የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብርተኛ ድርጅት እንዲሠረዝ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ምክር ቤቱ ባሄደው ልዩ ስብሰባ ህወሓትን ከሽብርተኛ መዝገብ ለማንሳት በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔውን አፅድቋል። ኾኖም ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብርተኝነት መዝገብ መሰረዙን፤ 61 የፓርላማ አባላት ተቃውመዋል። አምስት የፓርላማ አባላትም ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች፤ በተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በግል ተመራጮች የተያዙት 16ቱ ብቻ ናቸው።
በፓርላማው ውሎ ከገዢው ፓርቲ የፓርላማ ተመራጮች “ጠንከር ያሉ” አስተያየቶች መቅረባቸውን ስብሰባውን የታደሙ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። ከእነዚህ የፓርላማ ተመራጮች መካከል የሆኑ አንድ የብልጽግና ፓርቲ አባል፤ “የፖለቲካ መረጋጋት እና ደህንነት በጣም በአሳሳቢነት ላይ ባለበት ሰዓት፤ የህወሓትን አሸባሪነት አንስቶ ወደ ሥርዓቱ ማስገባት ለመንግስትም አደጋ ነው ብዬ የራሴን ምክረ ሃሳብ እሰጣለሁ” ብለዋል። “መሬት ላይ ያሉ ልንቀርፋቸው የሚገቡ በርካታ ችግሮች አሉ” ያሉት እኚሁ የፓርላማ አባል፤ “ ‘አሁን ህዝቡስ ከእኛ ጋር ነው ወይ’? የሚለውን ጥያቄ መንግስት ማየት ያለበት ይመስለኛል” ሲሉ መቅደም ያለበት ነገር መኖሩን በአጽንኦት ተናግረዋል። “የህዝብ ድጋፍ በደንብ ሳይኖረን ይኼንን አሸባሪ ቡድን ወደ ስርዓቱ ውስጥ መክተት ሁለት ዕጣ ፈንታ አለው። አንድ መንግስት ስልጣኑን ለአሸባሪዎች መስጠት፤ ሁለት ኢትዮጵያን ወደ ተለየ ቀውስ መስደድ” ሲሉም ውሳኔው ይኖረዋል ያሉትን ውጤት ለፓርላማው አስረድተዋል።
በፓርላማው የመንግስት ተጠሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ያቀረቡትን የውሳኔ ሃሳብ የተቃወሙት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባል ግን እኒህ አባል ብቻ አይደሉም። ሌላ አንዲት የብልጽግና ፓርቲ ተመራጭም፤ ህወሓትን ከአሸባሪነት መሰረዝ “ጊዜው አይደለም። ቆም ብለን ማሰብ መቻል አለብን” ሲሉ ተደምጠዋል። የፓርላማ አባሏ፤ ከውሳኔው በፊት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት “ዝርዝር ሪፖርት ለፓርላማው ሊቀርብ ይገባል። የስምምነቱ እያንዳንዱ ነጥብ የት እንደደረሰ መገምገም አለበት” ሲሉ በቅድሚያ መደረግ ያለበትን ጉዳይ አመልክተዋል። ከትጥቅ አፈታት ጋር በተያያዘም የተወካዮች ምክር ቤት አባሏ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። “እንደ አንድ የምክር ቤት አባል ‘ምን ያህል [መሳሪያ] መውረድ ነበረበት?’ ‘ምን ያህል ወረደ?’ ብሎ ህዝብ ቢጠይቀኝ እኔ መልስ የለኝም። በቂ መረጃ አልተሰጠኝም” ብለዋል ተመራጯ። ሌላ ሶስተኛ የገዢው ፓርቲ አባልም በተመሳሳይ የመንግስት ተጠሪው ያቀረቡትን ውሳኔ ሃሳብ “ወቅቱን ያልጠበቀ” ሲሉ ነቅፈውታል።
ከብልጽግና ፓርቲ አባላት በተጨማሪ የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮችም በስብሰባው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተመራጩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ “የፌደራል መንግስቱ ከሞላ ጎደል በሆደ ሰፊነት የሚጠበቅበትን ነገር እያደረገ ቢሆንም፤ በትህነግ ወይም በትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር በኩል ግን የሰላም ስምምነቱ እየተተገበረ ነው የሚል እምነት የለንም” ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም አስታውቀዋል። “ከሽብር እና ከጦርነት ፖለቲካ የመስራት ባህሪ ባልተቀየረበት ሁኔታ፤ ትህነግን ከሽብር ሊስት ማንሳት ታሪካዊ ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ” ሲሉም ዶ/ር ደሳለኝ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። የአብኑ የፓርላማ ተወካይ በአስተያየታቸው ማሳረጊያ ላይ “በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ትህነግ የገባውን ቁርጠኝነት መፈጸም አለመፈጸሙ በአግባቡ ተረጋግጦ” ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ ጠይቀዋል። የህወሓት “ቁርጠኝነት” “ገለልተኛ በሆኑ እና ፓርላማው በሚያቋቁመው አካል እንዲጣራ” ሲሉም ተጨማሪ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል። የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዩ በዚሁ ንግግራቸው “መብራራት አለባቸው” ያሏቸውን ጉዳዮችንም አንስተዋል። “ህወሓትን ከሽብርተኝነት ማንሳት ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ ይችላል ወይ?” የሚል ጥያቄ ያነሱት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳቡን “ለሌላ ጊዜ እንዲሻገር በተቃውሞ ውድቅ እንዲያደርገው መጠየቅ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
የተቃዋሚው የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌሕዴድ) ተመራጭ አቶ አለሳ መንገሻ በበኩላቸው፤ የሰላም “ስምምነቱ አተገባበር ግልጽ ባልሆነበት፣ ከህዝቡ በርካታ ጥያቄ እየተነሳ ባለበት በዚህ ጊዜ፤ ይኼ ውሳኔ ሃሳብ ጊዜውን የጠበቀ ነው ብለን አናምንም” የሚል የተቃውሞ አስተያየት ሰጥተዋል። ህወሓት ከአሸባሪነት ሊሰረዝ የሚገባው፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባባር ሪፖርት ለፓርላማው ከቀረበ በኋላ መሆን እንዳለበት አቶ አለሳ አክለዋል።
ሶስት ሰዓታት በወሰደው በዚህ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ልዩ ጉባኤ”፤ የፓርላማ አባላት ግማሽ ያህሉን ጊዜ ወስደው ጥያቄ እና አስተያየታቸውን አቅርበዋል። እድል ካገኙ 14 የፓርላማ አባላት መካከል ሰባቱ፤ የህወሓትን ከሽብርተኝነት የመሰረዝ ውሳኔ ሃሳብን ተቃውመው አስተያየት ሰጥተዋል። የሃሳቡ ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ሲያነሱት የነበረው ጉዳይ፤ ህወሓትን ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ ከመሰረዝ በፊት “የሰላም ስምምነቱ በህወሓት በኩል ሙሉ በሙሉ መተግበር አለበት” የሚለው ነው።
የውሳኔ ሃሳቡን ደግፈው የተናገሩ የፓርላማ አባላት በበኩላቸው፤ የሽብርተኝነት ፍረጃው መነሳት “የሰላም ስምምነቱን ዘላቂ ያደርገዋል” የሚል መከራከሪያ ሲያቀረቡ ተደምጠዋል። ይህ የፓርላማ አባላቱ ሃሳብ፤ ለጥያቄዎች ምላሽ ሲስጡ በነበሩት በፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስም ተስተጋብቷል። የሽብርተኝነት ስያሜ ማንሳት፤ “ስምምነቱ ላይ ያሉት ነገሮች እንዳለ ተተግብረው አብቅተው፣ ማሳረጊያው ላይ የሚሆን ነገር ሳይሆን፤ ሌሎች ግዴታዎች እየተተገበሩ፣ አብሮ በሂደት ውስጥ መተግበር ያለበት፤ መፈጸም ያለበት ነገር ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል ሲል የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡
