‹‹በትምህርት ሥርዓቱ ዙሪያ ተጠያቂነት መኖር አለበት››

Date:

ዶ/ር አማኑኤል ኤርሞ

(የትምህርት ባለሙያ እና የኢዜማ ሊቀመንበር)

አሳሳቢውን የሀገራችንን የትምህርት ሥርዓት እየታዩ ካሉ ውጤቶች ጋር አሰናስለው ብዙዎች በተለያየ መድረክ እና አጋጣሚ ሥጋታቸውን ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ላይ የታየው አስደንጋጭ የውጤት ማሽቆልቆል በትውልድ ዕጣፈንታም ላይ ኾነ በሀገር ሁለንተና ላይ የሚኖረው ኪሣራ ብዙኃኑን በማሰሳብ ላይ ይገኛል፡፡ከጋዜጠኞ ፍቃዱ ማ/ወርቅ ጋር በትምህርቱ ዘርፍ ከአራት ዐሠርታት በላይ ያገለገሉትን እና እያገለገሉ ያሉትን ዶ/ር አማኑኤል ኤርሞን እንግዳ አድርገን በመጋበዝ እነኚህኑ አሳሳቢ ጉዳዮች አንስተናል፡፡ እንኾ፡-   

ግዮን፡- በቅድሚያ ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- አማኑኤል ኤርሞ እባላለሁ፡፡ ሦስተኛ ዲግሪዬን በትምህርት አመራርና አስተዳደር ላይ ነው የሠራሁት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግሎት እየሰጠሁ እገኛለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም በሀገራችን በሚገኙ የተለያዩ የትምህርት ተቋማትም በኃላፊነት ሠርቻለሁ፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሥር የከተማዋ መምህራን ሱፐርቫይዘሮችን በመምራት ለ8 ያህል ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ በትምህርት ቤቶች እንዲሁ በመምህርነት ረጅም ዓመታት የሠራሁ ሲኾን፣ በተጨማሪም በትምህርት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ ከማውጣት አኳያ ባለኝ አቅም የተለያዩ መጻሕፍትን ለማዘጋጀት ሞክሬያለሁ፡፡

ግዮን፡- መጻሕፍቶችዎ በምን በምን ርዕስ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው?

ዶ/ር አማኑኤል፡- አንደኛው መጽሐፍ ‹‹የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ተግዳሮቶች የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈተና›› የሚል ነው፡፡ በአማርኛ የታተመ ነው፡፡ ሌላው መጽሐፍ ደግሞ ‹‹የ21ኛው ክፍለ ዘመን የትምህርት አመራር›› የሚል ርዕስ ያለው ነው፡፡ ሦስተኛው መጽሐፌ ደግሞ ‹‹የትምህርት ሱፐርቪዢን አገልግሎት›› የሚል ነው፡፡ አራተኛው መጽሐፍም እንዲሁ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የትምህርት ጥራትን አስመልክቶ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የታተመ መጽሐፍ ነው፡፡

ግዮን፡- የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ብዙ ጊዜ ይተቻል፡፡ አሁን ላይ ምን ያህል ችግሮቹ በትክክል ተለይተው ለውጥ ለማምጣት ተሰርቷል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር አማኑኤል፡- የሀገራችን የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ በ1997 ዓ.ም የወጣ ነው፡፡ የዚህ ፖሊሲ ላይ ምሰሶ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ነገሮች የትምህርት ተደራሽነት ፣ የትምህርት ፍትሐዊነት ፣ የትምህርት ብቃት ፣ የትምህርቱ ተገቢነት እና የትምህርት ጥራት የሚባሉት ናቸው፡፡ በዚህ ፖሊሲ ሊሳኩ ጥረት ከተደረገባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ የትምህርት ተደራሽነት የሚለው ነው፡፡ የፖሊሲው የመጨረሻ ግብ ደግሞ ችግር ፈቺ ትውልድ ማፍራት የሚል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተወዳዳሪ እና መልካም ሥነ ምግባር ያለው ትውልድ ማፍራት ይጠበቃል፡፡

ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ በሀገራችን የተሠራው ሥራ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ትምህርት ተደራሽ ሲሆን ፍትሐዊነት የሚባለው ሂደትም አብሮ ይታሰባል፡፡ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እኩል ትምህርት እንዲያገኝ የተሠሩ መልካም ሥራዎች አሉ፡፡ ጥያቄው መኾን ያለበት በትምህርቱ ዘርፍ በትክክል እኛ የጠወደቅነው የቱ ጋር ነው የሚለው ነው፡፡ ይኽ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ መልሱ ብዙም አያሻማም፡፡ ‹‹የትምህርት ጥራት›› ላይ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ላይ ተገቢው ሥራ ካልተሠራ እንደ ተደራሽነት፣ አግባብነት እና ብቁነት የመሳሰሉት ግቦች ዋጋ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ የትምህርት ጥራት እስከሌለ ድረስ ተደራሽነትም፣ ፍትሐዊነትም፣ ተገቢነትም አይኖርም፡፡ በሌላ አነጋገር ብቁ ተወዳዳሪ እና መልካም ሥነምግባር ያለው የሰው ኃይል ማፍራት አይቻልም ማለት ነው፡፡

ግዮን፡- እስቲ አሁን ደግሞ ወደ ፖለቲካዊ ሕይወትዎ እንግባ፡፡ ፖለቲካ ውስጥ እንዴትና ምን ለማሳካት ገቡ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- በእኔ ዕምነት እያንዳንዱ ሰው የፖለቲካ ተሳትፎ አለው፡፡ ደግሞ ማንም ሰው የፖለቲካ መሀይም መኾን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካ ሀገራችንን ጨምሮ በማንኛውም ሀገር ዜጎች ኢኮኖሚዊም እንበለው ሃይማኖታዊ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ በኾነው ማኅበራዊ ሕይወታቸው ላይ ትርጉም አለው፡፡ ጠቅለል አድርገን ካስቀመጥነው ፖለቲካው በሀገሪቱ ያለውን ኃይል የሚይዝ ነው ልንል እንችላለን፡፡ ይህ ኃይል ደግሞ በሕብረተሰቡ ላይ መልካምም ይሁን መጥፎ ውጤት መፍጠር የሚችል ነው፡፡ በእኔ ዕምነት ለሀገራችን የሚበጀው ማንኛውም ዜጋ ሳይሸማቀቅ ሳይፈራ በሚበጀው መንገድ የጋራ ማንነቱን ይዞ ተባብሮ መኖር የሚችልበት ሁኔታን መፍጠር ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ‹‹ፖለቲካ›› ስንል አስተዳደርን የሚይዝ ስለሆነ ሀገራችን እንደማንኛውም ሀገር ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እንድትኖር እንፈልጋለን፡፡ ኾኖም በሀገራችን ያለው ሥልጣን ቀደም ብዬ የጠቀስኩትን የሰዎችን ሙሉ ማንነት መሠረት ያላደረገ በመኾኑ የዜግነት ፖለቲካ ትግል ያስፈልጋል፡፡ እኛ ይኽን በማሰብ ነው ወደ ፖለቲካው የገባነው፡፡ በግሌ በትክክል ወደ ፖለቲካ የገባሁበት ቀን ‹‹ይኼ ነው›› ማለት አልችልም፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካ ከምናነበው ነገር ጭምር በመነሳት ቀስ በቀስ በራስ ላይ እያደገ የሚሄድ እና በሒደትም ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ የሚወጣ ነገር ነው፡፡

በኢትዮጵያ እስካሁን የሚበዛው ነጠላ ማንነትን ማዕከል ያደረገ ፖለቲካ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የማንነት ፖለቲካ ለሀገራችን አይጠቅምም፡፡ ፖለቲካችን የጋራ ማንነት ላይ ያተኮረ እንዲኾን መሥራት የሚኖርብንም ለዚህ ነው፡፡ በሀገራችን ያለው ፖለቲካ፣ በሀገራችን ካለው የኢኮኖሚ ዕድገት የዴሞክራሲ ግንባታና ማኅበራዊ ትስስር ጋር ሲነፃፀር በጣም የቀጨጨ ነው፡፡ ዓለም ያለችበት ደረጃ እና እኛ ያለንበት ደረጃ ፍፁም የተራራቀ ነው፡፡ የሰው ልጅ ወደ ግብርና ሥርዓት እራሱን ያሳደገው ከክርስቶት ልደት በፊት ነበር፡፡ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የገባው ደግሞ የዛሬ አራት መቶ ዓመት በፊት ነበር፡፡ ዛሬም ላይ ቢኾን እኛ የመረጃ ዘመን ላይ ቆመን፣ ሌላው ዓለም ወደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንት እየነጎደ ነው፡፡ እኛ ገና በምግብ ራሳችንን ያልቻልን በግብርና ላይ ጥገኛ የኾን ዜጎች ነን፡፡ ለዚህ ሁሉ ሁኔታ ዋነኛ ምክንያቱ የሀገራችን ፖለቲካ አለመዘመንና አለማደግ ነው፡፡

መፍትሔው ደጎሞ ሕዝብን መሠረት ያደረገ ግን ደግሞ ከሕዝብ አርቆ ማሰብ የሚችል መሪ መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ እውነታ ከተነሳን ወደ ፖለቲካ መግባት በትኩረት ላስተዋለው ሁሉ ግዴታ ነው፡፡ በእኔ ዕምነት እውቀት ያለው ሁሉ ወደ ፖለቲካ መግባት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ሳይንሱ ‹‹ፖለቲካን ፖለቲካ ያወቀ ሰው የሚጫወትበት ገበጣ ነው›› ይለዋል፡፡ በጥቅሉ ፖለቲካ የምሁራን ጨዋታ ነው፡፡ እኔም ወደ ፖለቲካ የገባሁት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በዚህም እኔም የራሴን አስተዋፅዖ አደርጋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ለሀገራችን እና ለሕዝባችን እድገት፣ ለሉዓላዊነታችን፣ ለዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ መረጋገጥ ብሎም ሀገራችንን ከኋላ ቀርነትና ድህነት ለማላቀቅ ደግሞ መታገል ይኖርብናል፡፡

ግዮን፡- የኢዜማ አባል ከኾኑ ምን ያህል ጊዜ ኾነዎት? ያሎት ኃላፊነትስ ምንድነው?

ዶ/ር አማኑኤል፡- የኢዜማ አባል ከኾንኩ ቆይቻለሁ፡፡ አሁን ላይ በፓርቲው ያለኝ ኃላፊነት ግን የፓርቲው ሊቀመንበርነት ነው፡፡

ግዮን፡- ወደ ትምህርቱ ጉዳይ እንመልስዎትና በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ምን ያህል ዓመት ሠሩ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ከ40 ዓመታት በላይ በትምህርቱ ዘርፍ ማለትም በማስተማርና በትምህርት አስተዳደር አገልግያለሁ፡፡

ግዮን፡- ከነበሮት ረጅም የአገልግሎት ጊዜ አንጻር፣ ባለፉት ሦስት ሥርዓቶች የነበረውን የትምህርት ፖሊሲ እና አፈጻጸም በንጽጽር እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር አማኑኤል፡- በደርግ ግዜ የነበረው የትምህርት ሥርዓት ትንሽ የተለየ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው በወቅቱ የነበረው የሶሻሊዚም ሥርዓት ነበር፡፡ ያኔ ትምህርት ለንቃተ ሕሊና ተብሎ ነበር የሚሠጠው፡፡ ከዛ በኋላ በነበሩት ፖሊሲዎች ግን ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ትምህርት ከአምስት በላይ ምሰሶዎችን መሠረት አድርጎ ነው የሚሠጠው፡፡ ያኔ የነበረው የተማሪ ቁጥርም አነስተኛ ነው፡፡ ዛሬ ግን የተማሪው ቁጥር በጣም ብዙ ነው፡፡ ወደ 22 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ በፊት ይህን ያህል የተማሪ ቁጥር አልነበረም፡፡ በደርግ ጊዜ ከምናያቸው ነገሮች አንዱ የደርግ መንግሥት ትምህርት ለርዕዮት ዓለም አስፈላጊ እንደኾነ ቢያውቅም፣ በትምህርት ሥርዓቱ ግን ጣልቃ አይገባም ነበር፡፡

እኔ ለምሳሌ በወቅቱ የደርግ አባልም አልነበርኩም፡፡ ነገር ግን በነፃነት በዘርፉ እንቀሳቀስ ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ በትምህርት ላይ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በዝቶ ይታያል፡፡ የሰከነ የመማር ማስተማር አመራር የመስጠር ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ በትምህርቱ ዙሪያም የተረጋጋ ሁኔታ የለም፡፡ አሁን ላይ ደግሞ የሀገራችን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታ አልፎም ማኅበራዊ ሁኔታችን የተረበሸና ያልተረጋጋ ነው፡፡ ኢኮኖሚው፣ ፖለቲካው እና ማህበራዊ መስተጋብራችን ባልተረጋጋበት ሁኔታ ደግሞ የትምህርት ሥራ አስቸጋሪ ይኾናል፡፡

ግዮን፡- በትምህርት ሥርዓቱ ዙሪያ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- የትምህርት ሥርዓቱ ላይ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መኖር አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ላይ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በግልፅ ይታይ ነበር፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው ዓመት ላይ ከነበሩ ተፈታኝ ተማሪዎች መካከል ያለፉት 3 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 97 በመቶዎቹ ተማሪዎች ደግመዋል፡፡ ይኼ ሲኾን ከባድ ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ይመጥናሉ ብሎ ነው የሚፈትናቸው፡፡ ነገር ግን እነሱ ሲወድቁ ተጠያቂው ብዙ ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች የሚመጡት ከክልል ነው፡፡ ክልሎች ደግሞ የራሳቸው የፖለቲካ መዋቅር ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ የወደቁ ተማሪዎችን መሠረት በማድረግ ክልሎች መጪዎቹ ተፈታኞች ላይ ምን ያህል ሥራ ሠርተዋል የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡

ክልሎች ችግሩ እንዳይደገም ‹‹ኢንተርቬሽን›› መሥራት አለባቸው፡፡ አካዳሚው ዙሪያ የሚገኘውን በየደረጃው ያለውን ባለድርሻ አካል አሳምነው ስትራቴጂ ቀይሰው ፈጣን እቅድ አዘጋጅተው ወደ ተግባር ማስተካከል ሲኖርባቸው ይኽን ሲያደርጉ አልታዩም፡፡ ይኽ ባለመኾኑ ምክንያት በሁለተኛው ዓመት መልቀቂያ ፈተናም መልሶ ከ3 በመቶ በላይ ተማሪ ማለፍ ሳይችል ቀረ፡፡ ይህ ማለት ፖለቲካው ‹‹እኔ አዋቂ ነኝ፡፡ ትምህርቱን የምመረምረው እኔ ነኝ›› እስካለ ድረስ ለውጥ አይመጣም ማለት ነው፡፡ ዘንድሮ ያለፈው ተማሪ ብዛትም እንደሰማነው 5.4 በመቶ ነው፡፡ አሁንም ከትምህርት ጥራት አኳያ ትርጉም ያለው ኾኖ አይገኝም፡፡ ምክንያቱም ከትምህርት ጥራት ደረጃ አንጻር ካለፉት ተማሪዎች ምን ያህሉ ናቸው 75 በመቶ በላይ ያመጡ ተብለው ቢመዘኑ 1 በመቶ እንኳን ላይሞሉ ይችላል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ የትምህርት ጥራት የለም ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

የትምህርት ጥራት ማለት ‹‹ሚኒመም ስታንዳርድ›› ማለት አይደለም፡፡ አንድ ሰው ከ100 ሃምሳ አምጥቶ አለፈ ማለት አይደለም፡፡ የትምህርት ጥራት ለማለት አንድ ተማሪ 85 እና ከዚያ በላይ ማምጣት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለንበት ሁኔታ ፖለቲካው ትምህርቱን አጀንዳ አድርጎ አለመያዙን ግልጽ ያደርግልናል፡፡ ፖለቲካ ትምህርትን አጀንዳ አድርጎ መያዝ ካለበት ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ነው የሚጀምረው፡፡ ለዚህ ምሳሌ ላንሳ፡-

ለምሳሌ አሜሪካና ሩሲያ ተፎካካሪ በነበሩበት ዘመን መጀመሪያ ወደ ሕዋ የመጠቀችው ሩሲያ ነበረች፡፡ ሩሲያ ወደ ሕዋ ስትመጥቅ አሜሪካ ‹‹እኔ እዚያ ደረጃ ላይ ያልደረስኩት የትምህርቴ ጥራቴ ላይ ችግር ስላለው ነው›› ብላ ወሰነች፡፡ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገንም በትምህርት ላይ ‹‹ኔሽን ፍሌክስ›› የሚል ሕግ አወጣ፡፡ ምክንያቱም ባላንጣው ወደሕዋ ስለመጠቀ በትምህርት ላይ በደንብ መሠራት እንዳለበት በማመኑ ነበር፡፡ በጥሩ ሁኔታ በመሥራቱም ሀገሩን ወደ ሕዋ ማምጠቅ ቻለ፡፡ ከዚያ በኋላ ፕሬዝዳንቱም የራሱን ትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ሕግ አውጥቶ የበለጠ አጠነከረው፡፡ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም ሌላ የተሻለ ሕግ በማውጣት የትምህርት ጥራቱን ከፍ አደርጓል፡፡ ወደ እኛ ሀገር ስንመለስ በንጽጽር የተሠራው ሥራ ምንድነው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

ዳግማዊ ምኒልክ ዘመናዊ የተባለውን ትምህርት አስተዋወቁ ፤ ዐጼ ኃይሌሥላሴ ያን የትምህርት ሥርዓት አስፋፉ፡፡ የደርግ መንግሥት ደግሞ የሶሻሊዚም ትምህርትን አስተዋወቀ፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታን የምናየው ነው፡፡ ስለዚህ የትምህርት ሥርዓታችን ሀገርን ታሳቢ ያደርገ የመንግሥት አጀንዳ መኾን አለበት፡፡ ለምሳሌ የኮሪደር ልማቱ መንግሥት አጀንዳ አድርጎ ስለያዘው ነው በዚህ መልክ እየተፈፀመ ያለው፡፡ የትምህርት ሥርዓትም በዚህ መልኩ የመንግሥት አጀንዳ መኾን ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡

ግዮን፡- ካነሱት አይቀር፣ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከ1 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ አለመቻላቸው ተገልጽዋል፡፡ ይኼ እንደ ሀገር የሚኖረው ውጤት እንዴት ይታያል?  

ዶ/ር አማኑኤል፡- አንድ ሀገር ኢንተርቬንሽንና ተጠያቂነት የሚባል ነገር ያስፈልገዋል፡፡ ‹‹ኢንተርቬንሽን›› ስትራቴጂ ነድፎ ችግሩን መቅረፍ ነው፡፡ ተጠያቂነት (አካውንቲቢሊቲ) ግን በኃላፊነት ላይ ያለው ባለሥልጣን ተጠያቂ የሚኾንበት አሠራር ነው፡፡ እኛ ሀገር ተጠያቂነት የሚባል ነገር ባለፉት 30 ዓመት አልነበረም፡፡ ለነገሩ ተጠያቂነትን የሚያመጣው ሕግ ነው፡፡ የትምህርት ሕግ ደግሞ የለም፡፡ ተጠያቂነት የሚያስከትል የትምህርት ሕግ የለንም፡፡

ለምሳሌ ዘንድሮ 1163 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አላሳለፉም፡፡ ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች የአንዱ ርዕሰ መምህር የኔ ተማሪ ነበር፡፡ እንደነገረኝ ከኾነ ትምህርት ቤታቸው በመጀመሪያ ዓመት ፈተናም አንድም ተማሪ አላሳለፈም፡፡ ‹‹እናስ ምን አደረጉ›› ስለው ስብሰባ ጠሩኝ አለ፡፡ ስብሰባ ሲጠሩት ሊያስሩት መስሎት እንደነበር ነገረኝ፡፡ ‹‹ለምን?›› ስለው መጠየቅ እንዳለብኝ አውቃለሁ አለኝ፡፡ ነገር ግን ስብሰባ ተቀምጠን ‹‹ሁለተኛ ተማሪዎች እንዳይወድቁ›› ብለው አበላችን ባንክ መግባቱን ነግረውኝ ተመልሼ መጣሁ አለኝ፡፡ ይኼ ተጠያቂነት አለመኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡ ተጠያቂነት በየደረጃው መኖር አለበት፡፡ ተጠያቂነት የሚጀምረው ከራሱ ከተማሪው ፣ ከወላጅ ፣ ከመምህሩ ፣ ከትምህርት ቤቱ አመራር ፣ በየደረጃው ካለው አካል ነው፡፡ ምክንያቱም ትምህርት የግለሰብ ሳይኾን የጋራ ሥራ ውጤት ስለኾነ፡፡ ስለዚህ ተጠያቂነትን በሚገባ ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ ተጠያቂነት ከሌለ ለውጥ አይመጣም፡፡ አሜሪካኖች እነዚያን ሁሉ ሕጎች ሲያወጡ ተጠያቂነትም አብረው በማረጋገጥ ጭምር ነበር፡፡ እኛም ሀገር ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል፡፡ ባልተፃፈ ሕግ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ተጠያቂነት የሚያሳይ ሕግ ሊኖረን ይገባል፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን ወንጀለኛ መቅጫም ይሁን ፍትሐብሔር ሕግ ላይ ተማሪ በመውደቁ ተጠያቂው አካል ይቀጣ የሚል የለንም፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተጠያቂነት መስፈን ካልቻለ ችግሩ በየዓመቱ የሚደገም ይኾናል፡፡ በእርግጥ በትምህርት ሥርዓቱ ዙሪያ የተጠያቂነት ሕግ ማውጣት ለርዕሰ መምህሩና መሰል አካላት ጉዳት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለሀገር ያለው ጠቀሜታ ግን የገዘፈ ነው፡፡ ስለዚህ ተጠያቂነት እራሱ መፈራት የለበትም፡፡ ተጠያቂነት ማለት መታሠር ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በትምህርት ሂደቱ በርካታ የሀገር ሀብት ባክኖ ተማሪ ማለፍ የማይችል ከኾነ ትምህርት ቤቱ ቢዘጋ የተሻለ ነው፡፡ ትምህርት ቤት ፍሬ የማያፈራ ከኾነ ትምህርት ተዘጋ ቢባል ምን ይገርማል? ነገር ግን ትምህርት ሲዘጋ እነዚህ መምህራን የት ይሄዳሉ? ፍሬ አላፈራህም የተባለ ዛፍ እንደሚቆረጠው ፍሬ ያላፈራም መምህርም ወደ ቤቱ ሊሸኝ ይችላል፡፡

ግዮን፡- አንዳንዶች ለተማሪዎች መውደቅ እንደምክንያት የሚያቀርቡት የሚፈተኑበትን ቦታና የፈታኞች ማንነት አዲስ በመኾኑ በሚደርስባቸው ሥነልቦናዊ ሥጋት ነው ይላሉ፡፡ ምን ይላሉ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ይኼ ፈፅሞ አሳማኝ ያልኾነ እዚህ ግባ የማይባል ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በቀጣይ ዓመት ዩንቨርሲቲ ገብተው የሚማሩ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መፈተናቸው ይበልጥ ሞላራቸውን ይገነባዋል እንጂ እንዴት ወደ ሥነልቦናዊ ሥጋት ይከታቸዋል? ተማሪዎች የሚፈተኑት ያነበቡትን ነው፡፡ በዚያ ላይ ከራሳቸው ባልደረቦች ጋር በመኾን ነው፡፡ ለአንድ 12ኛ ክፍል ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ግቢ መፈተን የተሻለ መነሳሳትን ይፈጥርበታል እንጂ በምንም መልኩ መደናገጥና የሥነ ልቦና ውድቀት አያስከትልበትም፡፡ በሌላ በኩል ተማሪዎች በዚህ ሁኔታ መፈተናቸው የሚያደርስባቸው ‹‹የሥነልቦናዊ ጉዳት አለ›› የሚል ጥናት በሌለበት ሁኔታ ይህን ምክንያት ለመውደቃቸው ሰበብ አድርጎ ማቅረብ ተቀባይነት የለውም፡፡

ግዮን፡- ለተማሪዎች ውድቀት እንደ ምክንያት የሚነሳው ሌላው ጉዳይ በሀገሪቱ ያሉ ተማሪዎች በቂ የትምህርት አጋዥ መሳሪያዎችን አለማግኘታቸው ነው፡፡ በዚህስ አይስማሙም?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ይህን በተመለከተ የሚነሳው ችግር ያፈጠጠ ሀቅ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ያለው ችግር የከፋ ነው፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የትምህርት ተገቢነት የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ተማሪ ማወቅ አለበት ተብለው የተቀመጡ ብቃቶች አሉ፡፡ እነዚህ ብቃቶች ለሚመለከተው አካል ሁሉ ኃላፊነት የተሰጡ ናቸው፡፡ ማለትም በመምህሩ መምሪያ እና በተማሪው ደብተር ላይ የሚቀመጡ ናቸው፡፡ የትምህርቱ አጠቃላይ ዓላማ ዝርዝር ዓላማና ይዘት በሚል ተያይዘው የተቀመጡ ናቸው፡፡ ተማሪዎች እነዚህን መጽሐፍት ካላገኙ ለጉዳት ይዳረጋሉ፡፡

ይህ የሚኾነው ደግሞ ተማሪዎች እራሳቸው እንዲያጠኑ ምቹ ሁኔታ ሳይኖራቸው ሲቀር፤ ወላጅ ሊረዷቸው ሳይችል ሲቀር፤ እንዲሁም መምህሩ የቤት እና የክፍል ሥራ ሳያሠራ ተማሪዎቹንም ሳይከታተል ሲቀር ነው፡፡ መምህሩ ሲለበሱን በመጠቀም ተማሪዎች በሴሚስተር ውስጥ መማር የሚገባቸውን ሥርዓተ ትምህርት ወይም በዓመት ውስጥ ተማሪዎች መማር የሚገባቸውን ያህል ማስተማር ካልቻለ በጣም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የመምህር መምሪያና የተማሪዎች አጋዥ መፅሐፍት መኖር በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ግድ ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ያለው ምርጫ አንድ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ኦንላይን መጠቀም ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በጣም ከባድ ነው፡፡ ኦንላይን ማስጠቀም የሚችል መሠረተ ልማትም ፤ እንደስልክ ያሉ መገልገያ መሣሪያዎችም የሉም፡፡

ግዮን፡- አብዛኞቹ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጡበት የትምህርት ዘርፍ ላይ ጥናት መደረግ የለበትም ይላሉ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- እዚህ ላይ ማስተዋል ያሉብን ነገሮች አሉ፡፡ ፈተና በራሱ የትምህርት ጥራት አይደለም፡፡ ፈተና ደረጃውን ጠብቆ ለተማሪዎች የሚሰጥ ማረጋገጫ ነጥብ ነው፡፡ ያ ማለት ተማሪው ትምህርቱን መማሩን ለማረጋገጥ የሚጠቅም መሳሪያ ማለት ነው፡፡ የትምህርት ጥራት የሚያረጋግጠው በቂ የትምህርት ግብዓት ኖሮ ለማስተማር ቁርጠኛ የኾነ መምህር እና ለመማር ዝግጁ የኾነ ተማሪ ሲኖር ነው፡፡ በተጨማሪም በመማር ማስተማሩ ሂደት ዙሪያ ንቃት ያለው አመራር ሲኖር እንዲኹም ልጆቹን መከታተል የሚችል ወላጅ ሲኖር ነው የትምህርት ጥራት ዕውን የሚኾነው፡፡ መጀመሪያ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ባልተሠራበት ሁኔታ ስለ ፈተናው መጨነቅና ማውጠንጠን ትርጉም አልባ ድካም ነው፡፡ ፈተና በማክበድ ብቻ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ቁልፍ ጉዳይ የመማር ማስተማር ሂደቱ ደረጃውን ጠብቆ መሳለጥ መቻል ነው፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ዋነኞቹ ባለሚናዎች ተማሪው፣ መምህሩና ሥርዓተ ትምህርቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሦስት መስተጋብሮች በሥርዓት ካልተሠሩ ትምህርት ጥራት እውን ሊኾን አይችልም፡፡ ሁሉም መሥራት ያለበት ኃላፊነት ላይ ማተኮር ይኖበታል፡፡

ግዮን፡- ኩረጃ የማስቀረት ሂደት ላይስ ከመሠረቱ መሠራት የለበትም ይላሉ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ከአሁን ቀደም ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ ተማሪዎች ሁሉንም ትምህርት በአንድ መምህር ነበር የሚማሩት፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በፈተና ሳይወድቁ እንዲያልፉ ይደረግ ነበር፡፡ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ባለው የክፍል እርከን ላይም ተማሪዎች የክፍል ሥራና የቤት ሥራ ሠርተው ማርክ ይያዝላቸዋል፡፡ ‹‹የእጅ ሥራ ሠርተዋል›› ተብሎ ማርክ ይያዛል፡፡ እነዚህ  ማርኮችም ተደምረው የትምህርት ዓይነቱን 60 በመቶ ነጥብ ይይዛሉ፡፡ ይህ ማለት ተማሪዎች አዕምሮአዊ ፈተና ሳይፈተኑ 60 በመቶ ውጤት አግኝተዋል ማለት ነው፡፡ የቤት ሥራ በወላጅ ሊሠራ ይችላል፡፡ የቡድን ሥራውም በጓደኛ ይሠራል፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ በአቴንዳንስና በደብተር አያያዝ ሳይቀር ውጤት ይያዛል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ዓይነቱ አሠራር መወገድ አለበት፡፡ ማንኛውም በማርክ የሚያዝ ነጥብ ተማሪው በአዕምሯዊ ብቁነቱ፣ በእውቀቱና በልፋቱ የሚያገኘው ሊኾን ይገባል፡፡

ግዮን፡- የትምህርት ዓይነቶች መብዛት በተማሪዎች ውጤት ማጣት ላይ የእራሱ ‹‹ተጽዕኖ አለው›› ይባላል፡፡ ይህን እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ትምህርት መሰጥት ያለበት በምጣኔ ነው፡፡ መጥነን ማስተማር ይኖርብናል፡፡ ቀደም ሲል ግብርና፣ የእጅ ሥራ፣ ሙዚቃ፣ አርት፣ ወዘተ… የሚባሉ ትምህርቶች ይሰጡ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የሀገራችን ፖለቲካ ያመጣው ማንነት ተኮር ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ ይህም ማለት ተማሪዎች በብዙኃን ቋንቋ ብቻ ሳይኾን በማንነታቸውም ቋንቋ እንዲማሩ ይደረጋሉ፡፡ እንደእውነታው ግን በአንዳንድ ማንነት ተኮር ቋንቋዎች መማር መቋጫው ላይ በዚያ ቋንቋ የሚያነቡት ነገር አለመኖርን ያስከትላል፡፡ ለምሳሌ እኔ አንድ ቦታ ሄጄ በከንባትኛ ብማር ጋዜጣ ማንበብ፣ ቲቪ ማዳመጥ፣ ልዩ ልዩ መጻሕፍቶችን ማንበብ የምችልበት ሁኔታ የለም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ቋንቋ የተፃፉ ነገሮች ባለመኖራቸውና ውስን በመኾናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ስለትምህርት ሲታሰብ ንቁ ተወዳዳሪ መልካም ሥነምግባር ያለው ዜጋ ማፍራት መኾኑ ሊታጣ አይገባም፡፡ ንቁ ሲባል የተሠጠውን ኃላፊነት መወጣት የሚችል ማለት ነው፡፡ ተወዳዳሪ ሲባል ደግሞ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አቻዎቹን የሚመጥን መኾን ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ መልካም ሥነምግባር ሲባል ደግሞ በየትኛውም ሀገር እንደዜጋ ለሰው ልጅ የበጎ ነገር ምሳሌ ኾኖ የሚኖር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የትምህርት ሥርዓታችን መቀረጽ ያለበት ማንነት መሠረት አድርጎ ሳይኾን ከፍ ሲል የተጠቀሱትን ነጥቦች ታሳቢ አድርጎ መኾን ይኖርበታል፡፡

ግዮን፡- አንዳንዶች ‹‹አዲስ አበባ ውስጥ የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ከመሠጠቱ ጋር ተያይዞ፣ ለተማሪዎች ኦሮምኛ ማወቅ የበለጠ ማርክ ስለሚያስገኝላቸው ተማሪዎች ላይ የመጨነቅ ነገር ይታያል›› ይላሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ተማሪዎች ትምህርት ሲያበቁ ሥራ የሚፈልጉበት ቋንቋ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሥራ ቋንቋው ከአንድ በላይ ወደመኾን እየተሸጋገረ ነው፡፡ ስለዚህ ለተማሪዎች ቋንቋ ማወቅ በራሱ ጥቅም አለው፡፡ ተማሪዎች ቋንቋ በማወቃቸው ይጠቀማሉ እንጂ አይጎዱም፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ያለ ልጅ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ ቢማር ችግር የለውም፡፡ አካሄዱ ላይ ግን ችግሮች አሉ፡፡ ተማሪዎች ቋንቋውን ሲማሩ ተገደው ሳይኾን ፈልገው እንዲማሩ ማድረግ ይገባል፡፡ በጥቅሉ ግን ሀገራችን አሁን ባለችበት ደረጃ የትኛው የትምህርት ዓይነት ለተማሪዎች መቅረብ አለበት የሚለው መጠናት ይኖርበታል፡፡ በእርግጥ አይነኬ የኾኑ የትምህርት ዓይነቶች አሉ፡፡ እነዚህን የትምህርት ዓይነቶች ሀገራችንን ካለችበት ሁኔታ አንፃር አጥንቶ መለየት ይገባል፡፡

ግዮን፡- ከትምህርት መስፋፋትና ከትምህርት ጥራት መቅደም ያለበት ተግባር የቱ ነው ይላሉ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- የትምህርት መስፋፋት የሚያመላክተው የትምህርትን ተደራሽነት ተግባራዊ መኾኑን ነው፡፡ ስለዚህ የትምህርት ተደራሽነት መኖር በጣም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ተደራሽነቱ ከትምህርት ጥራት ጋር አብሮ መሄድ ይኖርበታል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችንም አሁን ላይ በራሳቸው ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተማሪው እያነሰ ሠራተኛው እየበዛ ነው፡፡ ይህ መኾኑ ደግሞ ብክነትን ያስከትላል፡፡ በመኾኑም በዚህ ዙሪያም ጥናት መደረግ ይኖርበታል፡፡ በአጠቃላይ በዋናነት የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ መምህሩ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩን አንድመምህር በተማሪዎች ውጤት ላይ ቢያንስ 35 በመቶ ተጽዕኖ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ መምህሩ አሁን በሀገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምንም እርዳታ የለውም፡፡ በዚህ ዙሪያ ተማሪው 40 በመቶ፣ ወላጅ 10 በመቶ እንዲኹም ርዕሰ መምህሩ 10 በመቶ በመማር ማስተማሩ ውጤታማነት ላይ ሚና አላቸው፡፡

ከዚህ አንፃር የመማር ማስተማሩ ትልቁ ቁልፍ ያለው በመምህሩና በተማሪው መካከል ነው፡፡ መምህሩ ላይ በጣም መሠራት አለበት፡፡ አሁን ባለው ሀገራዊ ተጨባጭ ያልተረጋጋ ሁኔታ እንደሀገር የመማር ማስተማር ሂደቱ በአግባቡ እየተከናወነ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በጥቅሉ የተማሪዎች ውጤት እና የትምህርት ጥራት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የላቀ የተማሪዎች ውጤት ለማምጣት የላቀ አገልግሎት ያስፈልጋል፡፡ የላቀ አገልግሎት በመስጠት በኩል ደግሞ ግንባር ቀደም ሚና የሚጫወተው መምህሩ ነው፡፡ ከዚያ ከፍ ሲል ደግሞ እራሱ ተማሪው ለትምህርት ያለው ዝግጁነት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በየደረጃው የሚኾኑ እንደ ወላጆችና የትምህርት አመራር ያሉ ባለድርሻ አካላት ባለሚናዎች ናቸው፡፡

ግዮን፡- በግል ትምህርት ቤቶችና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች መካከል የሚታየው የትምህርት አሠጣጥ ልዩነት ያለው ይመስላል፡፡ ይህን ለማቀራረብ ምን ማድረግ ይገባል ይላሉ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ልዩነታቸው የሚጀምረው ከተማሪ አቀባበላቸው ጀምሮ ነው፡፡ የግል ትምህርት ቤት የሚቀበለው የተሻሉ ተማሪዎችን ነው፡፡ የመንግሥት ትምህር ቤት ግን የብዙኃን ስለኾነ ሁሉንም ዓይነት ተማሪ ተቀብሎ ያስተናግዳል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የግል ትምህርት ቤት ላይ ክትትሉና ቁጥጥሩ ጠበቅ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም ቢዝነስ በመኾኑና የትምህርት ቤቱ ዋና ገቢ ተማሪው ስለኾነ ነው፡፡ በመንግሥት ትምህርት ቤት ግን ትምህርት በገንዘብ ሳይኾን በነጻ የሚሰጥ የዜግነት ድርሻ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈም ፖለቲካዊ ቢሮክራሲዎች የሚገኙት በመንግሥት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ለማቀራረብ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያሉ አመራሮች ላይ መሠረታዊ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ቁጥጥሩ እንዳለ ኾኖ ለመምህራን በቂ ክፍያ ከፍለው ስለሚያሠሩ መምህሩ አቅሙን አሟጦ ይሠራል፡፡ ተማሪዎችንም ቢኾን በከፍተኛ ክትትል ግዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡ የመንግሥት ትምህርት ቤት ግን ሰዓት ከመሸራረፋቸው በላይ በተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ክፍለ ጊዜዎች እንዲባክኑ ያደረጋል፡፡ በጥቅሉ የግል ትምህርት ቤቶች መምህሩንም ተማሪውን መርጠው የሚወስዱ ናቸው፡፡ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ይህን ለማቀራረብ ረጅም ጊዜ ይጠይቃል፡፡

ግዮን፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ-ገዝነት ያለው ጥቅም ምንድነው?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀት ማዕከል ናቸው፡፡ ዓለም ላይ ኦክስፎርድ የሚባል ዩኒቨርሲቲ አለ፡፡ ይህ ዩኒቨርሲቲ ራስ-ገዝ ነው፡፡ ሌሎች በርካታ ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች እውቀታቸውን እየሸጡ ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‹‹እውቀት መሸጥ ይችላል ወይ?›› የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲው እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል ወይ?›› የሚለው አጠራጣሪ ነው፡፡ በእርግጥም ሀገሪቱ አንጡራ ሀብቷን አራግፋ ያስተማረቻቸው ምሁራን አሉት፡፡ ተቋሙ የያዛቸውን ምሁራን አቅም ተጠቅሞ ‹‹ገንዘብ ይሠራል ወይ?›› የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ ስለዚህ ዩኒቨርሲቲው እየሄደበት ያለው አካሄድ በእኔ ምልከታ ትክክለኛ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሌሎች ሞዴል ከመኾኑም በላይ ከኋላ ቀራዊ የአሠራር ሂደት ይላቀቃል፡፡ ተወዳዳሪም ይኾናል፡፡

ግዮን፡- በመጨረሻ ማለት የሚፈልጉት ነገር ካለ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- የትምህርት ጥራትን ለማምጣትና ሥርዓቱን ለማሻሻል ስትራቴጂ መንደፍ አለብን፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ ዙሪያ ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ በየጊዜው የትምህርት ሥርዓታችንን እየፈተሸን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ በተለይ በመምህሩ ላይ መሠራት ይኖርበታል፡፡ በተማሪና በወላጅ እንዲሁም በትምህርት አመራሩ ላይም መሠራት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፖለቲካው በአካዳሚው ውስጥ ጣልቃ ባይገባ መልካም ነው ብዬ ሐሳቤን አጠቃልላለሁ፡፡

ግዮን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም እናመሠግናለን፡፡   

———-

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 216 ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!! በክርስቲያኖች ዘንድ ጥምቀት...

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...