85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በግብርናው ዘርፍ የተሰማራ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሴቶከች እንደሆኑ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስርአተ ፃታ ባለሙያ አቶ ታዬ ሳሙኤል ለብስራት ሬድዮ እንደገለፁት በዘርፋ ይህን የሴቶችን አቅም በአግባቡ መጠቀም አልተቻለም።
በዚህም ምክንያት በኢኮኖሚ ረገድ እንደ ሀገር አሉታዊ ጫናን እያስከተለ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከዓለም ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ ማነስ በሀገሪቱ ሀገራዊ ጠቅላላ የምርት እድገት ላይ ተፅእኖ አሳድሯል።
በጥናቱ ውጤት መሰረት ኢትዮጵያ በአመት ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታጣ የተናገሩት አቶ ታዮ ለጉዳዮ መፍትሄ ለማምጣት በግብርና ዘርፍ የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማስፋፋት የወጣው የ10 ዓመት ስትራቴጂ እንዲከለስ ተደርጓል ብለዋል።
ስትራቴጂው እ.ኤ.አ በ2015 ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የህጎች፣ የአሰራሮች እና የፍላጎቶች ለውጥ በመኖሩ፣ አሁን ላይ ያሉ አዳዲስ ህጎችን፣ የፋይናንስ ድጋፎችን እና የሴቶችን ተሳትፎ በማካተት ስትራቴጂው መሻሻሉን አቶ ታዮ ጨምረው ለጣቢየችን ተናግረዋል።
በተለይም ደግሞ ከቤት ውስጥ ስራዎች እና ኃላፊነቶች ጋር ተያይዞ በግብርናው ስራ ላይ ሴቶች ሙሉ ሰዓታቸውን እንዳይጠቀሙ በማድረጉ ለእነሱ ተስማሚ የሆነ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችሉበት ሁኔታ በስትራቴጂው ተካቷል ነው የተባለው።
