አሁን ላይ በትግራይ ክልል የተጋረጠው ረሀብ የክልሉ ፖለቲከኞች ሕዝቡን የሚፈልጉት ለፖለቲካ ግባቸው እንጂ ለሌላ እንዳልኾነ ያረጋገጠ ኹነት ኾኗል፡፡ የትግራይ ፖለቲከኞች ሁልጊዜ ‹‹ሕዛባችን›› እያሉ ቢያላዝኑም መሬት ያለው ሀቅ ግን ከዚያ የተለየ ነው፡፡ 27 ዓመታትን በትግራይ ሕዝብ ሥም ምለው ተገዝተው እና ሀገር ዘርፈው ለትግራይ ሕዝብ ግን እንደጦስ ዶሮ የሚረግፍበትን አሰቃቂውን ጦርነት አዋለዱለት፡፡ በምላሹም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ እንቁ ልጆቹን በጥይት አረር አስጨፈጨፉት፤ በሺ የሚቆጠሩ ወገኖቹን ለአካል ጉዳተኝነት ዳረጉት፡፡ ያም ኾኖ ግን ዛሬም ‹‹ሕዝባችን›› እያሉ ይለምኑበታል ግን አያበሉትም፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን ይታገሉበታል ግን አይታደጉትም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም ምንም እንኳን የክልሉ ሕዝብ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ቢገኝም ለዳግም ጦርነት እየቀሰቀሱት ይገኛሉ፡፡ አሁንም ጥቂት የክልሉ ልሂቃኖች የእንግሊዝና የፈረንሳይን የጦርነት ታሪክ እንደሞዴል መቁጠር ጀምረዋል፡፡
በታሪክ እንደሚታወቀው እነዚህ ሁለት ሀገሮች በዓለም ላይ ረጅሙን ጦርነት ያካሄዱ ሀገሮች ናቸው፡፡ ከ1337 እስከ 1453 ዓ.ም ለ116 ዓመታት የዘለቀ የግዛት ይገባኛል ፍልሚያን አካሂደዋል፡፡ የግዛት ጥያቄ ያለባት ቦታ የፈረንሳይ ኖርማንዲ ግዛት ነች። ለብዙ ዓመታት እንግሊዞች ኖርማንዲን ጨምሮ ብዙ የፈረንሳይ ግዛቶችን ተቆጣጥረው ያስተዳድሩ ነበር። ፈረንሳይ ደግሞ አቅሟ እየጎለበተ ሲሄድ ቀደምት ግዛቶቿን መሰብሰብ ተያያዘች፡፡ በዚህ ሳቢያም በዚህች ግዛት ላይ ረጅም ዓመታትን የዘለቀ ውጊያ ልታካሂድ ቻለች፡፡ በመጨረሻም ፈረንሳይ ከሦስት ትውልድ የእንግሊዝ ወረራ በኋላ ግዛቷን መልሳ አገኘች። የትግራይ ፖለቲከኞችም ይህ ቅዠት በልባቸው አለ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የዘነጉት ነገር ግን ፈረንሳይ “ኖርማንዲ” የተሰኘችው ግዛት ሀቃዊ ባለቤት መኾኗን ነው፡፡ አንድም ፈረንሳይና እንግሊዝ ጎረቤታሞች ሀገር እንጅ አዋሳኝ ክልልሎች አለመኾናቸውን ነው፡፡
የኛይቱ ትግራይና አማራ ጎረቤታም ክልል እንጅ አገሮች አይደሉም፡፡ የትግራይ ፖለቲከኞች ግን የፈረንሳይ የዓመታት የጦርነት ጉዞና ድል በቅናት በልቷቸው ዛሬም ስለሕዝባቸው ነባራዊ ሁኔታ ሳይኾን በጉልበት ወስደው በጉልበት ስለተቀሙት የወልቃይትና የራያ ግዛት መጠቅለል ያስባሉ፡፡ ለዚህ ግዛት ሲሉ የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ቢከስም እንኳ ግድ የሚሰጣቸው አይመስልም፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ ባለፈው ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የትግራይን ሕዝብ አስበልተው ወደተሸነፉበት ጦርነት ዳግሜ የጦርነት ግስጋሴ መሥመር ሲዘረጉ መታየታቸው ነው፡፡
የኾኖ ኾኖ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በክልሉ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስና የተጋረጠውን የረሀብ አደጋ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ የእርዳታ እጆቹን ካልዘረጋ በቀጣይ ሊፈጠር የሚችለው ችግር እጅግ ከባድ ሊኾን እንደሚችል አሳስቧል፡፡ ጉባኤው በመግለጫው ለሁለት ዓመታት የቆየው የትጥቅ ግጭት ፕሪቶሪያ በተደረገው የሰላም ስምምነት ቢቆምም ግጭቱ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ከፍተኛ ከመኾኑ የተነሳ እስካሁን ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ አለመቻሉን ጠቁሞ ጥርነቱ ያስከተለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ለመርመር ከሚመለከታቸው አካላት ፈቃድና ተባባሪነትን ባለማግኘቱና በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረው የኢሰመጉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በመዘጋቱ ምክንያት ሳይሳካ እንደቀረ አትቷል፡፡ በመኾኑም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) ሐምሌ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሠረት በእዚህ ግጭት ምክንያት በትግራይ ክልል ከአንድ ሚሊዮን (1,000,000) በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁሞ በተመሳሳይ የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ሐምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሠረት የትጥቅ ግጭቱ በክልሉ ያስከተለውን ቀውስ ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪ የምግብ እርዳታ ላይ የተደገፈ መኾኑን በመግለጽ በክልሉ ኮሌራና መሰል በሽታዎች መከሰታቸውን ገልጿል፡፡
ቀደም ሲል ጦርነቱ ባስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ በትግራይ ክልል በዋናነት ሰብዓዊ ድጋፍ ያቀርቡ የነበሩት የአሜሪካ ኤጀንሲ ለዓለም አቀፍ ልማት (USAID) እና የዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም (WFP) በእርዳታ ቁሳቁስ ላይ ስርቆት ተፈጽሟል በሚል እርዳታቸውን ያቋረጡ ሲኾን በዚህም ምክንያት በክልሉ ከፍተኛ የኾነ የምግብና የመድሀኒት እጥረት መከሰቱን ከሳምንት በፊት የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም ከአንድ ሺህ (1000) በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪ በቅርቡ የትግራይ አረጋውያን ማኅበር እንዳስታወቀው በትግራይ ክልል የጡረታ ደመወዝ ባለመከፈሉ እንዲሁም ባለው የምግብ እጦት በረሃብና በበሽታ ከ75 ሺሕ በላይ አረጋውያን የሞት አፋፍ ላይ ናቸው። የማኅበሩ ሊቀመንበር አርአያ ገሰሰ ማኅበሩ ጡረተኛ የኾኑና ጡረታ የማይከፈላቸው በጠቅላላው 75 ሺሕ አረጋውያንን ያቀፈ መኾኑን ጠቅሰው፤ የሚበሉትና የሚጠጡት ነገር ባለመኖሩ እጅግ ዘግናኝ ሁኔታ ውስጥ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ኢሰመጉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UNOCHA) መረጃን መሠረት አድርጎ እንደዘገበው በትግራይ ክልል ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ወደ ሆስፒታል እየገቡ ያሉ ሕጻናት ቁጥር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በ196% ጨምሯል፡፡ በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ችግር፣ ርሀብ፣ ከፍተኛ የምግብና የመድሀኒት እጥረት ምክንያት በዋናነት አጥቢ እናቶች እና ጨቅላ ሕጻናት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መኾኑን ጠቅሷል፡፡ በክልሉ ለተከሰተው ርሀብ፣ ከፍተኛ የኾነ የምግብና የመድሀኒት እጥረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲሁም የፌደራል መንግሥት ኃላፊነት እንዳለባቸው የጠቆመው መግለጫው ሁለቱም አካላት ይህ ሰብዓዊ ቀውስ ከእዚህ የከፋ ጉዳትን ሳያደርስ ለመቆጣጠር የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ኢሰመጉ በተጨማሪም የምግብ እጥረቱ ካስከተለው ርሀብ ጎን ለጎን በክልሉ የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት፣ የሕክምና ቁሳቁስ እጥረትና የሕክምና አቅርቦት እና ፍላጎት ተመጣጣኝ አለመኾን ከፍተኛ ችግር መኾኑን አንስቶ በዋናነት የስኳር፣ የቲቢ፣ የኤች አይ ቪ እና ሌሎችም መሰል በቋሚነት መድሐኒት አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው ሕመሞች ያለው የመድሐኒት አቅርቦት እጅግ አናሳ በመኾኑ አስቸኳይ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አመላክቷል፡፡
ኢሰመጉ አክሎም በክልሉ ለኢሰባዊ ቀውስ ተጋላጭ ለኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ልዩና አፋጣኝ ትኩረት በመስጠት ነፍስ አድን የኾኑ የምግብና መድሐኒት እርዳታዎችን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌደራል መንግሥትና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት እንዲያቀርቡ፣ ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰብዓዊ እርዳታዎች ምግብን እና መድሀኒትን ጨምሮ በተገቢው መንገድ ለተጎጀዎች እና እርዳታው ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንዲደርስ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች ላይ የሚደረጉ ስርቆቶችን እና ሕገ-ወጥ ንግዶችን እንዲቆጣጠር እና በእዚህም የፌደራል መንግሥቱ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ፣ በክልሉ ዋነኛ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያቀርቡት የአሜሪካ ኤጀንሲ ለዓለም አቀፍ ልማት (USAID) እና የዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም (WFP) ድጋፋቸውን እንዲያቆሙ ምክንያት የኾነውን የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች ስርቆት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲሁም የፌደራል መንግሥት ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን በሕግ እንዲጠይቁ እና በሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች ላይ ተገቢውን በቂ ቁጥጥር እንዲያደርጉ፣ በትግራይ ክልል ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ከፍተኛ ርሀብ የፌደራል መንግስት እንዲሁም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተገቢውን በቂ ትኩረት በመስጠት ካስከተለው ጉዳት የከፋ ጉዳትን እንዳያደርስ እና ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ ተቀናጅተው በመሥራት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ በማለት በአጽንዖት አሳስቧል፡፡
በአጠቃላይ አሁን ላይ ሀገሪቱ እንደሀገር ከፍተኛ ቀውስ ላይ የምትገኝ ቢኾንም በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ግን እጅግ የሚያሳስብ መኾኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቂያ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ወደ25 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች እርዳታ ፈላጊዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ተረጂዎች መካከል ደግሞ ከፍ ሲል እንደታየው የዕለት ደራሽ ምግብ እንኳን የሌላቸው አብዛኛውን ቁጥር የሚሸፍኑት ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ናቸው፡፡ በመኾኑም ጉዳዩ የሚመለከተው ማንኛውም አካል ችግሩ ከዚህ በላይ ከመግፋቱ በፊት አስፈላጊውን ርብርብ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ከፍ ሲል እንደተገለጸው ምንም እንኳ ሰሚ ባይኾንም የክልሉ መንግሥትም ይሁን የፌደራል መንግሥት እየተባባሰ የመጣውን ረሀብ ለማስቆም ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
