የዓለም ጤና ድርጅት ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሞትና ለበሽታ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ለመቀነስ አገራት በትንባሆ፣ በአልኮል እና በጣፋጭ መጠጦች ላይ የጣሉትን ታክስ እንዲያሻሽሉ ማሳሰቢያ ስጠቱ ተነገረ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በጄኔቫ በተካሄደው የድርጅቱ 158ኛው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ስብሰባ መክፈቻ ላይ “3 በ 35” የተሰኘ አዲስ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ይፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ይህ ንቅናቄ በዋናነት የሚያተኩረው እስከ ፈረንጆቹ 2035 ዓመት ድረስ በትንባሆ፣ አልኮል እና ጣፋጭ መጠጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግ የሚጠይቅ ነዉ።
የዓለም ጤና ድርጅት ጥሪ እንደሚያመለክተው፣ አገራት በእነዚህ ምርቶች ላይ የሚጥሉትን የታክስ መጠን በመጨመር ትክክለኛ የገበያ ዋጋቸው ቢያንስ በ50 በመቶ እንዲያድግ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህም የሰዎችን የመግዛት አቅም በመቀነስ ለበሽታ የመጋለጥ እድላቸውን ዝቅ ያደርገዋል ተብሏል።
ዶክተር ቴዎድሮስ በንግግራቸው እንደገለጹት፣ የታክስ ጭማሪው ሁለት ዋና ዋና ጥቅሞች አሉት። በአንድ በኩል እንደ ስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም እና ካንሰር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ስርጭት ሲቀንስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለመንግስታት ተጨማሪ ገቢ ያስገኛል።
“አገራት ከውጭ በሚገኝ እርዳታ ላይ ጥገኛ ከመሆን ወጥተው የራሳቸውን የጤና በጀት በሀገር ውስጥ ሀብት እንዲሸፍኑ የጤና ታክስ ቁልፍ መሣሪያ ነው” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ፣ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ እንደ ማሌዥያ፣ ሞሪሸስ፣ ስሎቫኪያ፣ ስሪላንካ እና ቬትናም ያሉ አገራት በእነዚህ ጎጂ ምርቶች ላይ ታክስ ጨምረዋል። በዘንድሮው የ2026 መጀመሪያ ደግሞ ህንድ በትንባሆ ላይ አዲስ ቀረጥ የጣለች ሲሆን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ በጣፋጭ መጠጦች ላይ የደረጃ ታክስ ተግባራዊ ማድረጓ ተጠቅሷል።
በዚሁ ጋር በተያያዘ በዓለም ዙሪያ 4.6 ቢሊዮን ሰዎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንደማያገኙ እና 2.1 ቢሊዮን ሰዎች ደግሞ ለሕክምና በሚያወጡት ከፍተኛ ወጪ ሳቢያ ለድህነት እየተዳረጉ መሆኑን ዶክተር ቴዎድሮስ አስገንዝበዋል።
