የኩላሊት ታማሚዎች ለአንድ ቀን ዲያሊስስ እስከ 5 ሺህ ብር እንደሚያስፈልጋቸው እና ይህም በኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ የኑሮ ሁኔታ ጋር ወጪውን መቋቋም እንዳልቻሉ ተገልጿል:: በርካቶች በአቅም ማጣት ምክንያት ህይወታቸውን እያጡ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም የዲያሊስስ ህክምና በበቂ ሁኔታ የሚሰጡ ተቋማት ቁጥር አነስተኛ መሆን ሌላኛው ችግር እንደሆነባቸው የኢትዮጵያ የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ሰለሞን አሰፋ ተናግረዋል።
የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ለኩላሊት ህመምተኞች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ህይወታቸውን ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ይሁን እና አገልግሎቱ ከሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ አንፃር ለበርካታ ህሙማን ለመድረስ እጅግ አዳጋች ሆኖብናል ብለዋል።
ድርጅቱ ህሙማኑ የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንዲያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቢሰጥም ኩላሊት የሚለግሳቸው ሰው ባለመኖሩ አብዛኛው ህመምተኛ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ማንኛውም ሰው በህይወት እያለ ኩላሊቱን ለመለገስ ቃል እንዲገባ እና ህይወቱ ሲያልፍ ኩላሊቱን ለህሙማን ለመለገስ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ በአስቸኳይ እንዲወጣ እና ወደ ተግባር እንዲገባ ለመንግስት የቀረበው ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡
በዚህም በርካቶችን ከሞት መታደግ የሚቻል መሆኑ ተነግሯል።በዚህም ጉዳዩ የሚመለከተው አካልም ይህንን ህግ በአስቸኳይ ወደ ተግባር ሥራ ላይ እንዲውል ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
እንዲሁም በተስፋ እየጠበቀ ያለውን ህመምተኛዉ ንቅለ ተከላ እስኪያደርግ ድረስ ለዲያሊሲስ ወጪ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ እያቀረቡ እንደሆነ ዶክተር ሰለሞን አሰፋ ተናግረዋል።
ለብስራት ሬዲዮ
