪያ ይከፈላል፡፡ እነርሱም፡- ዓመት፣ ወር፣ ሳምንት፣ ዕለት፣ ሰዓትና ኬክሮስ በመባል፡፡
ኬክሮስ ትንሹ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ሰዓት፤ ሌሊትንና መዓልትን አንድ አድርጎ አንድ ዕለት ከሚያሰኙ ሃያ አራት ሰዓቶች አንዱ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡
ዕለት ሳምንትን የሚያስገኝ የአንድ ሱባዔ ዕለት አንድ ሰባተኛ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ሳምንት ወርን የሚያስገኝ የአንድ ወር አንድ አራተኛ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ወር ዓመትን የሚያስገኝ የአንድ ዓመት አንድ ዐሥራ ሁለተኛ ክፍለ ዘመን ነው፡፡
በዚህ ውስጥ ሁሉ ‹‹ጳጉሜን ሕያዊት›› ናት፡፡ ጳጉሜን ‹‹ሄፓጎሜኔ›› ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ መሆኑንና ትርጉሙም ጭማሪ ማለት እንደሆነ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ይበይናል፡፡ በግእዙም ተወሳክ እየተባለችም ትጠራለች፤ ያው ተጨማሪ ለማለት ነው፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በተባለው መጽሐፋቸው እንዳመላከቱት ጳጉሜን ከዐውደ ወርኅ ስለተረፈችና ባመት መጨረሻ ስለተገኘች ተረፍ ትባላለች፡፡ ይህችው አምስት ቀን ከሩብ የነበረችው ሕያዊት ጳጉሜን በአራተኛ ዓመት ትሞላና አምስት ቀን የነበረችው ስድስት ቀን ትሆናለች፡፡
ስድስተኛውን ጳጉሜን አራቱ ወንጌላዊያን (ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ) በሰዓትና በኬክሮስ ከአራት አድርገው ስለተካፈሉት እንደ አምስተኛ ከአበቅቴ ገብቶ አይቆጠርም፤ ስድስተኛነቱም ለአለፈው ለሉቃስ ጳጉሜን ነው እንጂ ለሚመጣው ለዮሐንስ ጳጉሜን አይደለም፡፡
አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ ‹‹ለኢትዮጵያ ታሪኳ-ነው መልኳ›› በተባለው መጽሐፋቸው ‹‹ጳጉሜን ወር እንዳትባል አቅም ያንሳታል፤ ሳምንት እንዳትባል አምስት ቀን ብቻ ሆናለች›› ካሉ በኋላ አውሮፓውያን የወር ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ እኛ የወርን ቁጥር ሰላሳ ብቻ ስናደርግ እነሱ ሰላሳ አንድ ብለው የሚቆጥሩት ወር አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ሳያደርጉ የዓመት ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ የዓመቱንም ቀን ቁጥር ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ከኑስ ብለው ደምረውታል፡፡ ሊቃውንቱ አንድ ሱባዔ ቀን፣ ቀኖና እንዲፈጸምባት ለብቻ ለይተው አኑረውታል›› ይላሉ፡፡
አፈ ሊቅ አክሊሉ በዚሁ መጽሐፋቸው ስለ ‹‹ሕያዊት ጳጉሜን›› የሚሰጡትን ማብራሪያ በመቀጠል ‹‹ይህ ዓለም ኑሮ፣ ኑሮ በመጨረሻ ያልፋል ፤ ጌታ ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል፤›› ሲሉ ‹‹የጌታ የመምጣቱ ነገር እንዲነገርባት፣ መስዋዕት እንዲሰዋባት፣ ምጽዋት እንዲመጸወትባት ለይተው መድበዋታል›› ይሉና ሕዝቡም በተለምዶ ጳጉሜን ዕድሜ ትሰጠናለች፣ ኋላም ታድነናለች ብለው ጾም እንደሚጾሙባትም በማስረጃነት የቅዱስ መልከ ጼዴቅን ድርሳንና ንግሥት ዘውዲቱ ምኒልክ በዚሁ አስተሳሰብ የጾም ሥርዐት ይፈጽሙባት እንደነበረ ታሪክ ጠቅሰው ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የነቢዩ ሄኖክ መጽሐፍ የዓመቱን አቆጣጠር ሦስት መቶ ስድሳ አራት አድርሶ ገለጠው እንጂ ጳጉሜን ጨርሶ አልዘነጋትም፡፡ ‹‹የጳጉሜን አቆጣጠር አንዱን ከወር ሌላውን ደግሞ ከዓመት ጋራ ቢያደርገውም በሁሉም አቆጣጠር ውስጥ ሕያዊት ሆና መገኘቷ የታወቀ ነው፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡
ጳጉሜን የወራት ሁሉ ፍጻሜ፣ በዓመት ውስጥ መከራና ደስታ ሲያፈራርቁ የቆዩት ወራት አልፈው አዲሱን ዓመት ይዞ የሚመጣው የመስከረም ዋዜማ፣ የዓመቱን መፈጸም የምታስረዳ የዘመን ፍጻሜ ናት፡፡ በዚህች የፍጻሜ ዘመን፣ ነገረ ምጽኣትን የምንዘክርበት ዓመት እንደተፈጸመ ሁሉ የዚህ ዓለም አኗኗራችን ይፈጸማል፤ ዓለሙም ምኞቱም እንደዚሁ ያልፋሉ ብለን ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ጳጉሜን ስለ ዓለሙ ማለፍ የተነገረውን ሁሉ የምናስብባት ናት፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው፡፡ እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደመጎናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፤ ይለወጣሉ፡፡ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም፤›› በማለት ይናገራል፡፡ (መዝ 101፥25)
ቅዱስ ዮሐንስም በመልዕክቱ ‹‹ዓለሙም ምኞቱም ያልፋል፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤›› ሲለን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ‹‹ሰማይና ምድር ያልፋል፤›› ብሏል፡፡ (ማቴ 5፥15) እናም ከላይ በጠቀስነው አግባብ መሠረት ነገረ ምጽኣትን በጳጉሜን እናስባለን፡፡
ጳጉሜን አጭር እንደመሆኗ በአምስት ወይም በስድስት ቀናት ተጠናቃ ታልቃለች፡፡ የጌታችን አመጣጥም እንዲሁ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! በጌታ ዘንድ አንድ ቀን ሺህ ዓመት፤ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ፡፡ ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ እንዳይጠፉ ወዶ ስለእናንተ ይታገሣል፤›› ያለው፡፡ (2ኛ ጴጥ 3፥8)
ጳጉሜን የአዲስ ዓመት መቀበያ ዋዜማ እንደመሆኗ አዲስ ሕይወት ይዛ ትቀርባለች፡፡ የምናዝንበትን ወይም የምንደሰትበትን ዓመት ታስረክበናለች፡፡ በዚህ አንጻር ዕለተ ምጽኣትም አዲስ ሕይወትንና ከፍርድ በኋላ የሚመጣን ኑሮ የሚያስረክብ ስለሆነ ጳጉሜን እናስባታለን፡፡
በዚህች የዘመን ድራር በአዲሱ ዓመት መልካም እንዲገጥመን፣ ዓመቱ የጥጋብ፣ የደስታ የጤና እንዲሆንልን አድርግልን ብለን ፈጣሪን እንደምንለምን ሁሉ ከዕለተ ምጽኣት በኋላ ያለው ሕይወታችንም መልካም እንዲሆን ወደ መንግሥትህ እንድንገባበት አድርግልን፤ በመንግስትህም አስበን የምንልባት ጊዜም ናት፡፡
በጳጉሜን ስለ ቀጣዩ ኑሯችን እቅድ እናወጣለን፤ የጋብቻ ሥርዐታችንን ለመፈጸም፣ ቤተሰቦቻችንን ለመርዳት፣ ለመማር፣ ሀገርን ለማገልገል እና ዕቅዳችንን በተግባር ለማዋል ራሳችንን እናዘጋጃለን፡፡
አዲሱ ዓመት ምድራዊ ኑሯችንን ከላይ በጠቀስነው መልኩ ለማበጃጀት እንደምንጨነቅ ሁሉ ከዕለተ ምጽአት በኋላ ስለሚገጥመን ሰማያዊ ኑሮ ማሰቢያ ጊዜ መሆኗን ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡
ሕያዊት ጳጉሜን በምድርም ሆነ በሰማይ፣ ስለሚገጥመን አዲስ ሕይወት እናስብባታለን፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሚገኙ ምዕመናን ከተቻላቸው እንዲያስቀድሱ፣ በግል መጾም የሚፈልጉም እየጾሙና እየጸለዩ እንዲሰነብቱባት ሁና የተገኘች ነች፡፡ በዚህች ወቅት ብዙዎች ወደ ገዳማት በመሄድ ይሰነብታሉ፡፡ ምዕመናን በየጸበሉ እየሄዱ ይጠመቃሉ፡፡ በዚህች ወቅት የሚወርደው ዝናብ እንደ ፀበል ስለሚቆጠር ሕፃናትም ሆኑ አዋቂዎች ራሳቸውን በሚወርደው ዝናብ ለማስመታት የሚያደርጉት ጥረትም የጳጉሜን ልዩ ትዝታ ነው፡፡ ጳጉሜን በሰማያዊም ሆነ በምድራዊ ግብራችን ልንዘክራት የሚገባን የዘመን ፈርጥ ናት፡፡ ሕያዊነቷም ይኼው ነው፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!!
