ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጾታ እኩልነት ጥያቄዎች ገፍተው ወደ አደባባይ እየመጡ ነው። በተለይም በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ጉዳዩ ሰፊ ትኩረትና ሽፋን አግኝቷል። ነገር ግን ብዙ ሴቶች ‘ፌሚኒስት’ መባልን አይፈልጉትም። በአሜሪካና በእንግሊዝ በተደረጉ ተከታታይ የዳሰሳ ጥናቶች እንኳ ብንመለከት ከአምስት ሴቶች አንዷ ብቻ ‘ፌሚኒስት’ መባልን ትሻለች። ያም ሆኖ በጾታ እኩልነት የሚያምኑ ሴቶች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነው።
ሴቶችን አንድ ያደረጉ ንቅናቄዎች
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ጾታዊ ንቅናቄዎች ዓለምን ከዳር እስከ ዳር አነቃንቀዋል። ዶናልድ ትራምፕ በ2017 ሥልጣን ሲይዙ ሚሊዮኖች አደባባይ ወጥተው ተቃውመዋቸዋል። የሰልፉ ዓላማ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረውን የሴቶች መብትን መከላከል ነበር።
በሆሊውድ የሃርቬይ ዌንስን ቅሌት 80 ሴቶች ድምጻቸውን ካሰሙ በኋላ ዓለም “ሚ ቱ ” በሚለው ንቅናቄ ተናውጦ ነበር። ተዋናይት አሊሳ ሚላኖ ጥቃት የደረሰባችሁ ሁሉ “እኔም ተጠቅቻለሁ ” በሉ ካለች ወዲህ በ 24 ሰዓታት ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ሴቶች ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ ቁልፍ ቃል በ 80 አገራት ውስጥ መጠነ ሰፊ ንቅናቄን ፈጥሯል። ከዚህ ክስተት በኋላ በርካታ ሴት ተዋንያን ፌሚኒስት መሆናቸውን ይፋ አደረጉ። ያም ሆኖ ግን ጥናቶች አሁንም እንደሚያመለክቱት አብዛኞቹ ሴቶች “ፌሚኒስት” የሚለው ቃል እንደሚጎረብጣቸው ነው።
አኃዞች ምን ይናገራሉ?
በ 2018 በተደረገ አንድ ጥናት 34 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ፌሚኒስት ነን ሲሉ ተናግረዋል። ይህ አኃዝ በ 2013፣ 27 በመቶ ብቻ ነበር። በቅርብ ዓመታት ወደ አደባባይ የወጡ የጾታ እኩልነት ንቅናቄዎች ያመጡት ለውጥ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። አኃዙ በአውሮፓ አገራት መካከል እንኳ ሰፊ ልዩነት እንዳለ ያሳያል።መጠይቅ ከተደረገላቸው የጀርመን ሴቶች 8 ከመቶ ብቻ ‘ፌሚኒስት’ ነን ሲሉ በአንጻሩ 40 እጅ የሚሆኑት የስዊድን ሴቶች “ፌሚኒስት” ስለመሆናቸው በኩራት ተናግረዋል።ዋናው የጥናቱ ጭብጥ ስለምን ሴቶች “ፌሚኒስት” መባልን ጠሉ የሚለው ነው። የጥናቱ አስገራሚ ገጽታ ደግሞ ራሳቸውን ፌሚኒስት ብለው መጥራት የማይወዱ ሴቶች
43 በመቶ እንግሊዛዊያን፡ “ሴቶች ቤት መዋል አለባቸው“
27 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበትና በ2016 በአሜሪካ የተደረገ ሌላ ጥናት ከተጠያቂዎች ሁለት እጅ የሚሆኑ በጾታ እኩልነት የሚያምኑ ሆነው ተገኝተዋል። በ1977 ይህ አኃዝ አንድ አራተኛ ብቻ ነበር።
በተመሳሳይ በ 2017 በእንግሊዝ በተደረገ ሌላ ጥናት ከመቶ ስምንት እጅ የሚሆኑት ብቻ የሴቶች ሚና በቤት ውስጥ መወሰን ይኖርበታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ሴቶች ልጅ በማሳደግና ምግብ በማብሰል መወሰን አለባቸው ብለው የሚያምኑ ዜጎች ቁጥር በ 1984 ዓ.ም. 43 ከመቶ ደርሶ እንደነበር ማስታወስ ያሻል። ይህ አኃዝ የሚነግረን በዓመታት ውስጥ ትልቅ የአመለካከት ለውጥ መምጣቱን ነው። ጥያቄው አሁንም በዚህ ሰፊ የአስተሳብ ሽግግር በተደረገበት ዘመን እንኳ “ፌሚኒስት” መባል የማይወዱ ሴቶች ቁጥር ለምን ከፍተኛ ሆነ የሚለው ነው።
ቃሉ አሉታዊ ገጽታን ተላብሷል
በ2018 በተሠራ ሌላ የዳሰሳ ጥናት ከፍ ባለ የቢሮ ሥራ ላይ ያሉት እራሳቸውን “ፌሚኒስት” ብለው ለመጥራት አያፈገፍጉም።ነገር ግን ዝቅተኛ ሥራ ላይ በተሠማሩት መሀል ቃሉ እምብዛም አይወደድም።ሌላ ጥናት እንዳሳየው ደግሞ ፌሚኒዝም በነጮች ዘንድ ካልሆነ በሂስፓኒክ፣ በእስያና በጥቁሮች ዘንድ ጥሩ ስም የለውም። ሦስት እጅ የሚሆኑ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ሴቶች ፌሚኒዝም የነጭ ሴቶችን ሕይወት ያሻሻለ ነገር አድርገው ነው የሚወስዱት።
ሌላው ለቃሉ አለመወደድ ምክንያት ተደርጎ በጥናት የተወሰደው ነባር አስተሳሰቦች ለውጥ አለማሳየታቸው ነው። ስካርሌት ከርቲስ በቅርብ ባሳተመችው ” Feminists Do not Wear Pink and Other Lies” በተሰኘው መጽሐፏ እንዳሰፈረችው ፌሚኒስቶች በ 1920ዎቹ ትዳር ያልቀናቸው፣ ወንድጠል፣ በወሲብ ምርጫቸውም አፈንጋጭ፣እንዲሁም ወንዳ ወንድ ተደርገው ይታሰቡ እንደነበረና ይህ አስተሳሰብ ከመቶ ዓመት በኋላም እንዳልተቀረፈ ታስረዳለች። በዳሰሳ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ብዙዎቹ ሴቶችም እራሳቸውን “ፌሚኒስት” ከሚል ቃል ማራቅ የሚሹት ሰዎች ከላይ በተጠቀሱት አሉታዊ መገለጫዎች የተነሳ ነው።
እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የፌሚኒዝም ፅንሰ ሐሳብ እምብዛም የሚታወቅ አይደለም። ሆኖም፣ የ “ቢጫ እንቅስቃሴ” (YELLOW MOVEMENT) እና ፌሚኒዝምን የሚያራምዱ እና የሚደግፉ ጥቂት ቡድኖች አሉ። ፌሚኒዝም እምብዛም ጎልቶ የማይታይ ፅንሰ ሐሳብ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የሴቶች እኩልነትን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ትግሎች የሚያደርጉም ጥቂት ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች አሉ።
እነዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የመብቶች እና የእኩልነት እንቅስቃሴዎች የሴቶችን በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ እና ወንዶች በኅብረተሰቡ ውስጥ ስላሏቸው መብቶች ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚደግፉ ቢሆንም ፣ አንዳንዶቹ የሴቶችን በጉልህ የሥራ ቦታ መሾምን የመሳሰሉ የመንግሥት እርምጃዎችን ያበረታታሉ።
መነሻ ሃሳብ ፡- ቢቢሲ አማርኛ ዜና 2019
