ከልጅነት እስከ ወጣትነት፣ ከጉልምስና እስከ ሽምግልና ድረስ በአስደናቂ እና አይበገሬ ታሪኮች የተሞላው የብርሃኔ አበራ /ማዘር/ ግለ-ታሪክ ከስምንት ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ እነሆታትሞ ለአንባቢያን በቅቷል፡፡ በብዙዎች ዘንድ “ማዘር” በሚለው ስያሜ የምትታወቀው የብርሃኔ አበራ አስደናቂ ታሪክ ከንጉሥ ኃይለስላሴ እስከ ደርግ፣ ከኢህአፓ እስከ ኢህዴን ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ ማዘር ብርሃኔ በተለይም በኢህአፓ እና በኢህዴን ትግል ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ ነበራት፡፡ በእነዚህ ትግሎች ውስጥ መላው ቤተሰብ ለማለት በሚያስችል ልክ የተሳተፈ ሲሆን፣ በተለይም በኢህዴን የትጥቅ ትግል ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ ከ30 በላይ አባላት ወደ በረሃ መውጣታቸው ይታወቃል፡፡ የታሪኩ ዋና ባለቤት የሆነችው ማዘር ብርሃኔ ደግሞ ታግሎ በማታገሉ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ ተጫውታለች፡፡
ብርሃኔ አበራ የተወለደችው መጋቢት 28፣ 1934 ዓ.ም በሰቆጣ ከተማ ሲሆን፣ ወላጆቿ አበራ ለማ እና ስንዴ አዳነ በመላው ዋግ በሃብት እና በዝና የገነኑ ሰዎች ነበሩ፡፡ መስላወይ በ1951 ዓ.ም ፈቅዳ የመሠረተችው ትዳርም ቢሆን ከዚህ የበለጠ ውጤታማ ነበር፡፡ በሂደት “ማዘር” ለመባል የበቃቸው ስመ ብዙዋ ሴትታሪክ የሚጀመረው እንደ ቀየው ወግ እና ልማድ ገና በሰባት ዓመቷ ከተዳረችበት እለት አንስቶ ነው፡፡ በትምህርቷ ከፍተኛ ውጤት ታስመዘግብ የነበረችው ታዳጊዋ መስላወይ በዚያው የመቀጠል ፍላጎት የነበራት ቢሆንም፣ ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡ ብርሃኔ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ራሷን ለሴቶች መብት እና እኩልነት የምትሞገት ሴት ሆና አግኝታታለች፡፡ በዘመኑ “ቱጃር” ይባልየነበረውን ቤተሰቧን የደረግ አገዛዝ በልዩ ሁኔታ ማጥቃት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ስርዓቱን አምርራ መቃወም ጀመረች፡፡ በሴትነቷ ያጣቻቸውን መብቶች ለማስከበር መታገል የጀመረችው ብርሃኔ በሂደት አስከፊውን የደርግ ስርአትም ባላት አቅም የምትዋጋ ታጋይ ሆነች፡፡
በ1960ዎቹ መጨረሻ የኢህአፓ ትግል መቀጣጠል ሲጀምር ቀለም-ቀመስ የነበረችው ወጣት ብርሃኔ አበራ ትግሉን ለመቀላቀል አፍታ አልወሰደባትም፡፡ በኢህአፓ የህቡዕ አደረጃጀቶች ውስጥ ገብታ ከመታገል አልፋ ልጆቿን ጨምሮ በዙሪያዋ ያሉት የቤተሰብ አባላት ኢህአፓን እንዲቀላቀሉ አበረታትታለች፡፡ በዚህም በመጽሃፉ ውስጥ በዝርዝር እንደምንመለከተው በእርሷ፣ በባለቤቷ፣ በልጆቿ እና በቀሪው የቤተሰብ አባላት ላይ የህይወት ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ አደጋዎችን ተጋፍጣለች፡፡ ኢህአፓ ከፈረሰ በኋላም ቢሆን ማዘር ብርሃኔ ተስፋ አልቆረጠችም፡፡ ኢህዴን በዋግ ተራራዎች መሃል ተመሥርቶ የሰቆጣ ከተማን ማዳረስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ ቀደም ሲል ኢህአፓ ውስጥ የምታውቃቸውን ታጋዮች ካገኘች በኋላ ትግሉን ተቀላቅላለች፡፡ በሂደትም በሁኔታዎች አስገዳጅነት የትውልድ ከተማዋን ትታ እና ቤተሰቧን አስከትላበረሃ በመግባት እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ስትታገል ቆይታለች፡፡
የማዘር ብርሃኔ ታሪክ በእያንዳንዱ የህይወት ምእራፍ በፈርጀ ብዙ ፈተናዎች እና አልሞት ባይ ተገዳይነት የተሞላ ነው፡፡ “የ7 ዓመት ታዳጊ ከነበረችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ እርጅና ድረስ የዘለቁት እነዚህ ሰንሰለታማ ፈተናዎች ምን ይመስሉ ነበር፣ ብርሃኔ እነዚህን ፈተናዎች እንዴት አለፈቻቸው፣ ዛሬ በ83 ዓመቷ አምስተኛ ትውልድ ለማየት የበቃችው ማዘር በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች” የሚሉትን ጉዳዮች ከመጽሃፉ እናነባለን፡፡ የማዘር እና የቤተሰቧ ድንቅ ተጋድሎ ከዚህ ቀደም በተበታተነ ሁኔታ ሲነገር የቆዬ ቢሆንም፣ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በጥናት ተደግፎ ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡ “ማዘር ብርሃኔ፡ ዕንቁ የተጋድሎ ታሪክ” በሚል ርዕስ በአቶ ታደሰ ካሳ የተዘጋጀው ይህ መጽሃፍ በእናታችን 83ኛ የልደት ቀን ነገ እሁድ መጋቢት 28፣ 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ኔክሰስ ሆቴልከጠዋቱ 3:00 ጀምሮ በድምቀት ይመረቃል፡፡
መጽሃፉ የሚሸጥባቸውን ማከፋፈያዎች እና ሱቆች ወደፊት እናሳውቃለን፡፡ ለአሁኑ፣ አስተማሪነት ያለው አንድ ተጨማሪ ታሪክ ለአንባብያን ሁሉ ተበርክቷልና እንኳን ደስ አለን እንላለን፡፡
