ሪቮካፕ ፋውንዴሽን ለትምህርት ሚኒስቴር ከ100 ሺህ በላይ መጻሕፍትን ለገሠ

Date:

ከዐሥር ዓመት በፊት በአሜሪካን ሀገር የተቋቋመው ሪቮካፕ ፋውንዴሽን ኩባንያ በዛሬው ዕለት ከ100 ሺህ የሚልቁ መጻሕፍትን ለትምህርት ሚኒስቴር አስረክቧል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌን ጨምሮ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች እና የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ የሪቮካፕ ፋውንዴሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ የኾኑት አቶ ሀብቴ መስፍን በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ኩባንያቸው ከዚህ ቀደምም በመሰል ማኅበራዊ ኃላፊነትን በሚፈልጉ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለአብሮት ቤተ መጻሕፍት፣ ደብረ ብርሃን አካባቢ ለሚገኝ አካዳሚ እና ሌሎችም በመቶ ሺዎች የሚቀጠር የትምህርት መማርያና አጋዥ መጻሕፍትን ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው በአሜሪካን ሀገር ባሉ የቡና መሸጫ ሱቆቹ ቡናን ከማስመጣት ጀምሮ በመቁላት እና በችርቻሮ በመሸጥ ለተጠቃሚዎች በማድረስ ላይ የሚገኝ መኾኑን የገለጹት መሥራቹ ‹‹ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ቡና አብቃይ የኾኑ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦችን በትምህርት፣ በጤና እና በንግድ ዘርፍ በማገዝ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ በመድረኩ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በኢትዮጵያ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ይገኛሉ ያሉ ሲኾን አብዛኞቹ የሚማሩበት ት/ቤት ግን ከደረጃ በታች በመኾኑ እንዲህ ያሉ የትምህርት መርጃ የሚኾኑ መጻሕፍትን እና የትምህርት መሣሪያዎችን እገዛ በማድረግ የበቃ እና ተወዳዳሪ ተማሪ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ማገዛ ይገባል ብለዋል፡፡

ሪቮካፕ ፋውንዴሽን ይኽን ዐይነቱን ኃላፊነት በመውሰድ የተጫወተው ሚና እና ያደረገው የመጻሕፍት እርዳታም እጅግ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ሪቮካፕ ፋውንዴሽ የለገሳቸው 5 ኮንቴይነር በቁጥ ከ100 ሺህ በላይ የሚኾኑ የትምህርት መጻሕፍትም ለወሎ፣ ለጅማ፣ ለአፋር፣ ለባሕርዳር እና ለጎንደር ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ኮንቴይነር መጽሐፍ የርክክብ ሥነ ሥርዓት የተካሔደ ሲኾን፣ የሦስቱም ክልል የትምህርት ቢሮ ተወካዮችም መጻሕፍቱን ተረክበዋል፡፡

ሪቮካፕ ፋውንዴሽንን እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ከተመሠረተበት 2013 ጀምሮ፣ ቡና አብቃይ ማኅበረሰቦችን በትምህርት፣ በጤና እና በንግዱ ዘርፍ ከመርዳት ጀምሮ፣ የሪቮካፕ ፋውንዴሽን ባለአክሲዮኖች በወሰኑት መሠረት በእያንዳንዱ የችርቻሮ ሱቆቻችን ከምንሸጠው አንድ ሲኒ ቡና 0.10 ዶላር፣ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ከረጢት ቡና 1.00 ዶላር በመለገስ የሚታወቅ ሲኾን፣ ባለፉት ዓመታት ደግሞ ወደ አምስት መቶ ሺህ የሚጠጉ ትምህርታዊ መጻሕፍትን ወደ ኢትዮጵያ ልኳል፡፡ ብዙዎቹ መጻሕፍትም ተደራሽ የተደረጉት ለቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማህበራት እና ለሌሎች በገጠራማ አካበቢዎች ለሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሲኾን፣ ይኽ የኾነውም ገጠራማ በኾኑ አካባቢዎች ለሚኖሩ ትምህርት ቤቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ-መጻሕፍትን በመክፈት በአማካኝ ከ1500-5000 የሚኾኑ መጻሕፍትን በመለገስ ነው። የመጻሕፍቱ ክፍፍልም ትምህርት ቤቱ ባለው የክፍል ደረጃ እና በትምህርት ቤቱ በሚማሩ ተማሪዎች ብዛት ላይ የተመሠረተ መኾኑን ፋውንዴሽኑ ይፋ ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ሪቮካፕ ኮፊ ኮርፖሬሽን መቀመጫውን በዩኤስ አሜሪካ ካንሳስ ግዛት ያደረገ እና በሕግ ተመዝግቦ ለትርፍ የተቋቋመ ኩባንያ ነው።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የክሪፕቶ ሥራ ፈጣሪው የ15 ዓመት እስር ተፈረደበት

የቀድሞው የክሪፕቶከረንሲ ሥራ ፈጣሪ ተሰውሯል ከተባለ 40 ቢሊየን ዶላር...

5ኛው የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ተካሄደ

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት በየዓመቱ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ...

የንግድ ሚኒስቴር 13 ምርቶችን በመነሻ ሀገር የጥራት ማረጋገጫ (PVoC) እንዲያገኙ ወሰነ

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት፣ በሀገር...

ገዳ ባንክ ከ444 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለፀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን በ2018 ዓ.ም...