Home ምን እንጠይቅልዎት? “ራስን የሚክድ ፍቅር ከእናቴ አውቄያለሁ” ጋዜጠኛ ዓለምነህ ዋሴ

“ራስን የሚክድ ፍቅር ከእናቴ አውቄያለሁ” ጋዜጠኛ ዓለምነህ ዋሴ

“ራስን የሚክድ ፍቅር ከእናቴ አውቄያለሁ” ጋዜጠኛ ዓለምነህ ዋሴ

ዓለምነህ ለእናቱ ያለው ፍቅር የተለየ ነው ይባላል፤ በሬዲዮ ቃለምልልሱም የቴዲ አፍሮን “ባይገርምሽ ገና እወድሻለሁ” ዘፈን እንደመረጠ አልዘነጋውም፡፡ እባክህ ዓለምነህ እስኪ ስለዚህ ትንሽ አጫውተን፡፡

ትዕግስት ወልደማርያም (ከአደይ አበባ)

ዓለምነህ፡- ለእናቴ ያለኝ ፍቅር የተለየ ነው፡፡ ለሁሉም ሰው እናት እናት ናት፡፡ አባቴ ወታደር በመሆኑ ብዙ ጊዜ ሕይወቱን ያሳለፈው ጦር ሜዳ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ አባቴን የማውቀው ለፈቃድ ሦስት አራት ጊዜ በመጣበት ወቅት ነበር፤ ለእኔ ብርቅ እንደሆነ ነው የኖረው፤ የ17 ዓመት ልጅ ከሆንኩ በኋላ ጡረታ ወጥቶ ነው የማውቀው፡፡ ስለዚህ ከእናቴ ጋር ያለኝ ቁርኝት በጣም ጥብቅ ነበር፡፡ እናቴ ተጫዋች፣ ተረተኛ ናት፤ ለምንም እና ለማንኛውም ነገር ተረት አላት፡፡ በተናደደች፣ በተቆጣች ወይም በተደሰተች ወቅት በቁጣዋ እና በሳቋ መካከል የምታወጣቸው ተረቶች በጣም ይደንቁኛል፡፡ …የማርያም ጽዋ ማህበር ላይ ሁሌ እኔን ነው ይዛኝ የምትሄደው፤ እኔና እናቴ በፍጹም በመልክ ስለማንመሳሰል ጓደኞቿ እርሷን ሠላም ካሉ በኋላ እኔን “የማነው ይሄ ባሪያ ደግሞ” ይሏታል፡፡ ይሄን ያህል አንመሳሰልም፡፡ …እናቴ ግን “ከልጆቼ መካከል እኔን የምትመስለው አንተ ነህ” ትላለች፡፡ ቤት ውስጥም ከእህቶቼም፣ ከወንድሞቼም ሁሌም የመረጥኩትን የምበላ እኔ ነኝ፡፡ የእኔ ፍላጐት ነው የሚጠበቀው፡፡ …ከእኔ በላይ ሦስት ወንድሞች፣ ከእኔ በታች አንድ እሕት አለችኝ፡፡

…እና ለእናቴ ያለኝ ፍቅር በጣም ልዩ ነው፡፡… እርሷ በሕይወት ባለመኖሯ ግን ከባድ ጉዳት ደርሶብኛል፤ …ላገግም አልቻልኩም፡፡ ለምሳሌ፡- ሞተች፣ ተቀበረች ብለህ የምትወጣው ነገር አለ፡፡ …እና እርሱን ስላላወጣሁ ነው መሰል ብዙ ነገር ተደራረበብኝ፡፡ አሁን ከላይ ለብሼ የምሄደው ነገር አለ እንጂ ውስጤ ብዙ ችግር አለበት፤ አንድ በርሷ ጉዳይ ላይ መጥቀስ የምፈልገው ነገር፡- የስምንት ወይም የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሆኜ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን እስከ ጊዮርጊስ ወይም እስከ መርካቶ ሊሆን ይችላል ተልኬ ሳይሆን እዚያ ደርሼ ተመልሼ እመጣለሁ ብዬ በማሰብ እንዲሁ ለመዝናናት በአውቶብስ እሄዳለሁ፤ ያኔ ብርቅ ስለነበር፡፡ …እየሄድኩ እያለ ልክ ስድስት ኪሎ የካቲት 12 ጋር አውቶቡሷ ስትቆም ሰዎች ከየካቲት 12 ሆስፒታል አስከሬን ሪሬሳ ሳጥን እያወጡ ይላቀሳሉ፡፡ ያንን ነገር ሳይ አሁን በሕይወቴ የማልረሳው፣ ልቆጣጠረው የማልችለው የብርድ ስሜት ውስጤ ገባ፡፡ …ያኔ በጭንቅላቴ የመጣው እናቴ ትሞታለች የሚለው ነው፡፡ ያኔ እኔ የማውቀው ትልቅ ሰው ይሞታል፤ ከዚያ እንደ ዕድሜው ልጅ ይከተላል የሚለውን ነው፡፡ …ያንን በማሰብ አንድ ቀን እርሷ ልትሞት እንደምትችል አሰብኩ፤ በጣም የሚገርመው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁልቀን የምቀናው ብዙ ወገን፣ ብዙ ዘመድ፣ 40 ወንድም፣ 10 እህት፣ አክስት፣ አጎት ባለው ሳይሆን እናቱን፣ አባቱን፣ እሕቱን ወንድሙን የማያውቅ… በጉዲፈቻ ያደገ ሰው ያስቀናኝ ነበር፡፡ ይህ ሰው በዚህ ዓለም ላይ ያለበት ትልቁ አደጋ በራሱ ላይ የሚመጣው ብቻ ነው፡፡ እንደዚህ የሚወዳቸውን ሰዎች በቁሙ ሆኖ የማጣት አደጋ የለበትም ብዬ ስለማስብ በእንደዚህ ዓይነት ሰው በጣም እቀና ነበር፡፡ እስካሁን ያጠፋሁትን እግዚአብሔር ይቅር ይበለኝ ነው የምለው፡፡ እናትነት ፀጋ ነው፤ እናቴ ያንን ፀጋ ሰጥታኛለች፤ እርሱም ፍቅር ነው፡፡ ራስን የሚክድ ፍቅር ከእናቴ አውቄያለሁ፤ የሚያሳዝነው ራስን የሚክድ ፍቅር ከእናቴ ተቀብዬ እኔ በአንፃሩ ራስ ወዳድ መሆኔ ነው፡፡ እርሷ ራሷን ትታ ስትወደኝ እኔ ያንን ፍቅር ያለምንም ማመዛዘን በመውሰድ የእርሱ ተቃራኒ ራስ ወዳድ ሆኜ ስላደግሁ በዚህ ተቃርኖ ውስጥ ነው የምኖረው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ትልቁ ደስታዬ ልጆቼ ናቸው፤ …ለእኔ የነፈገውን፣ ለእናቴ የነፈገውን ለዘመዶቼ የነፈገውን እድሜ ለልጆቼ ካደረገልኝ በዚህ እጽናናለሁ፡፡

ለስፖርት ከፍተኛ ፍቅር እንዳለህ ከምታቀርባቸው ፕሮግራሞች መረዳት እችላለሁ፤ ለመሆኑ ከማራዶናና ከፔሌ ማንን ታስበልጣለህ? ሁለቱን የዓለማችን ከዋክብት እንዴት ትገልፃቸዋለህ?

ገረመው ባላኬር (ከልደታ)

ዓለምነህ፡- ልዩ ፍቅር ያለኝ ለማራዶና ነው፤ ምክንያቱም ማራዶናን ነው የማውቀው፤ ማራዶና ነው መሬት ላይ ያንከባለለኝ፡፡ በተለይ እንግሊዝ ላይ ሁለተዋኛዋን ጎል ሲያገባ፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ሁለተኛዋን ጐል በሪፕሌይ ነው ያየኋት፤ ለምን? ማራዶና ተጫዋቾቹን እያጠፈ፣ ዚግዛግ እያደረገ፣ እየሸነሸነ ሲሄድ፣ (እኔ የእንግሊዝኛውን ቃል እወደዋለሁ፤ ባንቡዝሊንግ ማለት ነው) እያደረገ ሲሄድ ልቤ አልቻለም፡፡ በነገራችን ላይ ሥጋችን የማይችለው ደስታ አለ፤…እና የተወሰነ ቦታ ላይ፣ ጎሉን ማየት ባለብኝ ሰዓት መሬት ላይ ተንፈራፈርኩ፡፡ ስለዚህ ጎሉን ከገባ በኋላ ነው ያየሁት፡፡ በመሆኑም ልዩ ፍቅር ያለኝ ለማራዶና ነው፤ የማልወድለት ነገር የለኝም፤ ምክንያቱም ስለማውቀው፡፡

ማራዶናንና ፔሌን እንዴት ትገልፃቸዋለህ ለተባለው ፔሌን ስታንዳርድ ልታደርገው ትችላለህ፡፡ አንድ የኳስ ተጫዋች ቁመቱ ዘለግ ያለ፣ ፈርጣማ፣ በግራውም በቀኙም መጫወት የሚችል፣ ግንባሩን እንደመምቻ የሚጠቀም፣ ሲሮጥ ፈጣን… መሆን አለበት፤ እና በዚህ ረገድ ፔሌ ስታንዳርድ ነው፡፡ ማራዶና ግን አንቲቴሲስ ነው፡፡

ፔሌን ስታንዳርድ ካደረግነው ማራዶና አንድ ኳስ ተጫዋች መሆን የሌለበት ነው የሚመስለው፤ ማራዶና በሁለት እግሩ አይጫወትም፤ በቀኝ እግሩ ይቆምበታል እንጂ ኳስ መንካት ይችላል ብዬ አላምንም፤ ቁመቱ አጭር ነው፤ ከቁመቱ ማጠር ጋር ብዙ ነገሮች አሉ፤ ስለዚህ ከፔሌ አንፃር ማራዶናን ስታየው እግር ኳስ መልማይ ብትሆን ልትዘለው የምትችለው ሰው ነው፤ ነገር ግን ማራዶናን ከፔሌ የሚያስበልጥብኝ አንዱ ነገር በአንድ እግሩ ብቻ እየተጫወተ ቴስታ አለመምታቱ ነው፤ ራሱ ፔሌ፤ “ማራዶናኮ በሕይወቱ ቴስታ የመታውና ያገባው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ እርሱም እንግሊዝ ላይ ነው፤ እርሱንም ያገባው በእጁ ነው” ብሏል፡፡ ስለዚህ እኔ ደግሞ ለፔሌ የምሰጠው ምላሽ “ለዚህ እኮ ነው ማራዶና ካንተ ይበልጣል የምለው” የሚለውን ነው፡፡ ማራዶና ኳሷን ሳም ነው የሚያደርጋት፤ ማራዶናና ኳስ ፍቅረኛሞች ናቸው፤ ይፈልጋታል-ትፈልገዋለች፤ ይጠብቃታል-ትመጣለታለች፤ ይነካታል-ትሄድለታለች፤ ፔሌ ለኳስ እንጀራ አባት ነው፡፡ አምባገነን ባል ነው፡፡ ያዳፋታል፤ ያሳድዳታል፤ ተከትሎ ይደርስባታል፤ ይረግማታል፤ ያንቀረቅባታል፡፡ እኔ በአጋጣሚ ፍቅርን ስለምወድ ማራዶናን በዚህ የተለየ አደርገዋለሁ፡፡

በአንድ ወቅት ኑሮዬን እስራኤል ነው የማደርገው ብለህ ነበር፤ አሁን ያለኸው ግን እዚህ ነው፤ ፈላሻ ነህ ወይ?

ሁሴን ሃሰን (ከጎንደር – በስልክ)

ዓለምነህ፡- ኑሮዬ እስራኤልም ኢትዮጵያም ነው የሚሆነው፡፡ እስራኤል እግዚአብሔር የሰጠኝ ቤቴ ነው፤ ኢትዮጵያ የተወለድኩባት ሃገሬ ናት፡፡ ስለዚህ ተንፈራጥጬ እኖራለሁ፡፡ ይሄ መብቴ ነው፤ ፈላሻ ነህ ወይ ለሚለው በእናቴ በኩል ቤተ-እስራኤል ነኝ፡፡ ወደዚያም ሃገር ያስኬደኝ እርሱ ነው፡፡ ፈላሻ ሆንህ፤ ቤተ እስራኤል ተባልህ ሁሉም ነገር በኢትዮጵያ ውበት ውስጥ የሚገለጽ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ስለዚህ እኔ ኢትዮጵያም እስራኤልም እኖራለሁ፤ “እስራኤል ኑሮዬን አደርጋለሁ፤ ኢትዮጵያ አልኖርም” የሚል ንግግር አልተናገርሁም፡፡

በጋዜጠኝነት ሕይወት በጣም የተደሰትህበትና ያዘንህበት ወቅት ይኖራል?

መቶ አለቃ አዳሙ ወልዱ (ከመሃንዲስ)

ዓለምነህ፡- በጋዜጠኝነት ሕይወቴ በአብዛኛው ተደስቼ ነው የኖርሁት፤ በጣም የተደሰትሁበት አጋጣሚ ሳዳም ሁሴን ጠረጴዛ የመቱ ጊዜ ነው፤ ለዐረብ ሀገር መንግሥታት “ይህቺ ጽዮናዊት ምናምንቴ (Non-Entity) አንድ የዐረብ ሃገር ብታጠቃ እንግዲህ ፈጣሪ አይለመነኝ ግማሽ በግማሽ አነዳታለሁ” ብለው የተናገሩ ጊዜ የሆነ ነገር ሊፈጠር ነው ማለት ነው ብያለሁ፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ዛቻና ፉከራ ከኋላው ትንሽ መሠረት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ያቺ ሃገር ልትሰጥ የምትችለውን አጸፌታ አውቃለሁ፤ ሁልጊዜ መካከለኛው ምስራቅ አንዳች ሁነት የሚፈጠርበት ቦታ ነውና እንደ ጋዜጠኛ ሆነህ ስታስበው አዲስ ነገር፣ አዲስ ወሬ የሚመጣበት ነው፡፡ እና ያቺ ወሬ Excite (ኤክሳይት) ስላደረገችኝ ከዚያች ጊዜ ጀምሮ ሳዳም ሁሴን ጦርነት እስኪገቡ ድረስ እንድከታተል ምክንያት ሆናኛለች፡፡

የሌኒን ሐውልት ሲፈርስ ደግሞ የተደሰትሁበት ግራ የተጋባሁበትም ነው፡፡ ሕዝብ በሌኒን ላይ ይህን ያህል ጥላቻ እያለው በሌኒናዊ ሥርዓት ውስጥ ያን ያህል ዝም ብሎ መቆየቱ ሳስበው በአጠቃላይ ለሰው ልጅ እንዳዝን አድርጎኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰው እንደ ስሜቱ፣ እንዳስደሰተው ይኖራል ማለት አይደለም የሚል ግንዛቤ ነው ያመጣብኝ፡፡ …የሌኒን ሐውልት ሲፈርስ በጫማ ይደበድቡት ነበር፤ አንድ ሰው በእግራቸው መሬት ላይ ተንበርክከው እጃቸውን ወደ ፈጣሪ ዘርግተው በጥልቅ ስሜት የተናገሩትን አስታውሳለሁ፤ “ጀግናው ኃይለ ሥላሴ ባሠሩት የአፍሪካ አዳራሽ ፊት ለፊት፤ የርሳቸው ሐውልት ሊቆም በሚገባ ቦታ ላይ፣ ኢትዮጵያ ሀገራችንን ወደ ጉስቁልናና ወደ ረሃብ የለወጠ፣ በጤፍ ፋንታ በቆሎና ማሽላ እንድንበላ ያደረገ ኮቴ መናና እዚህ ተገትሮ” እያሉ በሳቅና በእንባ መሃል ሆነው ነበር የሚናገሩት፡፡ ስለዚህ ሁልቀን የምናገረው ነገር አለ፡፡ ሰዎች ያሳዝኑኛል፤…እና ያንን ነው ያረጋገጠልኝ፤…ሰው ይሄን ያህል የሚጠላው ከሆነ፣ ይሄንን የሚያህል ሐውልት በሃገሩ ላይ እንዴት ቆሞ ሊኖር ቻለ? ብዬ ተሰምቶኛል፤ ሲፈርስም በማየቴ ደስ ብሎኛል፤ ጋዜጠኝነት ይህንንም ሁሉ ያገኘሁበት ነው፡፡

ዕንቁ፡- ብዙ ጊዜ ዘገባዎችህን በምን ዙሪያ ላይ ማቅረብ ደስ ይልሃል?

ሙሉጎጃም በየነ (ከዶሎመና)

ዓለምነህ፡- እኔ ሌክቸር ነገር አልወድም፡፡ በዚህ ዓለም ትልቁ ነገር የሰውን ስሜትና ሰውን ያከበረ፣ ስሜትን የተከተለ ማንኛውም የፍቅር፣ የጦርነት፣ የሠላም ሁነት ደስታ ይሰጠኛል፡፡ ቴሌቪዥን ስሰማ ወይም ራሴ ስጽፍ ብዙ ጊዜ እንባዬን የሚያመጡት ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ደግነት፣ ኢትዮጵያውያን ተራቡ ብሎ የመነሳትን ትልቅነት የመሳሰሉ ነገሮችን ሳላለቅስ ማየት አልችልም፡፡ በጣም ነው የሚመስጠኝ፡፡ በ30 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት ላይ ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚሞቱ ኢትዮጵያውያን የሚቆረቆሩና ገንዘባቸውን፣ ልብሳቸውን የሚሰጡ ሰዎች መኖራቸውን ስሰማ በጣም ነው ስሜት የሚሰጠኝ፡፡ በአጠቃላይ ከሰው ሕይወት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ፍቅርና ስሜት ያላቸው ነገሮች ያስደስቱኛል፡፡ …እኔ መዘገብ የምፈልገው እንደዚህ በሰው ዙሪያ፣ ከሰው ሕይወት፣ ከደምና ከአጥንት ጋር የተያያዙ ነገሮችን ነው፡፡

በቴሌቪዥን መታየት አትፈልግም ይባላል፤ ለምንድን ነው?

ኃይሌ ሙሉነህ (በኢ-ሜይል)

ዓለምነህ፡- እውነቱን ለመናገር ጠያቂዬ ልክ ናቸው፤ በቴሌቪዥን መታየት አልፈልግም፡፡ ብዙዎቹ ከሚያስቡት ጋር የተያያዘ ግን አይደለም፡፡ በቴሌቪዥንም ብቻ ሳይሆን በግሌም ብዙ ሰው ባለበት ቦታ ይጨንቀኛል፡፡ አንድ ነገር እንዳደርግ ስጠበቅ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ ምንም ነገር ከራሴ መንጭቶ በራሴ መንገድ የምሠራው ካልሆነ ያ ነገር ፍላጎቴ አይደለም፡፡ አሁን በፋና ኤፍኤም 98.1፣ ዕሁድ ከ3-4 “አንድ ሰዓት እንደማመጥ” ፕሮግራም ስሰራ በጣም ነው የምደክመው፡፡ ማንም ይሁን አንድ ሰው እንኳ ዓለምነህን ላዳምጥ ብሎ ለተቀመጠ ሰው መስማት ያለበትን ነገር መስጠት አለብኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡ በሬዲዮ ሥራ ላይ እንደተረዳሁት የተደማጭነትህ መጠንም ሆነ ከርሱ ጋር አብረህ የምታገኘው ጥቅም በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ቴሌቪዥን ላይ ብሠራ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ እንዲያውም በዚህ ወቅት ስፖርት ትኩረት ስቧል፤ ኢቴቪ ቢፈቅድልኝ ቴሌቪዥን ላይ መሥራት የምፈልገው ከስክሪን ጀርባ ነው፡፡ እኔ መታየት የለብኝም፡፡ ዓለምነህን ካላየን ሞተን እንገኛለን የሚሉ ካሉ አንድ ደቂቃ ብቅ ልል እችላለሁ (ረጅም ሳቅ)፡፡ ነገር ግን ከስክሪን ጀርባ ሆኜ በተለይ በእግር ኳስ እና በአትሌቲክስ ዙሪያ አንዳንድ ትንታኔዎችን ብሠራ በጣም ሕዝቡን አስደስተዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ከሥዕል ጋር ተዳምሮ እኔም ፍላጎቴን አረካለሁ፡፡ ይህን ጥያቄ ስላነሱም አድማጮቼን በጣም ነው የማመሰግነው፡፡ አንድ ቀን ይህን ጥያቄ ለኢቴቪ አቀርባለሁ፡፡

ዕንቁ፡- በቅርቡ ዳጉ ላይ በተገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብ አዝኗል፤ እንደ ጋዜጠኝነትህ አትሌቲክሱ የነበረበትን ትልቅ ደረጃና አሁን ያለበትን ሁኔታ እንዴት ትገልፀዋለህ?

ዓለምነህ፡- በእኔ እምነት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ መውደቅ ወይም መውረድ የአትሌቶቹ ጥፋት ብቻ አይደለም፤ በዚህ ጉዳይ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የሚወቀስበት ነው፡፡ አትሌቲክሱ ላይ ቀነስን ማለት ሁሉንም ነገር ለመጠቀም ያለንን መንፈስ እያጣን ነው፡፡ በዚህ አባባሌ ስህተት ልሆን እችላለሁ፡፡ አትሌቲክስ ተራ ስፖርት አይደለም፤ አትሌቲክሱ የኢትዮጵያ መንፈስ ነው፤ ኢትዮጵያን እንወዳለን፤ እናደንቃለን፣ ትልቅ ናት የምንል ከሆነ ያ የትልቅነቷ መገለጫ ነው፤ ስለዚህ አትሌቲክሱ ሊቀንስ አይችልም፤ ግን በግልፅ ለመናገር በታወቁ ገናና አትሌቶቻችን አማካይነት ነው እንጂ አሁን ባለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሰዎች ሥር ሆኖ አትሌቲክሳችን ተራመደ ብዬ አላስብም፡፡ አሁንም እነዚህ አትሌቶች በራሳቸው ነው እያቆዩን ያሉት፡፡ …እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እየሠራው ያለው ነገር የለም፡፡ ሁላችንም እንደ ጋዜጠኛ ብዙ ጽፈናል፤ ስለዚህ እዚህ አገር ብዕር አቅም ከሌለው፣ የሕዝብ አስተያየት አቅም ከሌለው ሌላ እኔ የማውቀው አቅም የለም፤ ስለዚህ ከለንደን ኦሎምፒክ በኋላ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሰዎች ይውረዱና ለተሻለ ሰው ይስጡ፡፡ እስከ ለንደን ግን እነዚህ ሰዎች ቢያንስ ያሉትን አስተባብረው፣ የግል ጥቅማቸውን ገትተው፣ አትሌቲክሱን አንድ እርከን ከፍ እንዲያደርጉት እጠብቃለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ኬንያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት ኢትዮጵያውያን እንድናፍር ያደርገናል፡፡…አትሌቲክስ መንፈሳችን ነው ብዬ አስባለሁ፤ እሱን ካጣን ከዚሁ ጋር አብሮ በኢትዮጵያ የመኩራታችን፣ በኢትዮጵያ ተስፋ የማድረጋችን ነገር ሁሉ በተለያየ መልኩ እየቀነሰ፣ ትርጉም እያጣ ሊመጣ ይችላል፡፡ ይሄ አጠቃላይ የሃገሪቱን ንባብ ነው የሚያመለክተው፡፡ ውድቀቱ ከታች እስከ ላይ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ መሆን የለበትም፤ ለንደን ላይ በምንም ተአምር ኢትዮጵያ በኬንያ መበለጥ የለባትም፤ በ5,000፣ በ10,000፣ በማራቶን፡፡

ትውልድና እድገትህ የት ነው? ከባለቤትህ ጋር እንዴት ተዋወቃችሁ? ስለ ልጆችህም ብትነግረኝ…

ትዝታ ንጉሱ (ከቤልኤር -አ.አ)

ዓለምነህ፡- ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ኬላ የሚባለው አካባቢ ነው፡፡ አንደኛ ደረጃን ሕዝባዊ ሠራዊት፣ ሁለተኛ ደረጃን ሚያዚያ 23፣ ከዚያ እንጦጦ አጠቃላይ ት/ቤት ነው የተማርኩት፡፡ በመካከሉ የሙያ ትምህርት መርጬ ኮከበ ጽባሕም ቆይቻለሁ፡፡ እንጦጦ ወደቴክኒክ ት/ቤት ሲያድግ ተመልሼ የአካውንቲንግ ሙያ ተምሬያለሁ፡፡

እኔና ባለቤቴ የተገናኘነው ዘጠነኛ ክፍል ሳለን ነው፡፡ እኔ ከ1-10 ደረጃ የወጡ ተማሪዎች ያሉበት ክፍል በመሆኔ የሙያ ትምህርት መርጬ ወደ ኮከበ ጽባህ ስሄድ እርሷ እዚያው እንጦጦ አጠቃላይ ት/ቤት ቀረች፤ ያኔ ነው የማውቃት፤ መልኳ ቆንጆ ነው፤ ልጅ ነበረች፤ በተለይ ዐይኗ በጣም ያምር ነበር፤ አሁንም ቆንጆ ናት፡፡

በሬዲዮ የሰማሁትን የእነ ወጋየሁን ትረካ ክፍል ውስጥ በቃሌ አቀርባለሁ፤ ከተለያየ ሰው የሰማሁትን የራሴ ታሪክ አድርጌ አወራለሁ፡፡ ከድሮ ጀምሮ መመሰጥ እችል ነበር፡፡ ሰዎቹን ሁሉ እየመሰጥኩ ወንዶቹም ሴቶቹም ሲከቡኝ እኔ በነርሱ መካከል የማየው እርሷን ነው፡፡ ለመማረክ የምፈልገው እርሷን ነዋ! እና ስትፈዝዝ አያት ነበር፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ደፍሬ እንደወንድና እንደ ሴት “ብንገናኝስ” ብዬ ያልኳት እርሷን ነበር፡፡ “እሺ” አለችኝ፤ በነጋታው ተቀጣጠርን፤ የለችም፤ አኮረፍሁ፡፡ አኩርፌ ወደ ኮከበ ጽባሕ ሄድኩ፤ ግን እውነቱን ለመናገር ባገኛት ምን እንደማደርግ የማውቀው ነገር የለም፤ ምክንያቱም ሞዴል የለኝም፡፡

ከረዥም ዓመት በኋላ እኔን የምትወደኝ ልጅ ስላለች እሷን ልጅ ተዋወቃት በሚል ልታስተዋውቀኝ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መጣች፡፡ ያቺ የመጣችው ልጅ በትክክል ስለ እኔ ብዙ ነገር ታውቃለች፡፡ ከተመሰጡት ልጆች መካከል ስለነበረችም እርሷን መንከባከብ ነበረብኝ፡፡ ደምሴ ዳምጤ በአንድ ወቅት “ሚስትህን እንዴት አገኘሃት?” ሲባል “…ምን ሠፌዱም እንቅቡም ተላላኪ ነው” ያለው ነገር አለ፡፡ እና እኔ ያየሁት ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ለእኔ መታየትን ነበር፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ መጨረሻ ላይ ከእርሷ ጋር ለመገናኘት ችያለሁ፡፡ በእውነት ለመናገር ሕይወት ውጣ ውረድ ይኖረዋል፡፡ የሰዎች ባህርይ አለ፤ የእኔም ባህርይ አለ፤ የእኔ ባህርይ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ሰው የተመኛትን የማግኘት ዕድሉ ውስን ነው፡፡ እኔ ግን የተመኘኋትን ነው ያገኘኋት፡፡

ልጆቼ አራት ናቸው፤ በዚህ ዓመት አንተነህ ዓለምነህ 12 ዓመት ይሆነዋል፤ ሁለተኛዋ ኢየሩሳሌም (ማርያናዊት)፣ ሦስተኛው ናትናኤል (እኔ ቶማስ ነው የምለው) ሲሆን አራተኛዋ ሳሮን (እኔ ናኒና ነው የምላት) ይባላሉ፡፡

ሰዎች በእግዚአብሔር መኖር ያምናሉ፤ እኔ ግን የእግዚብሔርን መኖር የማውቅ ሰው ነኝ፡፡ ማመን ከመንፈሳዊነት ጋር ይገናኛል፡፡ ለእኔ ግን አንተ እኔን እንደምታየኝ እግዚአብሔርን በፍጥረቶቹ መኖር አውቀዋለሁ፡፡ እግዚአብሔርን በአየሩ፣ በባህሩ፣ በወንዙ፣ በሁሉ ነገር አውቀዋለሁ፤ ስለዚህ ብዙ ነገር ደርሶብኛል ብዬ ላስብ እችላለሁ፡፡ በሕይወቴ የሰጠኝና እኔን የሚያሳሳኝ ግን እነዚህ ልጆቼ ናቸው፡፡ ለእኔ ሕይወቴ ናቸው፡፡ እርሱ አግዚአብሔር አባታቸው እንዲሆን ነው የምመኘው፡፡ እኔ ባለሁበትም በሌለሁበትም ሁሌ እርሱ እንዲኖር እፈልጋለሁ፡፡ ልጆቼ በጣም ውዶቼ ናቸው፤ እኔ ትምህርታቸው ላይ ጥሩ እንዲሆኑ ነው የምፈልገው እንጂ በጣም አጥኑ አልልም፡፡ ባለቤቴ ግን አንደኛ ካልወጡ ትለኛለች፡፡ እኔ ለጨዋታ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ጥሩ እውቀት ያላቸው ተማሪዎች ይሁኑ ነው የምለው፤ ትምህርት አንድ ነገር ነው፡፡ ሁሉንም ነገር አይደለም፡፡ ሰው እንዲሆኑልኝ ነው የምፈልገው፡፡ እውቀትን፣ ፍቅርን፣ ትካዜን፣ ደስታን፣ ምንይሉኛልን፣ ድፍረትን፣ ማፈርን፣ መቅበጥን፣ መቆጠብንም ሁሉንም ነገር የሚያውቁና ከምንም ነገር በላይ መጀመሪያ ሰው እንዲሆኑልኝ ነው የምፈልገው፡፡ ሰው መሆን ከቻሉ ትምህርቱን በራሳቸው ጥረት ያገኙታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ትምህርት ብቻ ይሆንና ሰው መሆን ያቅታል፡፡ ይሄ ልጆቼ ላይ እንዲደርስ ስለማልፈልግ ከትምህርት ባላነሰ መልኩ ሰው ይሆኑ ዘንድ ነው የምፈልገው፡፡ ሰው መሆን ማለት እግዚአብሔርን ማወቅ ነው፤ ሰውን ማክበር፣ ሰውን መፍራት፣ ሰውን መውደድ ሁሉንም ነገር መሆን ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔ ሠው ለመሆን በጣም የቸገረኝ ሠው ስለሆንኩ ለልጆቼ የምመኝላቸው ሰው እንዲሆኑ ነው፡፡

ዓለምነህ እና ፍልስፍና በጣም ይዋደዳሉ ይባላል፤ ፍልስፍና ለአንተ ምንድነው?

ገነት ፍፁም (ከአ.አ.ዩ – በኢ-ሜይል)

ዓለምነህ፡- እኔን ከፍልስፍና ጋር ሳይሆን ከኮንቴምፕቴሽን (ከመቦዘዝ) ጋር ልታያይዘኝ ትትላለህ፡፡ ፍልስፍና ውስጥ እውቀትም አለ፤ የአስተሳሰብ መስመርም አለ፡፡ እኔ በልጅነቴ ብዙውን ሰዓት በጨዋታ አሳልፋለሁ፡፡ ትምህርት አልወድም ነበር፡፡ ጓደኞቼ በሙሉ ወደ ት/ቤት በሚሄዱበት ጊዜ እኔ የማሳልፈው እየተጫወትሁ ነው፡፡ ድሮ ጀምሮ ሜዳ፣ ሣር እወዳለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያለሁበት ቦታ ላይ ድንግጥ እስክል ድረስ በሆነ ነገር ራሴን ተመስጬ አገኘዋለሁ፤ የተመሰጥሁበትን ነገር ግን አላውቅም፤ ስለዚህ ፍልስፍና ሳይሆን መቦዘዝ (መመሰጥ) እወዳለሁ፡፡

ኢትዮጵያዊ ባትሆን ምን ሆነህ መፈጠር ትመርጣለህ?

ጌታያውቃል አዲሱ (ከባሕርዳር – በስልክ)

ዓለምነህ፡- ኢትዮጵያዊ ባልሆን ያው አሜሪካዊ ሆኜ ብፈጠር ነው የምመርጠው፡፡ አሜሪካ የሰውን ልጅ እስከነምጡቅነቱ እስከነስሕተቱ ትቀበላለች፤ በጣም የሠለጠነ ደረጃ የደረሰች፣ የሰውን ልጅ እንደ ስሜቱና እንደ አስተሳሰቡ አቻችሎ ለማኖር የሚያስችል የተሻለ ሲስተም የዘረጋች ሃገር ስለሆነች ምሳሌ ነች ብዬ አስባለሁ፡፡

እስራኤል ሃገር በሚሠራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለፋሲን ዳን ኮሙኒኬሽን ለመስራት ሄደህ ነበር፤ ምን ሠራህ?

ጥሩነህ ወንድሙ (ከአዲስ አበባ)

ዓለምነህ፡- ፋሲል ዳን በእስራኤል ሃገር “YES” በሚባለው የሳተላይት ቴሌቪዥን ላይ ካለው በዕብራይስጥ “አሩጽ” ከተባለ ቻናል ጋር በመጣመር በዚያ ለሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች ፕሮግራም ያስተላልፋል፡፡ እዚያ ሆኜ የሠራሁለት ፕሮግራም እርሱ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራቸው ዶክመንተሪ ፊልሞች ነበሩ፡፡ እነዚያን በእንግሊዝኛ የተሠሩ ዶክመንተሪዎች ወደ አማርኛ ተርጉሜ በአማርኛ እየተተረኩ በጣቢያው ይተላለፉ ነበር፡፡ በወቅቱም እዚያ በነበርኩበት ጊዜ ትኩረቴን እንዳሳርፍበት አድርጎኛል፤ ትንሽ ሳንቲም እንዳገኝም ምክንያት ሆኖኛል፡፡

በኢቴቪ የማስታወቂያ ክፍል ብዙ ጊዜ ትማረራለህ ይባላል፤ ምክንያቱ ምንድን ነው? በቅርቡ የወጣው አዲሱ የዋጋ ጭማሪስ የሚመጣልህን ማስታወቂያ ለማስተናገድ ተመችቶሃል?

ሳሚ ሕሩይ (በስልክ)

ዓለምነህ፡- እኔ በኢቴቪ የማስታወቂያ አሠራር በአጠቃላይ በጣም ማዘን ብቻ ሳይሆን መቼም ይሻሻላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ያለ ቴሌቪዥን ማስታወቂያ የራሴን የሬዲዮ ፕሮግራም ሠርቼ መኖር ኢኮኖሚዬን ሊፈታተነው ይችላል፡፡ ግን የልጆቼን የት/ቤት ክፍያ እስከከፈለልኝ ድረስ ይበቃኛል፡፡ ሌላ ነገር አልፈልግም፡፡ አዲስ አበባ ቁምጣ ሱሪ አድርጌ በእግሬ እየሄድኩ የተማርኩባት፣ የተወለድኩባት ከተማ ናትና ብዙ ነገር አይደንቀኝም፡፡ የኢቴቪ የማስታወቂያ ክፍል አስተሳሰብ ራሱ አይገባኝም፡፡ እርሱን አስቤ ስነሳ ብዙ ቦታ ላይ ፍርሃት ያድርብኛል፡፡ በጣም ይፋ የሆነ አድልዎ ነው የሚፈፅሙት፡፡ ማስታወቂያ አስገብቼ አይተላለፍልኝም፤ 30 እና 40 ጊዜ ካልታረመ አይሄድልኝም፡፡ ለ20፣ ለ30 ማስታወቂያ ከፍዬ ግማሹ እንኳን አይለቀቅልኝልም፡፡ በምፈልገው ሰዓትና ቦታ ማግኘት አልችልም፡፡ እኔ የማውቃቸው በስልክ እየደወሉ ቦታ ሲያስይዙ እኔ ግን በአካል ሰጥቼ እንኳን አይተላለፍልኝም፡፡ ስለዚህ ውጤታማ የሆነውን የማስታወቂያ ሥራ እንድጠላው ሆኛለሁ፡፡ ከመጥላቴ የተነሳም ድህነቱን መርጫለሁ፡፡

በእውነቱ በማስታወቂያ ሥራ ላይ ቀናነት የለም፤ እኔ የማስበው የማውቀው ሰው እኔን ያግዘኛል… እኔም ሌላ ቦታ አግዛለሁ ብዬ ነው፡፡ ነገር ግን እንደዚህ አይደለም እየሆነ ያለው፡፡

የማስታወቂያ ፈቃድ አለኝ፤ በኢቴቪ ማስታወቂያ አልሠራም፤ እንዴት እንደሚሠራ ጠፍቶኛል፡፡ ለምን ቢባል እነርሱ የፈለጓቸውን ሰዎች ብቻ አሳደጉበት፤ …የኔ ቅሬታ ሥር ነቀል ነው፡፡ ቢቻል በኢቴቪ የስፖርት ፕሮግራም አግኝቼ ልሠራ ብችል ደስ ይለኛል፤ ማስታወቂያው ግን ጤናዬን ያሳጣኛል፡፡

ኢትዮጵያን የሚያሞግስ መጽሐፍ አወጣለሁ ብለህ ነበር፤ ከምን ደረሰ?

ነፃነት አስረስ (ከፍካት ወጣቶች)

ዓለምነህ፡- ትክክለኛ ጥያቄ ነው፤ መጽሐፉ ሊወጣ ያልቻለው ብዙ ጊዜ ገንዘብ መሥራት ስለሚያቅተኝ ከስፖንሰሮች ጋር የመሥራት ችግር ስላለብኝ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ሁሉ ነገር በሐሳብ ተጀምሮ ያልቃል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ተስፋ አድርጌ የሆነ ቦታ ላይ እንደዚህ አደርገዋለሁ የሚለው ነገር በእርግጥ እየተሳካልኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ ማለት የምችለው ከዚሁ ላይ እየቀነጣጠብሁ በሬዲዮ የማቀርብበት ሁኔታ አለ፡፡ በራሴ መንገድ አቅም ፈጥሬ ማድረግ እስክችል ድረስ ያንን ማለት አልነበረብኝም፡፡ ስለዚህ እንደ ስህተትና ድክመት እወስደዋለሁ፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ቢፈቅድ ወደፊት ጥሩ ጋዜጠኛ እንድሆን ምን ትመክረኛለህ?

መስፍን መገርሳ (ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ)

ዓለምነህ፡- መጀመሪያ ሌላውን አድማጭ ሁን፤ የሰው ፍቅር ይኑርህ፡፡ ሰው ማለት ታሪክ ነው፡፡ ሰውን ካዳመጥኸውና ነፍሱን ካገኘኸው፣ ሁሌ ለሰው አክብሮትና ፍቅር ካለህ፣ ጋዜጠኛ መሆንህን የሚከለክልህ ማንም የለም፡፡ እናም ጥሩ ጋዜጠኛ ለመሆን ራስህ ሰው መሆን አለብህ፡፡ ቀና፣ ብሩህ የሆንህ፣ ዓይንና ጆሮህ ጉጉ የሆነ ሰው መሆን አለብህ፡፡ ከዚህ በተረፈ እውቀት ሊኖርህ ይገባል፡፡ በጋዜጠኝነት ውስጥ ግንዛቤህ ሰፋ ያለ እንዲሆን ብታነብ ጥሩ ነው፡፡ የቋንቋ ችሎታ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ መጻፍና ማቅረብ ይጠበቅብሃል፡፡ እነዚህን ሁሉ ጥረት አድርገህ የምታገኛቸው ናቸው፡፡ አስቀድመህ ሰው ሁን፤ ሰባኪ አትሁን፤ በምትጽፈው ነገር ለመመሰጥ የምትጽፍ ከሆንህ አንተ ጋዜጠኛ አይደለህም፡፡ ሳትመሰጥ መመሰጥ አትችልም፡፡ ሳትነካ መንካት አትችልም፡፡ ከልብህ አትለይ፡፡

ለጋዜጠኝነት ሕይወትህ በር የከፈቱልህ ሃምሳ አለቃ መርሻ ናቸው ይባላል፤ ምን ያህል እውነት ነው? ሃምሳ አለቃ መርሻ ማናቸው?

ኤልያስ ክብረቃል (ከስድስት ኪሎ)

ዓለምነህ፡- ሃምሳ አለቃ መርሻ ውድነህ እና እናቴ አረጋሽ አስናቀው ናቸው እኔን ጋዜጠኛ ያደረጉኝ፡፡ እናቴ ተረት አላት፤ ቋንቋ አላት፤ ጨዋታ በጣም ታውቃለች፤ ኃዘንተኛም ናት፡፡ ሃምሳ አለቃ መርሻ ፊደል ካስትሮን ነው የሚመስለው፡፡ የአባቴ ጓደኛ ነው፡፡ አንድ ግድግድ ተጋርተን ነው የምንኖረው፡፡ እና የቤታችን ግድግዳ ማሳመሪያው ጋዜጣ ነው፡፡ …ወታደርና ዓላማው፣ ሰንደቅ ዓላማችን የሚሉ ጋዜጦች አሉ፡፡ እኔ ደግሞ አዳርሼ ጨርሻቸዋለሁ፡፡ ይሄን ያደረግኩት ጋዜጠኛ ለመሆን አይደለም፡፡ …ዝም ብዬ የማደርገው ነው፡፡ ታዲያ ግድግዳችን ላይ ያለውን ጋዜጣ ሳነብ ጋሽ መርሻ ቤቱ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ በራሴ ድምፅ በምዝናናበት ወቅት ቤቱ ሆኖ እየሰማ እንዴት ማንበብ እንዳለብኝና ማወቅ ያለብኝን ነገሮች እየመከረ የሚመራኝና የሚያዳምጠኝ እርሱ ነበር፡፡ የት/ቤት ውጤቴን እየተከታተለ ያበረታታኝ ነበር፡፡ 12ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ በ1979 ዓ.ም በሬዲዮ የዜና ፋይል ጋዜጠኛ በሚቀጠርበት ወቅት የኢትዮጵያ ሬዲዮ የዜና ክፍል ኃላፊ የነበረችው ቤት ይዞኝ ሄዶ አስተዋወቀኝ፡፡ በዚያ መነሻነት ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተቀጠርኩ፡፡ እና በሂደት ሃምሳ አለቃ መርሻ የጎረቤቱን የኛን ቤት ነው የገነባው ማለት እችላለሁ፡፡ ያሠለጠነኝም ምሳሌ የሆነኝም ሰው ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ስንፍናህን ትገልፃለህ፤ ከምን የመጣ ነው? በሥራዎችህ ላይ በጣም ውሱን ነህ፤ ብዙ አትሠራም፤ ለምንድነው? መሥራት የሚገባህን ያህልስ ሠርቻለሁ ትላለህ?

አቤል ሠይፈ (ከ22 ማዞሪያ)

ዓለምነህ፡- አዎ! ሠነፍ ነኝ ብያለሁ፤…በጣም ሰነፍ ነኝ፡፡ ነገር ግን የሥራ መስመሮች አሉኝ፡፡ በምፈልጋቸው ነገሮች ላይ 24 ሰዓት መሥራት እችላለሁ፡፡ ከነዚያ ውጪ ሲሆን ደግሞ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ስኬት ለማምጣት ብዬ መንቀሳቀስ አልችልም፡፡ በዚህ በጣም ሰነፍ ነኝ፡፡ ይህን የማካክሰው እኔ በምፈልጋቸውና በምወዳቸው ቦታዎች ላይ በመሥራት ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሰው ስትሆን ደግሞ ገንዘቡ አይመጣም፡፡ መሥዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ …እናም እነዚያን መሥዋዕትነቶች ለመክፈል ፈራ ተባ የማለትና ዝግጁ ያለመሆኔ እስካሁን ድረስ ብዙ ነገር የመሥራት ዕድሌን ቀንሶታል፡፡ ከሰው ጋር ተግባብቶ የመሥራት እና የማሠራት አቅሜ አነስተኛ ነው፡፡ ይህንን እንደ ጉድለት አየዋለሁ፡፡ ሆኖም ስንፈቴን ለማስተካከልና ምርጫዬ ባልሁት ሙያዬ ላይ የሚያስፈልገውን መሥዋዕትነት በመክፈል ለመሥራት ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ሌሎች ስላደረጉት ብቻ የማላደርጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የቄሳርን ለቄሳር ይላል፡፡ መሥራት የሚገባኝን ያህል በፍፁም አልሠራሁም፤ አንዳንድ ጊዜ ስንፍናዬን ሳስብ ስሞት እንኳ ሊለቀስልኝ አይገባም እላለሁ፡፡

ዓይን አፋርነትህ ከምን የመጣ ነው?

ፌቨን ግርማ (ከኢ.ሬ.ቴ.ድ)

ዓለምነህ፡- በእውነት የዚህን ምክንያት አላውቅም፤ ግን አሁን የመጣ አይደለም፤ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው፡፡

ግብጽንና ካሜሩንን በተመለከተ የዘገብከው ዘገባ ላይ ሶንግ በተባለው ተጫዋች ተናደህበት ነበር፤ ምክንያቱ ምንድነው?

ምስግና ገብረሚካኤል (ከፈረንሳይ ለጋሲዮን)

ዓለምነህ፡- የካሜሩኑ ሪጎበርት ሶንግ በእድሜ አንጋፋ ነበር፤… እና እኔ ተናድጄበት ሳይሆን ግብፅና ካሜሩን ሲጫወቱ የእድሜ ልዩነት የፈጠረውን ሁኔታ በማየት ነው የተናደድሁት፡፡ ሶንግ ኳሷን ለበረኛ ለመስጠት የወሰደበት ጊዜና የግብፁ ዚዳን የወሰደው ፍጥነት የተሞላበት ግምትና ውሳኔ ከእግር ኳስ ልምድ ባለፈ የዚዳንን የእድሜ ልጅነት ያሳያል፡፡ ልጅነትንና ሽምግልናን ነው በዚያ ጨዋታ ላይ ለማየት የቻልኩት፡፡ ያኔ ምን እንዳልኩ አላስታውስም፡፡

ጋዜጠኝነትን መቼ ነው የጀመርኸው? የሬዲዮ ፋናስ ቋሚ ሠራተኛ ነህ?

ሄኖክ ወልዳጋብር (ከአዳማ)

ዓለምነህ፡- ጥር 1 ቀን 1979 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ስቱዲዮ በዜና ፋይል በፍሪላንሰርነት በ230 ብር ተቀጠርኩ፡፡ የፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ቋሚ ሠራተኛ አይደለሁም፡፡

የማስታወቂያ ድርጅት ከፍተሃል፤ መጠሪያው ማን ይሠኛል? እስካሁን ምን ያህል ሥራ ሠርተሃል? ከዚህ በኋላስ ምን ሥራዎችን እንጠብቅ?

መልካሙ ስንታየሁ (ከለቡ)

ዓለምነህ፡- የድርጅቴ ሥም “ዓለምነህ ማስታወቂያ” ይባላል፡፡ በዚህ ድርጅት በርካታ ማስታወቂያዎችን ሠርቻለሁ፤ ቴሌቪዥን የተከታተለ ሰው ያውቀዋል፡፡ በአንድ ወቅት የአንተ ድምፅ ብቻ በዝቷል፣ አይተላለፍ እስከመባል የደረሰበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ከእኔ እንዲጠብቅ የምፈልገው የዕሁድ “አንድ ሰዓት እንደማመጥ” ፕሮግራሜን “ሁለት ሰዓት እንደማመጥ” ማድረግ ነው፡፡ ይህም የሬዲዮ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ውሳኔ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሠዓት ቢጨመርልኝ ሌሎች ጋዜጠኞችንም ጨምሬ የማስፋፋት እቅድ አለኝ፡፡ የቤተሰብ ኃላፊ በመሆኔ እጅ ያጥረኛል፡፡ መጽሐፎቼም የሁልጊዜ እቅዶቼ ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግን …ዕንቁ መጽሔትን ለሚያነቡ የሥራ ኃላፊዎች፣ የድርጅት መሪዎች፣ የቢዝነስ ተቋማት ይህንን ሥራዬን አግዙልኝ የሚል መልዕክቴን ነው የማስተላልፈው፡፡ ልመና ሳይሆን በሙያ እንተጋገዝ ነው የምለው፡፡ ሃምሣ አለቃ መርሻ አግዞኛል፤ ለምኜው አይደለም፤ ዛሬ ዓለምነህን ለሚወዱ ሰዎች ዓለምነህን በዚህ ሰዓትና ወቅት እንዲያገኙት ትልቅ ምክንያት የሆነው ሃምሳ አለቃ መርሻ ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንችን እንተጋገዝ፣ ጥሩ የሆነ ነገር እንሥራ፤ ሐሳብ ሸጠው ለሚያድሩ መሠረት ሁኗቸው፤ እንሁናቸው ነው የምለው፡፡

ለምሳሌ፡- አቶ ሰይድ መሐመድ የአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት በባህርዩ በጣም ጥሩ ሰው ነው፡፡ ከሰዎች ጋር በቀላሉ ነው የሚግባባው፡፡ በብዙ ነገር እንዳየሁት ደግ ሰው ነው፡፡ ስኬታማ ሰውም ነው፤…ለአቶ ሰይድ ከመርካቶ አራተኛ ጣቢያ ጀምሮ ማስታወቂያ የምሠራለት እኔ ነበርኩ፡፡ ከዚያ ተነስቶ ጠቅላላ በአዲስ አበባ፣ በኢትዮጵያና በተለያዩ ቦታዎችም ቅርንጫፎችን ከፍቶ አሁን የምናውቀው “አምባሳደር ልብስ ስፌት” እስኪሆን ድረስ እኔ ነበርኩ ማስታወቂያ የምሠራለት፡፡ አሁን የአምባሳደርን ማስታወቂያ የሚሠራው እኔ ሳልሆን ሠራዊት ፍቅሬ ነው፡፡ አምባሳደር ማስታወቂያውን ሠራዊት እንዲሠራለት ማድረጉ ያለ አንዳች ማስመሰል ትክክለኛው የቢዝነስ ውሳኔ ነው፡፡ ሠራዊት በተለያዩ ዘርፎች ዝነኛ ሰው ነው፡፡ እናም የዚህን ሰው ፐርሰናሊቲ በመጠቀም የአምባሳደርን ጥራት ለማሳየት በመቻሉ አምባሳደርም ገኗል ብዬ ነው የማምነው፡፡ በአጠቃላይ አምባሳደር ሃገር እያለበሰ ነው ያለው፤ እነዚህ ሁሉ ተጨምረው ለአቶ ሰይድ አድናቆት እንዲኖረን አድርገዋል፡፡ ነገር ግን በአቶ ሰይድ ላይ አንድ ቅሬታ አለኝ፤ ከታች ከአራተኛ ጣቢያ ጀምሮ አብረን ተጉዘናል፤ አሁን ከእኔ ለምን ተለየ ሳይሆን እኔ በሬዲዮ ፕሮግራም የራሴን ገቢ ፈጥሬ እየሠራሁ ነው፤ ገና አራተኛ ጣቢያ ላይ ነው ያለሁት፤…እና መለስ ብሎ “ጥሩ ነው፣ በርታ” እያለ አምባሳደር እኔን ስፖንሠር ሊያደርገኝ አይገባም ወይ? …ፕሮግራሜን እንዳስፋፋ “በርታ” ሊለኝ ይገባል ነው የምለው፡፡ እኔን መጥቶ በመጎብኘት ምሳሌ መፍጠር አለበት፡፡ ሁላችንም ርቀን በሄድን ቁጥር መለስ ብለን የማየትና “ለእኛ ምን ተደርጎልናል? እኛስ ምን ማድረግ አለብን?” የሚል ጥያቄ ካላነሳን ገንዘብ ብቻውን ሃገር አያሳድግም፡፡ እንዲህ አይነት መተሳሰብ እንዲኖር እፈልጋለሁ፤ ትስስራችን ከግል ትውውቃችን ባለፈ ኢትዮጵያዊነታችን ነው፡፡

ዕንቁ፡- ለስንብት የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ…

ዓለምነህ፡- በአጠቃላይ በእኔ ላይ ፍላጎት ላሳያችሁ በሙሉ እግዚአብሔር ክብር፣ ጤና፣ ሠላም ይስጥልኝ፤ እንደኔ ላለ በአንድ ወቅት ለታወቀ ሰው ከእውነተኛው ሞት በበለጠ የሚያስፈራው መረሳት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የዝነኞች ሞት መረሳት ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አስታውሶ ዓለምነህ እናቱን ይወዳል ብሎ መጠየቅ ለእኔ ወደ ሕዝብ ተመልሼ እንድቀርብ፣ ትኩረት እንዳገኝ የሚያደርገኝና የመረሳት ስጋቴን የሚቀንስልኝ በመሆኑ የዕንቁንም መድረክ እንዳገኝ ስለረዳችሁኝ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

በተረፈ ለኢትዮጵያ ትልልቅ ሰዎች የማስተላልፈው መልዕክት ብዙ ሥራ ለመሥራት እየሞከራችሁ ነው፡፡ ትልልቅ ጥረቶችን እያደረጋችሁ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ነገር ነው እና በሥራችን ውስጥ እግዚአብሔርን እናስገባ እላለሁ፡፡ እግዚአብሔር የተነጋገርነውን በልቦናችን ያሳድርልን፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡

አጫጭር ጥያቄዎች

1. መጠጥ ትወዳለህ?

             እንደሁኔታው፤

2. ባለቤትህን ገጨት አድርገሃት ታውቃለህ?

             አንድ ቀን፤

3. የአንድ ቀን ሥልጣን ቢኖርህ?

             እግዚአብሔር ልቦናችንን ቀና እንዲያደርገው፣ ትልቅ ቁም ነገር ሊሠራ የሚችለው በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በመሸናነፍና በመቻቻል መሆኑን አንድ ቀን ሙሉ እንድናስብበትና እንድንጸልይበት አደርጋለሁ፡፡

4. ዕሁድን ከማን ጋር ታሳልፋለህ?

             ከቤተሰብ ጋር በቤቴ፤

5. ከእግር ኳስ የማን ደጋፊ ነህ?

             ለጊዜው ባይተዋር ነኝ፤

6. ከዓለማችን የምታደንቀው አንድ ሰው?

             ማንዴላ፤

7. ከሙያህ የመውጣት ሃሳብ አለህ?

             መቼም እስከመቼም፤ በፍፁም፤

8. ከድምፃውያን ማንን ታደንቃለህ?

             ዶን ዊሊያምስ፤

9. ተመልሶ በተወለደ የምትለው?

             ሙሴ፤

10. ከፊልምና ከቲያትር የቱን ትመርጣለህ? ፊልም፤