ቀጸላ ክፍሌ
ያሳለፍነው አምስት ዓመት ስያሜው ‹‹ለውጥ›› የሚል ቢኾንም በርካታ ነውሮቻችን አደባባይ ወጥተው የተገለጡበት በዓለም ፊትም እጅጉን የተዋረድንበት ነው፡፡ የብልጽግና መንግሥት ከበሰበሰው የኢህአዴግ እንቁላል ውስጥ ‹‹ሕይወት ዘርቼ ወጣሁ›› ቢልም በግልባጩ ግን የዜጎችን ሕይወት በመቅጨት የሥልጣን ማማውን ለማስቀጠል ከመጣር የዘለለ ጠብ ያደረገው ነገር የለም፡፡ በዚህም ወንበሩ ይጸና ዘንድ ሚሊዮኖች ተገድለው ሚሊዮኖች ተፈናቀሉ፡፡ ሚሊዮኖች ተርበው ብዙ ሺዎች ቤት አልባ ኾኑ፡፡ ሀገር በዜጎቿ ላይ መፍረስ ጀመረች፡፡ ምክንያቱም በተለይም እንደኢትዮጵያ ባሉ ለም ሀገሮች ላይ መንግሥት አለው ተብሎ የሚታሰብበት ሀገር ውስጥ 25 ሚሊዮን ሕዝብ ሊራብ አይችልምና ነው፡፡ በርካታ ሚሊዮን ሕዝብም ሊፈናቀል አይችልምናም ነው፡፡ በአንድ ቀን ከ400 በላይ የደሃ መኖሪያ ቤቶች በግሬደር መፍረስ አይጠበቅባቸውምና ነው፡፡ በሀገረ ኢትዮጵያ በዘመነ ብልጽግና ግን ይህ ኾኗል፡፡
በያዝነው ሳምንት መንግሥት ከዓመት በፊት በነታምራት ነገራና መሰሎቻቸው ላይ ጀምሮት የነበረውን የአፈናና የዱርየ ሥራ አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ድምጽ የኾኑ በርካታ ምሁራንና ማኅበራዊ አንቂዎችን እያደነ ማፈን መደብደብ አንቱ የተባለ ግብሩ ኾኗል፡፡ ሰሞኑን የኛ ቴቪ በተባለው የበየነ መረብ ሚድያ የምስራቅ አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ በመኾን እያገለገለ የሚገኘው ንጉሴ ብርሃኑን ሲቪል በለበሱ የመንግሥት አካላት አፍነው በመውሰድ ከፍተኛ ድብደባ አድርሰውበታል፡፡ ይህ የፖለቲካ ተንታኝ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዓይን ገላጭ የኾኑ ትንታኔዎችን የሚሰጥ የመንግሥትን ክሽፈት የሚያመላክት እንዲሁም መማር የሚችል የመንግሥት አካል ቢኖር ዓይን ገላጭ አቅጣጫን የሚያስቀምጥ ተንታኝ ነው፡፡ ንጉሴ ብርሃኑ ድብደባው የደረሰበት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፈው ማክሰኞ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ያቀረቡትን ሪፖርት መተቸቱን ተከትሎ ነው፡፡
በተመሳሳይ በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት መምህርና የታሪክ ተንታኙ ታየ ቦጋለም ሲቪል በለበሱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ ደርሶበታል፡፡ መምህር ታየ ቦጋ እንደሚታወቀው “መራራ እውነት” የሚሰኝ ድንቅ የታሪክ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ለንባብ ያበቃ ግለሰብ ነው፡፡ ኾኖም በተለያዩ መድረኮች ስለኢትዮጵያዊነት በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ኩርፊያ የገባው የብልጽግና መንግሥት ይህን ነውረኛ ተግባሩን ፈጽሞበታል፡፡ ሕግን የመሰለ ነገር በሰፈነበት ዓለም ላይ መንግሥት ይህን መሰል አሳፋሪ ተግባር ሲፈጸም መስተዋሉ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ይህ ነውር ጌጡ የኾነው የመንግሥት ተግባር በዚሁ ሳምንት ሌላም ተመሳሳይ ሥራን አከናውኗል፡፡ ይኸውም ዘረፋ ነው፡፡ እንደአንድ ተራ ወንበዴ የተለያዩ ተቋማት መዝረፍን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡ ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤን ቢሮ ሰብሮ በመግባት የተለያዩ ሰነዶችን ዘርፎ ማስረጃዎችን ለማጥፋት ሞክሮ ነበር፡፡ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልዩ ልዩ ሰነድ ክፍሎችንም በመስበር በርካታ ታሪካዊ ሰነዶችን ለማጥፋት ሞክሯል፡፡
በዚሁ ግብሩ ቀጥሎበት ሰሞኑን ደግሞ የተለያዩ ሚዲያዎችን ቢሮ በመስበር የሚዲያ መገልገያ መሣሪያዎችን ዘርፏል፡፡ መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ/ም ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት የተፈጸመ ሲኾን የድርጅቱ መገልገያ የነበሩ አራት ዘመናዊ ካሜራዎች፣ ኔክማይክ፣ ዙመር እና ሌሎችም መገልገያ ቁሳቁሶች ተዘርፈዋል። ቁሳቁሶቹ አራት ኪሎ ሚዲያን ጨምሮ ነገረ ወልቃይት ጭምር የሚገለገሉባቸው ነበሩ። የሚዲያ ፕሮዳክሽን ቁሳቁሶቹ አጠቃላይ ዋጋ ከአንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ተነግሯል። ኢትዮ 251፣ አራት ኪሎ ሚዲያ እና ነገረ ወልቃይት ሚዲያ ወቅታዊ ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮችን በመዘገብና ጥልቅ ትንታኔዎችን በመስጠት ከሚታወቁ ቀዳሚ የዲጂታል ሚዲያ አማራጮች መካከል መኾናቸው ይታወቃል። በአጠቃላይ ከፍ ሲል የተገለጹት አጸያፊ ተግባራት መንግሥት በስውር ያከናወናቸው ተግባራት ናቸው፡፡ በአደባባይ ሲጠየቅ ደግሞ መንግሥት የሰፈር ሚሊሻ አለመኾኑን አስረግጦ ነግሮናል፡፡
የኾኖ ኾኖ አሁን ላይ ይህ ብቻ ሳይኾን አጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ አየር ተቀይሯል። የአገራችን ዋና ዋና የፖለቲካ ችግሮች፣ ተባብሰው ቀጥለዋል። እዚህም እዚያም የተለኮሱ የጥላቻ እሳቶች ሀገር እያነደዱ ነው፡፡ አንደኛውን ከሰል አድርገው ከማውደም የሚመለሱም አይመስሉም፡፡ እነዚህ አውዳሚ የጥላቻ እሳቶች ከተራ ዜጋ እስከከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ድረስ፣ ከወረዳ ኃላፊ እስከ ከንቲባ ድረስ፣ ከቤተ ክህነት እስከ ቤተ መስጊድ ድረስ፣ ከሚዲያ እስከ ማኅበራት ድረስ የተቀጣጠሉ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉም በጥላቻ እቶን እየታመሰ ነው፡፡ ይህ የጥላቻ እቶን እስካሁን አንዱ ጠይ አንዱን ተጠይ ያደረገ በመኾኑ አጥቂና ተጠቂ እንጂ ግጥሚያ አልነበረውም፡፡ ወደፊት ግን መጠላላቱ ገዝፎ መጥቶ ተጠቂ የነበረው ኃይል ፊቱን ወደ ማጥቃት ካዞረ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡
ይህ ማለት በመንግሥት ጠማማ ፖሊሲ ምክንያት ከዓመት ዓመት ሲራብ የቆየው በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ካራ ካነሳ፤ ‹‹ሀገርህ አይደለም›› እየተባለ በማንነቱ እየተሳደደ በተፈናቃይ ካምፕ የከተመው በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ፊቱን ካዞረ፤ ለዓመታት ጥሮ ግሮ የሠራው ቤት በአንድ አዳር ዶግ ዓመድ የኾነበት በሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ከተቆጣ ማጣፊያ ማጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ሰባት ኾኖ ‹‹ብሶት ወለደኝ›› ያለው ህወሓት ያሳካውን ግብ ሚሊዮን ኾኖ ‹‹ብሶት መረረኝ›› ብሎ እንደሚሳካለት ለአፍታ አያጠራጥርም፡፡
በተለይ ከሰሞኑ ዓይነት ሁኔታ መንግሥት ራሱን ማረቅ ካልቻለ ማጣፊያው ማጠሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የትም ሀገር የተበደለ ሕዝብ የመልስ ምቱ ከባድ እንደሚኾን ይታወቃል፡፡ የተናቀ ሕዝብ ፍጻሜው የከፋ ኾኖ በሀገር ላይ ከፍ ያለ ዳፋ ቢያስከፍልም ለመንግሥታቱ ግን ከሁሉም የከፋውን ጽዋ ያስጎነጫል፡፡ ያ ከመኾኑና ሀገርም የለየለት ፍዳ ውስጥ ከመግባቷ በፊት የብልጽግና መንግሥት ወደ ቀልቡ ሊመለስ ይገባዋል፡፡ በተለይም የሰሞኑን ዓይነት የሕዝብ ድምጽ የኾኑ ሰዎችን ማፈንና የዱርየ ተግባር መፈጸምን ማቆም ይኖርበታል፡፡ አሁን ያለው የፖለቲካ ድባብ፣ ከአምና ከካቻምና በእጅጉ የተለየ ነው። አየሩን ያወደው የብሽሽቅና የጸብ ወሬ ብቻ ነው፡፡
ሰሞኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ሀገሪቱ በሕገ መንግሥቱም ኾነ ሀገሪቱ ፈርማ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮሎች መሠረት የሕዝብን አንድነት የሚንዱ፣ ጥላቻንና ግጭትን የሚያባብሱ ንግግሮችና ድርጊቶችን ማሰራጨት የለባቸውም ሲል ገልጿል፡፡ በኃላፊነት ቦታ የተቀመጡ ግለሰቦች የሕዝቦችን አብሮነት በማስቀደም ተጨማሪ ግጭትና መራራቅ እንዳይፈጠር ተግተው ሊሰሩ ሲገባቸው አንዱን ሕዝብ መጤ ሌላውን ነባር፤ አንዱን ብሔር ፀረ ሰላም ሌላውን የሰላም ዘብ፣ አንዱን የኃይማኖት ተከታይ ሰላማዊ ሌላውን አመጸኛ አድርጎ መሳልና መከፋፈል በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግሯል፡፡ እኛም እንላለን፣ በሥመ ለውጥ የተገለጠው ነውር በአስቸኳይ ወደጓዳው ይመለስ፡፡
