‘ልዩነትን ማክበር ‘በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት መጋቢት 27 2017 ዓ.ም ምሉዕ ፋውንዴሽን የኦቲዝም ቀንን አክብሯል።
በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ከምሽቱ 12 ሰዐት ጀምሮ በተከናወነው ታላቅ ሥነ ሥርዓት የቀድሞዋ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ወይዘሮ ሣህለወርቅ ዘውዴ በክብር እንግድነት ታድመዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን በሙዚቃ ያስጠራው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋም በፒያኖ ረቂቅ ሙዚቃ አቅርቧል፡፡
የምሉዕ ፋውንዴሽን መሥራች ወይዘሮ ትዕግስት ኃይሉ ካሣ የመጀመሪያ ልጇ በኦቲዝም ጥላ ስር የሚኖር ሲሆን በእንዴት ያለ መንገድ ልጇን እንዳገዘችው ግንዛቤ ስታስጨብጥ ቆይታለች።
የኦቲዝም ቀን በተከበረበት በዚህ ዕለት ልዩ ልዩ የግጥም እና የድራማ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ገጣሚያን ህሊና ደሳለኝ እና ረድኤት አሰፋ መሣጭ ግጥሞችን አቅርበዋል።
የምሉዕ ፋውንዴሽን መሥራች ወይዘሮ ትዕግስት ኃይሉ ስትናገር
“….ምሉዕ ፋውንዴሽን በኦቲዝም ጥላ ስር የሚኖሩ ልጆችን ለማገዝ አስቦ ሥራ የጀመረው በመኖሪያ ቤታችን ውስጥ ነው።
ከዚያ በኃላ ግን በሒደት በሺህ የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ጋር በተለያየ መልኩ መድረስ ችለናል። ቀዳሚው ለኦቲስቲክ ልጆች ቀጥተኛ የቴራፒ አገልግሎት መስጠት ነው። በአሁኑ ጊዜም 40 ልጆች የቴራፒ አገልግሎት እያገኙ ይገኛሉ።
በመቀጠል በቴራፒ ማዕከሉ ባለሙያዎቻችን የሚሰጡት አገልግሎት ብቻውን ፍሬ ስለማያፈራና የተነሳንበት ምሉዕ ማሕበረሰብ የመፍጠር ዓላማችንን መከተል ስላለብን የሕፃናቱን ቤተሰቦች በሥነ-ልቦና እና በተግባር ተኮር ዕውቀት የማብቃት ሥራ ሠርተናል።
በዚህ የሥልጠና መርሀ- ግብሩም ከ2200 በላይ ለሚሆኑ ለልዩ ፍላጎት ወላጆች፣ ተንከባካቢዎች እንዲሁም በትምህርት ቤቶች፣ በሕፃናት ማሳደጊያዎች፣ በሆስፒታሎች እና በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ በዕውቀት የተደገፈ ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡”በማለት ምሉዕ እያከናወነ ያለውን ተግባር በዝርዝር አስረድታለች፡፡
ወይዘሮ ትዕግስት ኃይሉ ከኦቲዝም ጋር በተያያዘ፣ ለ14 ዓመታት ልዩ ጥናት ያደረገች ሲሆን በ 2012 ዓ.ም ከተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን ጋር በመሆን መፅሀፍና ኦድዮ ሲዲ አሳትማለች፡፡ ከዚያም በመቀጠል የምሉዕ ፋውንዴሽን ሀሣብ ተጠነሰሰ።
ምሉዕ ፋውንዴሽን፣በኦቲዝም ዙሪያ ወላጆች ግንዛቤ እንዲያገኙ እየሠራ ያለ ተቋም ሲሆን በአገር ውስጥ እና በባህር ማዶ የሚገኙ ግለሰቦችና ተቋማት እያገዙት የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡
በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የተካሄደውን የኦቲዝም ቀን መድረክ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መድረኩን የመራችው የኪነ ጥበብ ሰው አዜብ ወርቁ ስትሆን በዕለቱም ለታደሙ ሰዎች ምሉዕ ፋውንዴሽንን እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቧል።
