‹‹መቅረዝ ጥራትን በማጉደል ሰዎችን መጥቀም ይቻላል ብሎ አያምንም››
‹‹ሆስፒታሉ የደንበኞች አገልግሎት ሥልጠና ለመስጠት አቅዷል››
የዛሬው የመጽሔታችን እንግዳ በቅርቡ አገልግሎት መሥጠት የጀመረው መቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ የአክስዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ማኅተመ በቀለ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ማኅተመ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የሕክምና ኮሌጅ የቀዶ ሕክምና መምህርም ናቸው፡፡ በዘርፉም ከዐሥራ ኹለት ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ በእርሳቸው፣ በሙያ አጋሮቻቸው እና በሌሎችም ሰዎች የተቋቋመው መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር አንድ የፕሮጀክት አካል የኾነው መቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል ከመጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት መሥጠት ጀምሯል፡፡ ለመኾኑ አክሲዮኑን ከማቋቋም ጀምሮ የሆስፒታሉን ውጥን እውን እስከማድረግ ድረስ የነበሩት ሒደቶች ምን መልክ ነበራቸው? ሆስፒታሉ አሁን ባለው ሁኔታ ተወዳዳሪ እና የላቀ የሚያደርጉት መለያዎቹስ ምንድናቸው? በአክስዮኑ ሥር ወደፊት ተግባራዊ የሚኾኑ ቀጣይ ፕሮጀክቶችስ ምን ምን ናቸው? ሲል የግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ከፕሮፌሰር ማኅተመ በቀለ ጋር የሚከተለውን ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡ እነኾ!
ግዮን፡- ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- ማኅተመ በቀለ እባላለሁ፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የሕክምና ኮሌጅ በሙሉ ፕሮፌሰርነት የቀዶ ሕክምና መምህር ነኝ፡፡ በዋናነት የምሠራው ጠቅላላ ቀዶ ሕክምና ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኩላሊት ንቅለ ተከላ እሠራለሁ፡፡ ለዲያሌሲስ ታካሚዎች ደግሞ ኤቪ ፌስቱላ እሠራለሁ፡፡ በቅርቡ ደግሞ የትልቁ አንጀት የፊንጢጣና የመሳሰሉት ችግሮችን የማክምበት ሰብ ስቤሻሊቲ ጀምሬአለሁ፡፡ ይህን ጉዳይ ከተለያዩ ውጭ ከሚገኙና ሀገር ውስጥ ካሉ ዩንቨርስቲዎች ጋር እየሠራንበት እንገኛለን፡፡ በቀዶ ሕክምና ላይ ከ12 ዓመት በላይ ቆይቻለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈም የተለያዩ ጥናቶችን እሠራለሁ፡፡ እስካሁንም የተለያዩ ትልልቅ ጆርናሎች ላይ ከ50 በላይ ጥናቶችን አሳትሜያለሁ፡፡ እነዚህም ተገምግመው ሙሉ ፕሮፌሰር እንድኾን አስችለውኛል፡፡ አሁንም የጥናት ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመኾን ኮሌጁን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡ ከዚህ በፊት የድንገተኛ ክፍል፣ አስተኝቶ ማከምና የቀዶ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ኾኜ አገልግያለሁ፡፡ አሁን ደሞ የጥናት እና ምርምር ዳይሬክተር ነኝ፡፡
ግዮን፡- ፕ/ሮ ማኅተመ በመቅርዝ ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ ያለዎት ኃላፊነት ምንድነው?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- የመቅርዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ ነኝ፡፡
ግዮን፡- መቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል መቼ ተቋቋመ? የመቋቋሙ ምክንያትስ ምንድነው? አርማስ ምንን ይገልፃል?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- መጀመሪያ መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ነው የተቋቋመው፡፡ መቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል የመቅረዝ ጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር አንዱ ፕሮጀክት ነው፡፡ አርማው የሕክምና ተቋምን ያሳያል፡፡ የቀይመስቀል ምልክት አለበት፤ የሕክምና መመርመሪያ ቁሳቁስን ይዟል፤ ታካሚዎችን በታላቅ ስነምግባር ምናገለግልበት በዚህም ስራችን እንደሚገለጥ የሚያስረዳ የብርሃን ምልክት አለው፡፡ ስለምስረታው ስናስብ ሆስፒታሉን የማቋቋም ጽንሰ ሐሳቡ የቆየ ነው፡፡ በህክምና የተመረቅን ሀኪሞች የሀገራችንን የጤና አገልግሎት እንዴት ማሻሻል እንዳለብን እናስብ ነበር፡፡ የድርሻችንን ለመወጣት በየጊዜው እንነጋገር ነበር፡፡ ይህ ንግግራችንም ወደ ተግባር ገብቶ ለዚህ ሊበቃ ችሏል፡፡ እኛ መጀመሪያ ሃሳባችን በትንሹ ነበር፤ ነገር ግን ቁጭ ብለን ሌሎች ባለሞያዎችን በማካተት ከፍተኛ አድረገነውል፡፡ መቅረዝ ላይ ያለው የቦርድስብስብ ሁሉም ሐኪም ብቻ ሳይኾን ከተለያየ ዘርፍ የመጡ ናቸው፡፡ ይህ በመኾኑም ተቋሙ የሀስብን የአደረጃጀት ውስንነት የለበትም፡፡ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የተቃኘ ሳይኾን ሁሉንም ያቀፈ ነው፡፡ ለምሳሌ ኅብረተሰቡ ስለ ሕክምና ያለው አተያይ ምንድነው የሚለውን ለማወቅ ችለናል፡፡ እኛ ያለን አተያይ ከማከም አንፃር ነው፡፡ ከመታከም አንጻርስ የሚለውን የሚያውቀው ኅብረተሰቡ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ከቢዝነስ ፣ተደራሽነት እና ግንባታ አንጻርም ለማየት ተችሏል፡፡ ከሁሉም አንጻር እንዲታይ አደረጃጀት እያስተካከልን መጥተናል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም ብዙ ሰዎች ተቀያይረዋል፡፡ እኔ ደግሞ ከመሠረቱ ጀምሮ ከነበሩት ጥቂት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ በጥቅሉ የሥራ ቅኝታችን ከሁሉም አንፃር ስናደርገው ሥራችን መደበኛ የሆነ አቅጣጫ መያዝ ቻለ፡፡ ለሀገራችን የሚመጥን፣ የሰዎችን ችግር የሚፈታ፣ ኅብረተሰቡን የሚያረካ እንዲኾን ለማድረግ እየጣርን ነው፡፡
ሁሉም ታካሚዎች በሀገራችን እንዲታከሙ ለማድረግ በትልቅ ደረጃ መሥራት እንዳለብን በማሰብ ነው አክሲዮኑን በሰፊው የጀመርነው፡፡ ምንድነው ውጪ ሀገር ያለው ብለን አየን፡፡ በሀገራችን ያለውን የግሉን ዘርፍም አየነው፡፡ ሕክምና አገልግሎት ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው፡፡ በመንግሥት ብቻ ተሸፍኖ የሚቻል አይደለም፡፡ ስለዚህ ብዙ የግል አገልግሎት ሰጭ ማዕከላት ያስፈልጋሉ፡፡ ይህ የግሉ ሴክተር ደግሞ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማደግ ይኖርበታል፡፡ እኛም ስንጀምር ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር አድቫንስድ የኾኑ አራት ፕጀክቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ጥራቱን የጠበቀበኁላ ወደ ተርሸሪ የሚያድግ ጠቅላላ ሆስፒታል ነው፡፡ ሁለተኛው ከፍተኛ አገልግሎት መሥጠት የሚችል የጊያግኖስቲክ ማዕከል መገንባት ነው፡፡ ሦስተኛ ደግሞ ትልቅ ወደማኑፍክቸሪግ የሚያድግ የፋርማሲ አገልግሎት መሥጠት ነው፡፡ ሌላውና አራተኛው ጤና ተኮር የሕብረተሰብ አገልግሎት የሚባል ነው፡፡ በዚህ ረገድ አገልግሎት ለመሥጠት ተዘጋጅተን ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አደረጃጀታችን መኾን ያለበት በአክሲዮን ነው፡፡ ምክንያቱም በራሳችን ገንዘብ አዋጥተን ኩባንያ ብናቋቁም ትንሽ ገንዘብ ይዘን ስለኾነ ወደ ኅብረተሰቡ የምንቀላቀለው ያሰብነውን ነገር መሥራት አያስችለንም፡፡ ስለዚህ ከፍ አድርገን ለመጀመር ወሰንን፡፡ በግሌ ይህን ወደመሰለው የአክሲዮን ሥራ ስገባ እና ሳደራጅ የመጀመሪያዬ ነበር፡፡
ስለዚህ ወደ 100 የምንጠጋ ባለሙያዎች ተነጋገርን አራት ሚሊዮን ብር ሰብስበን፤ መስከረም 12/2013 ዓ.ም አክሲዮኑን አስመዘገበን፡፡ በጊዜው እንደ አደራጅ ሰብሳቢ በመኾን የንግድ ፍቃድም በእኔ ስም ነበር፡፡ ካለችኝ ትርፍ ሰዓት እየቆነጠርኩ ሥራውን አከናወንኩ፡፡ ይህን ካደረግን በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተን አቅማችንን ለማሳደግ ሞከርን፡፡ መቅረዝ የሚያስበው በትልቁ ስለኾነ ካፒታላችንን አንድ ቢሊዮን አስመዝግበን፡፡ አክሲዮን መሸጥ ጀመርን፡፡ በዚህ ወቅት የነበረው ችግር የኮቪድ 19 መምጣት የሰዎችን የመኖር ሕልውና ጥያቄ ውስጥ አስገባ፡፡ በአንድ በኩል ሰዎች ሕክምና ተቋም መገንባት እንዳለብን ያመኑበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ግን የኮቪድ መከሰትና የመኖር ዋስትና ማጣት የኦኮኖሚ ውዥቀት ፈተና ኾነ፡፡ ስለዚህ ኢንቨስትመቱ ሰው እንዳሰበው የሚሳተፍበት መኾን አልቻለም፡፡ ሌላው ፈተና የኾነበት ከእኛ በፊት የነበሩ አክሲዮኖች የነበራቸው ታሪክ ነው፡፡ በተለይ ተሰበስበው ጠፉ የሚባለው ነገር ከባድ ነበር፡፡ ይህን መሰል ፈተና ባይገጥመን ኖሮ ከዚህ በቀደመ ጊዜና በተሻለ መልኩ መሥራት እንችል ነበር፡፡ አሁን የደረስንበት 250 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ በጣም ብዙ ጊዜ ፈጅቶብናል፡፡
በሌላ በኩል ፕሮጀክቱን ወደ ተግባር ለውጦ ለመሥራት ከተማው ውስጥ ያለው ሕንፃ አመቺ አልነበረም፡፡ አብዛኛው በከተማዋ የሚገኝ ሕንፃ ለሆቴል፣ ለአፓርትመንት፣ ለንግድ የተዘጋጀ ነበር፡፡ ስለዚህ ለሆስፒታል የሚኾን ሕንፃ ማግኘት በራሱ ፈተና ነበር፡፡ በትንሹ ስፔሻሊስት ክሊኒክ ትንሽ ቦታ ይዞ መክፈት ይቻላል፡፡ ጠቅላላ ሆስፒታል ሲባል ግን ከባድ ነው፡፡ እኛ ከአራቱ ፕሮጀክቶች በመጀመሪያ እናሳካለን ብለን ያሰብነው የሆስፒታልና የዲያግኖስቲክ ፕሮጀክት ነበር፡፡ ስለዚህ ሆስፒታሉን ከዓመት በፊት ካሳንቺስ አካባቢ የቀድሞው ዮርዳኖስ ሆቴል ለመክፈት ተስማማን፡፡ በዚህም የመጀመሪያው ሕልማችንን እውን አደረግን፡፡ ነገር ግን ከፍ ሲል እንደገለጽኩት የዚህ ሆስፒታል ሕንፃ ሆቴል ነው፡፡ ወደ ሆስፒታል ስናመጣው ሰዎች እንደ ሆስፒታል የሚጠቀሙበትና የሚገለገሉበት ለሐኪሙም ለታካሚውም ምቹ እንዲኾን ለማድረግ ሠርተናል፡፡ ቀለም ቀብቶ መግባት ሳይኾን ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታል ለማድረግ ሠርተናል፡፡ ዝግጁ ሲኾንም ከአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ፈቃድ አግኝተን ወደ ሥራ ገባን፡፡
ግዮን፡- አንድ ዓመት ሙሉ ወደ ሥራ ሳይጀምሩ ኪራዩን መክፈል አይከብድም?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- ልክ ነው ያለሥራ ኪራዩን መክፈል ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ለምን ይኽን ያህል ጊዜ ያለሥራ ቆየን ስንል ግራውንድ +10 እና ግራውንድ +3 ሕንፃ ማደስ ነበረብን ፡፡ ጎን ለጎንም የሆስፒታሉን መገልገያ እቃዎችን ለማምጣት ጊዜ ያስፈልግ ነበር፡፡ የሕክምና እቃ የሚያስገቡ ሰዎች ደግሞ የምንዛሬ ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ያዘዝናቸው እቃዎች በተመደበው የጊዜ ቀመር መሠረት መቅረብ አልቻሉም ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ሙሉ እቃ ኖሮን ለመጀመር ነው እቅዳችን ፤ምክንያቱም ቃል የገባነው ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ለመሥራት ነውና ነው፡፡ በመኾኑም ሁሉንም ነገር አሟልተን ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ ለምሳሌ የኦፕሬሽን ክፍላችን ከፍተኛ አየርን የማጣራት አቅም ያለው ሲስተም የተገጠመለት ነው፡፡ ይኼ ኢንፌክሽን በማፅዳት ማንኛውንም ሰርጀሪ ንፅሕናውን እንደተጠበቀ ለመሥራት ይረዳናል፡፡ ይኼ የተቋሙን ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ የአጥንት ህክምና በማንኛውም ኦፕሬሽን ክፍል መሥራት ቢቻልም እኛ ግን ሲ አርሞችን ገጥመን ጨርሰን ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ የአይሲኦ ማሽኖች ገብተው፣ የማዋለጃ ማሽኖቻችን ገብተው፣ ሊሎች በርካታ ነገሮችም ከተሟሉ በኋላ ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ እነዚህ መሣያዎች እስኪገቡ ድረስ ነው ግንባታው የተካሄደው እና ጊዜው ያራዘመው፡፡ እኛ ይኼን ሁሉ በስድስት ወር ውስጥ እንጨርሳለን ብለን ነበር፤ ነገር ግን ዐሥር ወር ጨርሶብናል፡፡
ግዮን፡- ከማሽነሪዎቹና ከቁሳቁሱ በተጨማሪ በመድኃኒት አቅርቦት ዙሪያ ያጋጠማችሁ ተግዳሮት ነበር?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- መድኃኒት የአንድ ጊዜ ሥራ ሳይኾን ቀጣይነት ያለው ሥራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የመድሀኒት እና የህክምና አቅራቢ ሰዎቻችን የተለያዩ ችግሮች ገጥመዋቸው እንጂ እኛን በጣም ተባብረውናል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች ጋር ትክክል ሳይኾን ሲቀር ውል አቋርጠናል፡፡ በጥቅሉ ወደ መድኃኒቱ ስመለስ መድኃኒት ቀጣይነት ያለው ሥራን የሚጠይቅ ነው፡፡ በየክፍሉ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሁሉንም አሟልተናል፡፡ በተጨማሪም ፋርማሲ አለን፡፡ አሁን ላይ ሦስት ፋርማሲዎች አደራጅተን መድኃኒት አስገብተናል፡፡ የላብራቶሪ ሬጅንቶችም አሟልተናል፡፡ ሬጀንቱን ከሚያቀርበው ካምፓኒ ጋር ለቀጣይ አቅርቦት ውል ፈፅመናል፡፡ ሕክምና በአንድ ሰውና በአንድ ነገር ብቻ የሚሠራ ሳይኾን የብዙ ነገሮች ስብጥር ነው፡፡ በመኾኑም በሕብረት እየሠራን ነው፡፡
ግዮን፡- መቅረዝ አጠቃላይ ሆስፒታል መቼ ተከፈተ? ሲከፈት ቀደመው ለመጡ መቶ ሰዎች ነፃ ሕክምና እንደምትሰጡ ገልጻችሁ ነበር፡፡ ምን ዓይነት ሕክምና በነፃ ሰጣችሁ?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- በጋዜጣዊ መግለጫችን እንዳነሳነው በ12/2015 ሕክምናውን ከፍተናል፡፡ መቅረዝ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ፍኖተ ካርታ ነድፎ የመጣ ተቋም ነው፡፡ ተቋማችን አትራፊ ተቋም ነው፡፡ ካለትርፍ መቀጠል አይችልም፡፡ አንድ የሚያተርፍ ተቋም ግን ከኅብረተሰቡ ጋር ጥብቅ ትስስር ሊኖረው ይገባል፡፡
ስለዚህ ተቋሙ መቶ የማኅበረሰቡን አባላት በነፃ ለማገልገል ኃላፊነት የወሰደበት ነው፡፡ እነዚህ መቶ ሰዎች በማንነታቸው እገሌ ተብለው የሚታወቁ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ከሕፃናት ማደጊያ፣ ከአረጋዊያን ተቋም የመጡ ሕክምናውን አግኝተዋል፡፡ የሕክምናውን ዓይነት በተመለከተ የትኛውም ዐይነት ሲኾን በዋናነት ተመላላሽ ሕክምና ላይ ትኩረት ያደረ ነው፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ ግን ማኅበራዊ ኃላፊነታችን ስንወጣ በሌላ ዘርፍ እንደሚኾን ግልጽ ነው፡፡ ትርፋችንን ካወቅን በኋላ በተሻለ መልኩ ማኅበራዊ ኃላፊነታችን እየተወጣን እንቀጥላለን፡፡ ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት አክሲዮን መኾናችንም የራሱ ጥቅም አለው፡፡
ግዮን፡- የውጪ ሀገር ጉዞ ሕክምናን ለማስቀረት እንደምትሠሩ ገልጻችኋል፡፡ ይህንን በተመለከተ ሰው በምን ዓይነት ሕክምና ወደ ውጪ እንደሚወጣ ጥናት ሠርታችኋል? ይህን ነገር ለማቀረትስ ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- መቅረዝን ስንከፍት ለሁሉም ዘርፍ ቢዝነስ ፕላን አዘጋጅተን ነው፡፡ ምን እንደሚጎድልና የትኛው የአገልግሎት ዘርፍ እንደሚያስፈልግ አጥንተን ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ በነገራችን ላይ ወደ ሥራው ከመግባታችን በፊት በትንሹ ለአራት ዓመት አስበንበታል፡፡ ቢዝነስ ፕላኑን ስንሠራ የትኛው ችግር ላይ የኅብረተሰቡ ፍላጎት ምንድነው የሚለው ሁኔታ ከግምት አስገብተን ነው፡፡ ከዚም ውስጥ አንዱ ውጪ ሄዶ መታከም ሲኾን ሌለው ሀገር ውስጥ ሕክምናው እየተሰጠ በተሻለ ደረጃ መቅረብ የሚችልበት ላይ መሥራት ነው፡፡ ለዘርፉ የሚመጥን ብቁ የሰው ኃይል ማደራጀትም ያስፈልጋል፡፡ ሰብስፔሻል ብቻ ማከማቸት ሳይኾን ተቋሙ ከጽዳት ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የሥራ ሂደት ድረስ ብቃት ባላቸው ሰዎች እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡
በጥቅሉ ግን ሀገር ውስጥ ያሉ ሰብ ስፔሻሊስት ሁሉ እኛ ጋር አሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰብ ስፔሻሊስቶቹ ባለአክሲዮን ናቸው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አገልግሎቱን እኛም እናቀርባለን፡፡ በሌላ በኩል የመቅረዝ አደረጃጀት አሁን ባለንበት ጠቅላላ ሆስፒታል ተብሎ ሰብ ስፔሻሊስት እንዲያገለግሉበት እቃዎችን ያስገባል፡፡ ስለዚህ አንድ የኩላሊት እስፔሻሊስት እኛ ጋር ሲፈልግ ዲያሌሲስ አለው፡፡ አንድ የአጥንት ሕክምና የሚሠራ ሰው አንድ ነገር እዚያው እያየ መሥራት ስለሚፈልግ ሲአር ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ሲአር አለን፡፡ ከዚህ በላይ የሚያስኬዱ ጉዳዮች ሲኖሩም ደግሞ ለምሳሌ እንደ ፒቲ ስካን ያሉ የካንሰር ስርጭትን የሚያሳዩ መሣሪያዎች የቀጣይ ጊዜ እቅዶቻችን ናቸው፡፡
ሰዎችን በጣም በቀላሉ ወደ ውጪ ሀገር ለሕክምና የሚያስወጣቸው ያለው አመለካከት ነው፡፡ ይህን ለማስቀረት ደግሞ ሕንፃና መሰል ነገሮች አያስፈልጉም፡፡ ተቋምን በደንበኛ አገልግሎት መገንባት ነው ይህን አመለካከት የሚያስቀረው፡፡ መቅረዝ ይህን በማድረግ ያለውን ችግር ያስቀራል፡፡ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶም እየሠራበት ይገኛል፡፡ በመኾኑም መቅረዝ እራሱን የቻለ የደንበኞች አገልግሎት ሥልጠና ለመስጠት አቅዷል፡፡ መቅረዝ በአገልግሎት አሰጣጡ ቅሬታ እንዳይነሳበት ይሠራል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሰው እዚህ የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች ወጭ ሄዶ ታክሞ ይመጣል፡፡ ይህን ለማስቀረት መቅረዝ በትጋት ይሠራል፡፡ ሌሎቹንም በደረጃ እዚሁ ለመሥጠት እንሞክራለን፡፡ ለምሳሌ የልብ ቀዶ ሕክምና በሀገራችን በበቂ ሁኔታ የለም ፡፡ እኛ ጋር የልብ ቀዶ ሕክምና ለመስጠት ሁሉንም ነገር በማዘጋጀትና ላይ እንገኛለን፡፡ የኩላሊት ንቅለ ተከላም መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት ከመንግስት ገር በመተባበር ለማስጀመር ጥረት እናደርጋለን ፡፡
ግዮን፡- በአንድ ጊዜ ሰባት የኩላሊት አጠባ እንጀምራለን ብላችሁ ነበር፤ ምን ማለት ነው ይኼ?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- አማርኛው ትክክል አይደለም፤ በእንግሊዘኛ የኩላሊት አጠባ የሚባል ነገር የለም፡፡ የሄሞ ዲያሌሲስ ነው የሚባለው፡፡ በደም ውስጥ ያለውን ከሰውነት መወገድ ያለበትን የኩላሊት ሥራ በማሽን ማሠራት ማለት ነው፡፡ በተለምዶ ግን ኩላሊት እጥበት ይባላል፡፡ ይህን በተመለከተ መቅረዝ ሰባት መደበኛ 3 ቪአይፒ በድምሩ ዐሥር የኩላሊት አጣባ የሚያገለግሉ አልጋዎች አዘጋጅተል ፡ ይህን ለመሥራት ከመንግሥት የምንጠብቀው ነገር የለም፡፡ ወደፊት ግን የኩላሊት ንቅለ ተከላን ለመሥራት ከመንግሥት ጋር እንሠራለን፤ ማለትም እስካሁን ለምሳሌ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አገልግሎቱ እየተሰጠ የሚገኝ ሲኾን ወደ ግል ጤና ተቋማት ግን አልዞረም፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ምክንያት ይኖረው ይኾናል፡፡ እኛ ደግሞ ይህን ከመንግሥት ጋር ተቀራርበን በሚሰጠን አቅጣጫ መሠረት ሥራውን ለማከናወን እንሞክራለን፡፡ እስከአሁን በመንግሥት ብቻ ይሰጥ ስለነበርም ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንጥራለን ማለት ነው፡፡ መንግሥት እንድንሠራ ከፈቀደልን መቅረዝ በዚህ ሥራ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የግል ተቋም ይኾናል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ሥራ በእኛ ብቻ ሳይኾን በየትኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ ተቋም ቢጀመር ደስተኞች ነን፡፡ ከየትኛውም ተቋም ጋር በትብብር ለመስራትም ዝግጁ ነን ፡፡
ግዮን፡- መቅረዝ በቴክኖሎጂ ከሌሎች የሀገራችን የዘርፉ ተቋማት በተሻለ መጥቷል ብላችኋል፤ ይህን ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- በቴክኖሎጂ መቅረዝ ጥቃቅን የሚመስሉ ግን ጥራት ያላቸው ነገሮችን ይዞ ቀርቧል፡፡ የመጀመሪያው የኤም አር ሲስተማችን ሲኾን በአዲስ መልክ የተደራጀ ነው፡፡ ይሕ በመኾኑም የኤም አር ብራንድ የራሳችን ነው፡፡ ከአንድ ትልቅ ኤቴክ ከተባለ ካምፓኒ ጋር ተዋውለን የተሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ጥሩ ፕላት ፎርም ይዘን መጥተናል፡፡ ለሌሎችም ይጠቅማል ብለን እናስባለን፡፡ ሌላው ታካሚዎቻችንን በሩቅም በቤታቸው ሆነው በአካልም እናገለግላለን፡፡ ዲጂታል ሪማይንደር እናደርጋለን፡፡ አስፈላጊ ሲኾን እቤታቸው ኾነው ሕክምናውን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ይህን የምናደርገው በቴሌና በቪዲዮ በመታገዝ ነው፡፡ በዚህ ሕክምና ታካሚው በቀጠሮ ወደ ሆስፒታል ሲመጣም ሊያደርጋቸው የሚገቡ ቅድመ ዝግጅቶችም ይነግሩታል፡፡ ተዘጋጅቶ ይመጣል፤ ይህን ዘርፍ የሚሠራ ራሱን የቻለ ክፍል አለ፡፡
ሌላው መቅረዝ ለየት የሚደርገው ነገር የሕመምተኛነት ስሜትን በተመለከተ የሚሰጠው አገልግሎት ነው፡፡ ለምሳሌ ሆስፒታል ሄዶ ቀዶ ሕክምና የሚሠራለት ሰው የኾነ ቦታው ስለኾነ የታመመው ያ ሲወጣለት ጤነኛ ሰው ነው፡፡ ሆስፒታሉ ታካሚያኑ የበሽተኛነት ስሜት እንዳይኖራቸው ክፍሎቻችን ያደረጀንበት ሁኔታ ልዩ ነው፡፡ ለምሳሌ የፕሬዝደንሻል ሩም የሚባል ክፍል አለን፡፡ ይህ ክፍል በጣም ሰፊ ሲኾን የራሱ የኾነ ስቲም፣ ጃኩዚ፣ ኪችን፣ ፍሪጅና መሰል ነገሮች አለው፡፡ ትልልቅ ባለሐብቶች የሚስተናገዱበት ኮንፍረስ የሚዘጋጅበት ነው፡፡ ይህ በራሱ የታካሚውን አዕምሮ ፈታ የሚያደርግ ነው፡፡
ሌላው ደግሞ እያደራጀነው ያለው የጂም እና ዌልነስ ማዕከል ነው፡፡ ሰዎች እዚያ መጥተው ፊትነሳቸውን የሚሠሩበት የተኙም ይሁን ተመላላሽ ታካሚዎች አገልግሎቱን የሚያገኙበትን ሁኔታ ተዘጋጅቷል፡፡ በሌላ በኩል እስካሁን ባለው ልምድ በሆስፒታል ውስጥ ቤተ-መጽሐፍት የለም፡፡ መቅረዝ ግን ቤተ-መፅሐፍት አለው፡፡ ሁሌ ከምግብ በኋላ ለሰው መጽሐፍ ይዞርለታል፡፡ በዚህ ሂደት የማንበብ ባሕል ይዳብራል፡፡ ሰዎች ካለባቸው የሕመም ጫና እና ጭንቀት እንዲወጡም ይረዳቸዋል፡፡ ታካሚውም ይሁን አስታማሚው ቁጭ ብሎ በማንበብ የተሻለ ነገር ያገኛል፡፡ ይኼ ከተለመደው ቁጭ ብሎ ማውራት የተለየ ነው፡፡ በሌላ በኩል በየክፍሎቹ ቴሌቪዥኖች አሉ፡፡ በዋይፋይ ኮኔክት መኾን የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚያም ታካሚው ወይም አስታማሚው የራሱን ኮኔክት አድርጎ መጠቀም ይችላል፡፡
ግዮን፡- ከምትሰጡት የአገልግሎት ልሕቀት አንፃር የታችኛውን የማኅበረሰብ ክፍል በቀላሉ ተጠቃሚ ሊኾንበት ይችላል?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- መቅረዝ ጥራትን በማጉደል ሰዎችን መጥቀም ይቻላል ብሎ አያምንም፡፡ መቅረዝ ሲፃፍ በ”k” መፃፍ ይቻላል፡፡ እኛ ግን “k” በ“Q” ነው የተካነው፡፡ “Q” የምታመላክተው “ኳሊቲ” ወይም ጥራት የሚለውን ነው፡፡ ስለዚህ መቅረዝ ጥራትን አያመቻምችም፡፡ ጥራትን ከግምት በማስገባት ዋጋ መቀነስ ተገቢ አይደለም፡፡ እኛ ከማንም በታች እንወርዳለን አላልንም፡፡ እኛ ለአገልግሎታችን ተመጣጣኝ ዋጋ እናስከፍላለን፡፡ የትም የሌለ አገልግሎት ከሰጠን ከሌላው ጋር መወዳደር አይኖርብንም፡፡ የምንሰጠው አገልግሎት የዋጋ ተመን ያወጣነውን የሚሸፍንልና ትርፍ በሚያስገኝ ዐይነት መልኩ ነው የሚኾነው፡፡ ለምሳሌ መቅረዝ የሕፃናት ክፍል በጣም የሚያምር ነው፡፡ እንደውም ለልጆቼ የክፍሉን ቪዲዮ ሳሳያቸው መጫወቻ ቦታ መስሏቸው ውሰደን ብለውኛል፡፡ ክፍሉ በዚህ ልክ የሚስብ ነው፡፡ ይህን ኢንቨስት ያደረግነው ታከሚዎቹ ተደስተው እንዲሄዱ ሲሆን እኛም አገልግሎቱን የሚያስቀጥል ገቢ ለማገኘት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ዋጋችን ወርዶ ጥራት እንዳይዛባ ወይም ዋጋችን በዝቶ ጥራት እንዳይቀንስ ሁሉም ነገር ተመጣጣኝና በልኩ እንዲኾን እንሠራለን፡፡ የቢዝነስ ፕላን ስንሠራ ጥናት ስናደርግ ይህን ከግምት አስገብተን ነው፡፡ የተለያዩ ማስታወቂያዎችንም እየሠራን ነው፡፡ በመግለጫችን ላይም ለመጀመሪያ ታካሚዎቻችን 30% እንደምንቀንስ አስታውቀናል፡፡
ግዮን፡- በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጨ ለማስፋፋት ያላችሁ እቅድ ምን ያመስላል?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- ይህን ማድረግ የመጀመሪያ እቅዳችን ነው፡፡ ሆስፒታል የመጀመሪያው ሲኾን ሁለተኛው ደግሞተርሸሪ ሆስፒታል ነው፡፡ ቀጣዩ እቅዳችን ደግሞ ቴርሸሪ ሆስፒታል ነው፡፡ ይህን የምናስበው በመከራየት ሳይኾን ከመንግሥት ጋር በመነጋገርና ቦታ ተረክቦ በመገንባት ነው፡፡ የሆስፒታል ዲዛይኑ አለን፡፡ አዲስ አበባ ውስጥም በምናገኘው ቦታ ቴሪሸሪ ሆስፒታል እንገነባለን፡፡ ሁሉንም አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡ ሪሐብሊቴሽን ሴንተር ጨምሮ የሚሰጥ ነው የሚኾነው፡፡ ሰው ከታከመ በኋላ ሪሐቢቴሽን ያስፈልገዋል፡፡ ይህን አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ይህ ዘርፍ በሀገራችን ያልተሠራበት ዘርፍ ነው፡፡ ሁሉም ቦታ ሰው ታክሞ መሄድ ብቻ ነው የሚታወቀው፡፡ ነገር ግን ሰው ከታከመ በኋላ ሪሐቢሊቴሽን ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ እኛ የምንገነባው ቴሪሸሪ ሆስፒታል ይህን ማዕከል ያካከተተ ነው፡፡ በሚቀጥለው አምስት ዓመት ውስጥ ይህን እውን ለማድረግ አቅደናል፡፡ በሌላ በኩል መቅረዝ እንደ ብራንድ መውጣት አለበት፤ ስለዚህ ቅርንጫፍ ሆስፒታሎችን መክፈት ትልቁ እቅዱ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ላይ ይከፍታል፡፡ ታካሚው ከጋምቤላ አዲስ አበባ፣ ከመተማ አዲስ አበባ ከሌላውም ሩቅ ቦታ ወደ አዲስ አበባ መምጣት የለበትም፡፡ ስለዚህ ብራንዶችን አስጠብቀን ባሉን ሞዴሎች በሀገሪቱ ወደ ሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ቅርጫፎች እንከፍታለን፡፡
የፋርማሲ ሥራችንም ቢኾን እንደ ሆስፒታሉ በልዩ ሁኔታ ነው የሚመጣው፡፡ ፋርማሲያችን እንደምናያቸው መድኃኒት ቤቶች መድኃኒት በመቸርቸር ብቻ አይገደብም፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ይገባል፡፡ ትንንሽ መመረት የሚችሉ ግን ደግሞ በሀገራችን የማይመረቱ የፋርማሲ ዕቃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የተለያየ ናሙና መውሰጃ ቴስት ቱዩቦች እዚህ አይመረትም፡፡ እነዚህ መሰል ነገሮችን ለማምረት ጊዜውን ጠብቀን ለመሥራት እንሞክራለን፡፡ እንደ ሀገር የውጪ ምንዛሬውን ለመቆጣጠር እነዚህን ማምረት ያስፈልጋል፡፡ በቦርዱ ውስጥ ያለ ባለሙያም የራሱን ኃላፊነት እየተወጣ ይሄዳል፡፡ አሁን አንድ ማኔጅመት አለን፡፡ በሲኦው ስር ዳይሬክተሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ዳይሬክተሮች አሳይመንታቸውን እየወሰዱ በመሥራት ያመጣሉ፤ በዚህም ያሰብናቸውን እናሳካለን፡፡ አክሲዮናችም እየሸጥን እንቀጥላለን፤ አሁን ያለን የተመዘገበ ካፒታል አንድ ቢሊዮን ነው፡፡ 250 ሚሊዮን ሸጠናል፡፡ ለመጋቢት 30 ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተናል፡፡ አቅጣጫ ሰጥተን ለሚቀጥሉት ፕሮጀክቶች ስያሜዎቻችንን እንቀጥላለን፡፡
ግዮን፡- በሀገራችን በባለሙያዎች የተቋቋመ አክሲዮን የእናንተ የመጀመሪያው ነው?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- እኔ የማውቃቸው በብዛት ፒኤልሲ ዎች ናቸው፡፡ ምናልባት ግን አንድ ሌላ ተቋምም ያለ ይመስለኛል፡፡ በባለሙያ ደረጃ በእኛ መጠን የመጣ አክሲዮን ግን የለም፡፡ መጀመሪያ ስንቋቋም 102 ሙያተኞች ኾነን ነው፡፡ አሁን ላይ ሦስት ሺህ ባለአክሲዮን ደርሰናል፤ ከዚህ ውስጥ 60% የሕክምና ባለሙያዎች ነን፡፡ የሕክምና ባለሙያ ሲባል በሁሉም ዘርፍ ማለት ነው፡፡
ግዮን፡- በውጪ ዓለም ያሉ ወደ 100 የሚኾኑ ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች የመቅረዝ ባለአክሲዮን ናቸው ተብሏል፡፡ ይህ ነገር ቢያብራሩልን?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- ከእኛ ጋር የተማሩም ውጪ የተማሩም ሐኪሞች በተለያዩ ዓለማት አሉን፡፡ እነዚህ ሐኪሞች መቅረዝ ሲቋቋም በጣም ደስተኛ ኾነው ተቀላቅለውናል፡፡ ኢንቨስት ሲያደርጉ ኢንቨስተመንቱ ጨንቋቸው ሳይኾን አብረው ለመሥራት ዜጋቸውን ማገዝ እንደሚገባቸው በማመን ነው፡፡ ስለዚህ የማገዝ ሂደቱን በተመለከተ እድሜ ለቴክኖሎጂ ነው የሚባለው፡፡ ለምሳሌ አንድ ራጅ ተነቦ በአንባቢው የእውቀት ደረጃ መረዳት የማይቻል ከኾነ ወይም የሁለተኛ ሰው አስተያየት የሚያስፈልግ ከኾነ አስተያየቱን ከውጭው ሐኪም ጋር በቴክኖሎጂ በመገናኘት መልስ ማግኘት ይቻላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ችግሮቻችንን መነጋገር መመካከር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ መጥተው የሚሠሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሠራ ነው፡፡ ይኼ ከመንግሥት ጋር መነጋገርንም ይጠይቃል፡፡ አሁንም ይህን መሰል አገልግሎት በፈቃደኝነት የሚሰጡልን ሐኪሞች አሉ፡፡ እኛ ግን እነዚህን ሰዎች እስከወዲያኛው በበጎፈቃደኝነት እየሠሩ እንዲቀጥሉ አንፈልግም፡፡ ስለዚህ የክፍያ ሁኔታዎችን እያመቻቸን በደንብ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ እንጥራለን ፡
ለምሳሌ ከሕንድ እዚህ መጥቶ ሕክምና ሰጥቶ የሚሄድ ቡድን አለ፡፡ እኛ ግን ይሄን ከመንግሥት ጋር ተነጋግረን እነዚህን ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው በፈቃደኝነት ከሠሩ እንደፈቀዳቸው መከፈል ካለበትም ለመክፈል እናመጣለን፡፡ በጥቅሉ ከፍ ሲል የተገለጹት ባለአክሲዮን ዶክተሮች ከእነርሱም በላይ በርካታ ሰዎችን ይዘው ይመጣሉ ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ከሀገር ውጪ ያለ ሰው ከሚያገኘው ገንዘብ ይልቅ ሀገሩን ማገልገል ይበልጥ ይፈልጋልና ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ቀና ልብ ያላቸው ባለ አክሲዮኖች ስላሉን እና ኔትወርኩን መዘርጋታችን ልዩ ያደርገናል፡፡
ግዮን፡- መቅርዝ በተለያየ አጋጣሚ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በቡድን እየሄደ አገልግሎት የመስጠት እቅድ አለው?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- አዎ፤ በተለየ አጋጣሚ አንዳንድ ቦታዎች ችግሮች የሚፈጠሩ ከኾነ የቡድን ልዑክ ሄዶ ያክማል፡፡ መቅረዝ ማኅበራዊ ኃላፊቱን የሚወጣው ሳንቲም በመሥጠት ወይም ነጻ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ብቻ ሳይኾን ባለሙያንም በመስጠት ጭምር ነው፡፡ መቅረዝ ላይ የሚያገለግል ባለሙያ ተቋሙ በሚያዘጋጀው ፍኖተ ካርታ መሠረት ይሠራል፡፡ የተለያዩ ቦታዎች በመሄድ ታማሚውን በማየት ባለበት ሕክምናውን እንዲያገኙ የማድረግ ሁኔታ ሊኾን ይችላል፡፡ መቅረዝ በደንብ ሲደራጅ ደግሞ በየቦታው እቃዎችን ይዞ ሄዶ የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ግዮን፡- መቅረዝ ከታካሚ አያያዝ እና መስተንግዶ አንፃር እስካሁን ካለው አሠራር ምን የተለየ ያዘጋጀው ነገር አለ?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- መቅረዝ ገንዘብ ለማግኘት ቢያስብ ኖሮ ቀደም ብሎ ባልተሟላ እቃ መጀመር ይችል ነበር፡፡ መቅረዝ የአገልግሎት ኃላፊነቱን መስጠት የቅድሚያ ተግባሩ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ተቋሙ ለትርፍ የተቋቋመ በመኾኑ ተጠንቅቆ ነው የሚሠራው፡፡ እኛ ጋር የመጣ ታካሚ በአገልግሎት አሰጣጣችን ዙሪያ ቅሬታ እንዲኖርበት አንፈልግም፡፡ ታካሚው በጸባይም በአገልግሎትም ረክቶ እንዲሄድ ነው የምንፈልገው፤ መቅረዝ የትኛውም አስተያየት ለመቀበልም ዝግጁ ነው፡፡ እሴታችንም ፈሪሀ እግዚአብሔር የተከተለ ሥራ መሥራት ነው፡፡ ምናልባት ግን በሥራ ሂደት ላይ የሚፈጠር ችግር ቅሬታዎች ቢኖሩ ሊፈታ የሚችል ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተናል፡፡ ተቋሙን ከኅብረተሰቡ ጋር አብረን እያሻሻልን ነው የምንሄደው፡፡ ስሕተቶች ከሁሉም በኩል ሊመነጩ ስለሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ታሞ የሚመጣ ሰው ብዙ ሊል ቢችል እንኳን በመንከባከብ ችግሩን ለመፍታት ይሞከራል፡፡
ግዮን፡- ሁሉም የሕክምና አገልግሎቶች በስፔሻሊስቶች ይሰጣል ብላችኋል፡፡ ይህን የምታደርጉት በየቀኑ ነው?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- አዎ፤ በየቀኑ ነው የምንሰጠው፡፡ ቅጥር ስፔሻሊስት ሐኪሞች አሉን፡፡ ፊት ለፊት የሚቀመጡት እነርሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለጽንስና የማህፀን ችግር ላለበት ሰው ስፔሻሊስት አለ፡፡ የቀዶ ሕክምና ኬዝ ካለም ቀጥታ ማግኘት ይችላል፡፡ ስፔሻሊስቶች ሁሉንም ቀን አሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ስፔሻሊስቶች በሚገቡበት ክሊኒክ በትርፍ ሰዓታቸው ይገኙልናል፡፡ እኛ 18 ተመላላሽ ሕክምና ክፍል አለን፡፡ በሁለትና ሦስት ፈረቃ በቀን ብዙ ሐኪም ይጠይቅልናል፡፡ ይኼ የአዋቂ ተመላላሽ ታካሚዎች ብቻ ነው፡፡ ብቻውን የሕፃናት እና የእናቶች አለ፡፡ ስለዚህ ሰዎች መጥተው በሚፈልጉት ስፔሻሊስት ታክመው መሄድ ይችላሉ፡፡ ሰብ ስፔሻሊስት ታክመው መሄድ ይችላሉ፡፡ ሰብ ስፔሻሊስቶቻችን በፕሮግራም የሚሠሩ ናቸው፡፡ ስቴሻሊስቶቻችን ግን በቋሚነት ሁሌም አሉ፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት ነገር ካለ እድሉን ልስጥዎ?
ፕ/ሮ ማኅተመ፡- መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር ለሕብረተሰቡ በጤናው ዘርፍ ብርሃን ለማብራት የተቋቋመ ነው፡፡ መሪ ቃላችን ፍቅርና ሙያ እንክብካቤ የተሞላበት የላቀ አገልግሎት የሚል ነው፡፡ ስለዚህ በዘያ ልክ ነው አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጀነው፡፡ ማንም ሰው አይመመው፤ ካመመው ግን ወደ መቅረዝ ጠቅላላ ሆስፒታል ይምጣ፡፡ እዚያ መጥታችሁ ታከሙ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ እኛ ጋር መጥታችሁ ያያችሁትን አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ነገር ንገሩን ማለት እፈልጋለሁ፡፡ መቅረዝ የጤና አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር ሌሎች አገልግሎቶችንም ይሰጣል፡፡ በቀጣይ ቴርሸሪ ሆስፒታል የሚከፍትበት ሁኔታ ይቀጥላል፡፡ በዚህ ዙሪያ በቅርቡ ማብራሪያ እንሰጣለን፡፡ በተለይ ጠቅላላ ጉባኤ መጋቢት 30/2015 ካካሄድን በኋላ የሚቀጥለውን የአክሲዮን ሽያጫችን በምን መልኩ እንደሚቀጥል እናሳውቃለን፡፡ ሌሎች ከአክሲዮን ጋር የተያያዘ መረጃ ካስፈለገ የመቅረዝን ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ዳይሬክተር ሕጎች አሉ፡፡ በ09-91-73-73-73 ላይ ደውሎ መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ በቀጣይ ከመንግሥት ጋር ተጋግዘን የሀገራችንን ብቻ ሳይኾን የአፍሪካንም ሕዝብ እናገለግላለን ብለን እናምናለን፡፡
ዐሥር እውነታዎች ስለ መቅረዝ
የተመሠረተበት ጊዜ – መስከረም 12/2013 ዓ.ም
የባለአክሲዮኖች ብዛት – 3000
የተከፈተበት ካፒታል – 250 ሚሊዮን
የተፈቀደ ካፒታል – 1 ቢሊዮን
መሪ ቃል – ‹‹ፍቅርና ሙያዊ አክብሮት የተሞላበት የላቀ እንክብካቤ››
አክሲዮን ሽያጭ የተጀመረበት – መስከረም 2013 ዓ.ም
ሥራ የጀመረበት – መጋቢት 12 ቀን 2015
ዋናው መሥሪያ ቤት መገኛ – ካሳንቺስ አዲስ አበባ
