ሠራተኞች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ተከትሎ፤ ለተለያዩ ጉዳቶች እየተዳረጉ ነው ሲል የኢትጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
‘የዜጎች አካላዊ፣ አእምሯዊና ማህበራዊ ደህንነት የተጠበቀ ሲሆን፤ የሥራ ደህንነታቸው ተጠብቋል’ ማለት እንደሚቻል የሚናገሩት በኮንፌዴሬሽኑ የሞያ ደህንነት እና ጤንነት አጠባበቅ ባለሞያ አቶ ደምሰው እንዳፈራው፤ ይህ ካልሆነ ግን በሠራተኞች ላይ የተለያዩ ጉዳቶች የሚከሰቱበት ሁኔታ ስለመኖሩ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የሙቀት መጠን እንዲጨምር በማስቻሉ በተለይም ሥራቸው በመስክ ላይ የሆነ እንደ ኮንስትራክሽን፣ የእርሻ ሥራ እና በግንባታ እንዲሁም በትንስፖርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች በለውጡ ምክንያት ለሚከሰት ጉዳት ያላቸው ተጋላጭነት እንደሚጨምር ተናግረዋል፡፡
“ይህም አንድ ሰው ሊኖረው የሚችለው አማካኝ ሙቀት እንዲዛባ እና የሠራተኞች ሙቀት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አልያም ከሰውነት ውስጥ ከፍተኛ ፈሳሽ እንዲወጣ ከማሳቸሉም በተጨማሪ፤ የጡንቻ መዛል እና መሰል ሁኔታዎች እንዲያጋጥሙ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
የዝናብ መጠን መቀነስ እና መጨመር በተመሳሳይ ሠራተኞችን ለአደጋ አጋላጭ እንደሆነም፤ የሞያ ደህንነት እና ጤንነት አጠባበቅ ባለሞያው ገልጸዋል፡፡
የዓለም አቀፍ የሞያ ደህንነት ቀን በየዓመቱ እንደሚከበር የሚናገሩት ባለሞያው፤ ባለፈው ዓመት ቀኑ ሲከበር መሪ ቃል ተደርጎ የተወሰደው “በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሰራተኞች ላይ የሚከሰት የጤና እክል ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰዋል።
በከፍተኛ ሞያ የሥራ መስክ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ለጤና ችግር አጋለጭ በመሆናቸው ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አጽንኦት የሰጡት አቶ ደምሰው፤ በቀጥታ ለጸሃይና ለሙቀት ተጋላጭ ለሆኑ ሠራተኞች እንዲሁም ለአሰሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
“የሠራተኞችን ጤና እና ደህንነትን ለማስጠበቅ በቀጥታ ለሙቀት አጋላጭ በሆኑት የሥራ መስኮች ላይ ለሙቀቱ መከላከያ እና መቋቋሚያ የሚሆኑ ግብዓቶችን ማዘጋጀት ይገባል” ሰሉም አሳስበዋል፡፡
