ቡሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ጄይ ክላይተን አርብ ዕለት ኢራን በውጭ አገራት የሚኖሩ “አሜሪካውያንን ዒላማ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምራለች” በማለት አስጠንቀቁ።ቴህራን በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሌሎች አገራት የሚገኙ አሜሪካውያንን ለመግደል የምታደርገው ሴራ “ከፍ ያለ ደረጃ ላይ” መድረሱን ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።
ማስጠንቀቂያው ሚስጥራዊ ያልሆነ ሰነድን የያዘ ሲሆን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተላከ ነው።
ይህ ባለ አንድ ገጽ ሰነድ ኢራን አላት ስለተባለው ዕቅድ የሚገልጽ መረጃ፤ አደጋ ላይ ሊወድቁ ለሚችሉ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ይህንን ሚስጥራዊ መረጃ የማግኘት ዕድል ለሌላቸውን ጨምሮ፣ ለተለያዩ የአሜሪካ መንግሥት ሠራተኞች ተደራሽ መደረግ እንዳለበት ያስጠነቅቃል።
ማስጠንቀቂያው የተሰጠው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዲፕሎማቶችን እና የአሜሪካ ጦር በቀጣናው ያለውን የሰው ኃይል እየቀነሰ ባለበት ወቅት ነው። እነዚህ እርምጃዎች የተወሰዱት ከኢራን የሚመጡ ቀጥተኛ ስጋቶችን እንዲሁም በየመን ከሚገኘውና በኢራን ከሚደገፈው የሁቲ አማፂ እንቅስቃሴ የሚመጡ ስጋቶች በተጠናከሩበት ወቅት ነው።
“የአሜሪካ ዜጎችን ለመግደል ኢራን የነደፈቻቸው ሴራዎች በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሌሎች አንዳንድ አገራት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደርሰዋል” ሲሉ ክሌይተን ጽፈዋል።
የትራምፕ አስተዳደር በኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃቶችን እንደገና ለመጀመር እያሰበ ባለበት ወቅት የወጣው ይህ ሰነድ፣ የተወሰኑ ዒላማዎችን ወይም ሴራዎቹ እየተጠነሰሱባቸው ናቸው የተባሉባቸውን አገራት በግልጽ አይጠቅስም፤ እንዲሁም ጥቃቶቹ በቅርቡ ሊፈጸሙ እንደሚችሉ የሚያሳይ ፍንጭም አይሰጥም።
ክሌይተን እንደገለጹት፣ የአሜሪካ የደህንነት ማኅበረሰብ ከተለያዩ ምንጮች የተሰበሰቡ ሚስጥራዊ መረጃዎች ላይ የተጣለውን ገደብ ለማላላት እየሰራ ሲሆን፣ ይህም መረጃዎቹ ለውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በስፋት እንዲጋሩ ያስችላል።
የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍም የዚህ ማስታወሻ ቅጂ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው፣ በአካባቢው በሚገኙ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች ላይ በርካታ የደህንነት እርምጃዎች ከተወሰዱ በኋላ ነው።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ አስፈላጊ ያልሆኑ የኤምባሲ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዟል።
በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች በርካታ የአሜሪካ ኤምባሲዎች፣ በ”ተገደበ የአሠራር ሁኔታ” ስር ሆነው የሠራተኞቻቸውን ቁጥር ቀንሰዋል። ሲቢኤስ ኒውስ ቀደም ብሎ እንደዘገበው፣ ይህ አሠራር ሠራተኞቹ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ በይፋ ሳያዝዙ፣ የሠራተኞቹን ቁጥር ለመቀነስ ያስችላል።
