“በቻይናዎች ዘንድ እምነትን ማግኘት በጣም ከባድ ነበር”

Date:

ጠበቃ መሠረት ሥዩም ( የማኩታ የሕግ አገልግሎት መሥራችና ማኔጂንግ ፓርትነር )

ግዮን መጽሔት :- በክፍል ሦስት ለጠበቃ መሠረት ያነሳናቸዉ ጥያቄዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል ። መልካም ንባብ

ግዮን፡- ከአፍሪካ ሀገራት ባሻገር ከቻይናዎችም ጋር የሥራ ግንኙነት አለሽ አይደል?


መሠረት፡- አዎ፡፡ ቻይና በልጅነቴ ከቤተሰቤ ጋር ሄጃለሁ፡፡ ስለንግዱ አጠቃላይ ሁኔታ ለመረዳት ብርሃን የፈነጠቀልኝም ከቤተሰቤ ጋር በልጅነቴ ሄጄ አንዳንድ ነገሮችን ማየቴ ነው፡፡ አንድ ወቅት እንደአጋጣሚ ከአንድ ቻይናዊ ባለሀብት ጋር ጉዞ ላይ ተገናኝተን ሥራ ሰጠኝ፡፡ እኔም በጥሩ ሁኔታ ሠርቼ አሳየሁ፡፡

በዚህ የተነሳ ግንኙነቴ እየሠፋ መጣ፡፡ በቻይናዎች ዘንድ እምነትን ማግኘት በጣም ከባድ ነበር፡፡ ኾኖም ግን አሳክቼዋለሁ፡፡ ከቻይናዎች ጋር ብቻም ሳይኾን ከቱርኮችም ጋር በርካታ ሥራዎችን ሠርቻለሁ፡፡ ቻይናዎች ግን ይለያሉ፡፡ ባሕላቸውንም እወደዋለሁ፡፡ ከቻይናዎች ጋር በርካታ የባሕል ምስስሎሽ አለን፡፡፡

ለምሳሌ በሠርግ ሰዓት ‹‹አናስገባም ሰርገኛ›› እነሱም ጋር አለ፡፡ ሴት ልጅ ከጋብቻ በፊት ክብሯን መጠበቋ ልክ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በእነሱም ዘንድ ትልቅ ክብር ያሠጣታል፡፡ በሕብረት መኖር፣ መደጋገፍ፣… የመሳሰለው ነገርም እንደኛው ነው፡፡ ቻይናዎች በጣም ፈጣኖችና ሥራ ወዳዶች ናቸው፡፡ ከእነርሱ ጋር መሥራት በጣም ያስደስታል፡፡ ከእነርሱ ጋር የምሠራው ቻይና ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይኾን በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥም ነው፡፡ በዱባይም ይሁን በሌሎች ሀገሮች በርካታ የቻይና ደንበኞች አሉኝ፡፡


ግዮን፡- ቻይንኛ ትናገሪያለሽ?


መሠረት፡- በጣም የተዋጣልኝ ባልኾንም እናገራለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ያሳደግኩት ቻይናዊ ልጅ አለኝ ፤ የቤተሰቦቹን ጉዳይ ከዚህ በላይ ይፋ ባላደርገውም ልጁ ግን ከልጆቼ የተለየ አይደለም፤ ብዙ ነገርም አስተምሮኛል፡፡


ግዮን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ትልልቅ የውጭ ተቋማት ጋር ያላችሁ የሥራ ግንኙነት ምንድን ነው?


መሠረት፡- ከብዙዎቹ ተቋማት ጋር የምንሠራው በማማከር ደረጃ ነው፡፡ የዚህ ጥቅሙ ግጭቶች ሲፈጠሩና ወደ ክስ ሲሄዱ ነገሮች እንዳይባባሱ በማማከር ብዙ አደጋዎችን ለማለዘብ ይጠቅማል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ትልልቅ ናቸው፡፡ አንዳንዴ የራሴን ክፍያ ትቼ የሀገሬን ጥቅም አስቀድሜ እሠራለሁ፡፡ በብዛት ከእኔ ጋር የሠሩ ተቋማት የከፋ ችግር አያጋጥማቸውም፡፡ ችግሮች ገጥመዋቸው ለመፍታት ብቻ ሳይኾን ችግሮች እንዳያጋጥማቸው ቅድመ ግንዛቤ ለመፍጠርና ሕጋዊ ኾነው እንዲሄዱ የማድረግ ሥራን በከፍተኛ ሁኔታ አከናውናለሁ፡፡


ግዮን፡- ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበራት አባል ናችሁ?


መሠረት፡- አዎ፣ በርካታ ተባባሪ አባል የኾንባቸው ሀገራት አሉ፡፡  

 
ግዮን፡- ወደ ሀገር ውስጥ እንመለስና፣ በመንግሥት በኩል ለእናንተ የአሠራር ሂደት እንቅፋት የኾኑ ቢሮክራሲያዊ ሂደቶች ወይም የፖሊስ አሠራሮች አሉ?


መሠረት፡- በዚህ ዙሪያ ጥሩ ነገር እንደሚያጋጥመን ሁሉ አስቸጋሪ ነገሮችም ያጋጥሙናል፡፡   

        
ግዮን፡- ከሕግ አኳያ መንግሥት ከውጭ ለሚመጡ ባለሀብቶች ምን ዓይነት አቀባበል ማድረግ አለበት ትያለሽ?


መሠረት፡- የሚመጣው ባለሀብት ሰላም ይፈልጋል ፤ ጥበቃ ይፈልጋል ፤ በሁሉም ነገር መተማመን ይፈልጋል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ባለሀብቱ ወደ ሀገሪቱ ከመግባቱ በፊት በሰበሰበው መረጃና ባጠናው ጥናት መሠረት የጠበቀውን ነገር ማግኘት ይኖርበታል፡፡

ካለበዚያ ገንዘቡን ኢንቨስት አድርጎ የጠበቀውን ነገር የማያገኝ ከኾነ ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ስለዚህ ባለሀብቱና የሚመለከታቸው ተቋማት መካከል ጥሩ መናበብ መኖር አለበት፡፡ ቃል የተገቡ ነገሮች ሁሉ በተቻለ መጠን መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም አጠቃላይ ኹነቱ የተሳለጠ መኾን ይጠበቅበታል፡፡

በዚያው  ልክ ከኢንቨስተሩ በኩልም ብዙ የሚጠበቁ ነገሮች አሉ፡፡ በሕግ ማዕቀፍ ሥር ኾኖ እያንዳንዱን ሕግና ደንብ አክብሮ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ተስማምቶ የገባበትን ማንኛውንም ሕግና ደንብ መፈጸምና መገዛት ይጠበቅበታል፡፡


መንግሥትም እንዲሁ ለኢንቨስተሩ ጥበቃ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከኢንቨስተሩ ጋር የሚገናኙ ማናቸውም ነገሮች የተቋማት ኃላፊዎችና ሁሉም አካላት ከኢንቨስተሩ ጋር ያላቸው ሂደት በአግባቡ የተሳለጠ መኾኑን መገምገምና ችግሮች ካሉም በአስቸኳይ መፍታት እና የሁልጊዜ ክትትል ማድረግ ይኖርበታል፡፡

አሁን ደግሞ ለኢቨስተሮች በመንግሥት በኩል ክፍት ስለኾነ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በብዛት ይገባሉ፡፡ በብዛት ሲገቡ እኛ ሀገር ተቋቁመው መገኘት የሚኖሩባቸው ተቋማት አሉ፡፡ እያንዳንዱ ተቋም ለዚህ ዝግጁ ኾኖ መገኘት ይኖርበታል፡፡


ከዚህ አንጻር ለምሳሌ ኢሚግሬሽን አንዱ ጥያቄዎች የሚነሱበት ተቋም ነው፡፡ አሁን ግን ይህ ተቋም ራሱን አሻሽሎና ዘምኖ እናገኘዋለን፡፡ እኔ ራሴ በቅርቡ ጠዋት ላይ ሄጄ አሥር ሰዓት ላይ ጉዳዬን ፈጽሜ ተመልሻለሁ፡፡ ይህ ማለት ቀደም ሲል ለወራትና ለቀናት ይቆይ የነበረ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት አሁን በአንድ ቀንና በሰዓታት ልዩነት ተገልጋይ መሸኘት መቻሉን ያሳያል፡፡

በተመሳሳይ እንደ ገቢዎች እና መሬት አስተዳደር አካባቢ ያሉ ተቋማትም ሲስተማቸውን እንደ ኢሜግሬሽን ሁሉ ማዘመን ይኖባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በዘርፉ ያሉ የሌላ ሀገር ተቋማት ያላቸውን የአገልገሎት አሰጣጥ ሂደትና ኢንቨስተሮቻቸው ያላቸውን ልምድ ያገናዘበ አገልግሎት ለመስጠት መጣር ያስፈልጋቸዋል፡፡


ግዮን፡- በሀገራችን በርካታ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ተሳትፎ ነበረሽ?


መሠረት፡- በርካታ ሕጎች ማሻሻያ ሲደርግባቸው ተሳትፊያለሁ፡፡ ለምሳሌ የሲቪል ማኅበረሰብ አዋጁ ሲሻሻል፣ የሥነ ሥርዓት  ደንቡ ሲሻሻል፣ የኢንቨስትመንት ሕጉም ሲሻሻል ተሳትፌያለሁ፡፡ የተወሰነ  ግብዓትም ነበረኝ፡፡ በአጠቃላይ በርከት ያሉ የሕግ ማሻሻያ ሂደቶች ላይ በመገኘቴ የዜግነት ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ፡፡


ግዮን፡- ቢሻሻል ብለሽ ያሰብሽው ሕግ ሳይሻሻል የቀረ አለ?


መሠረት፡- በማሻሻል ሂደቱ ላይ እያለን እኛ ያነሳናቸው ሀሳቦች ተካተዋል፡፡ አሁንም ግን ቢሻሻሉ  የምንላቸው ሕጎች በርካታ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የፍትሐብሔር ሕጉ በጣም ጥሩ ሕግ ነው፤ ነገር ግን ረጅም ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡

በተለይ አሁን ኢትዮጵያ ካጸደቀቻቸው አዳዲስ ዓለም ዓቀፍ ሕጎች ጋር ተያይዞ ብዙ ሕጎች መሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡ ሕጎቹ በ1949 የወጡ ኾነው ሳሉ በወጥነት ስናየው ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በጥሩ ሁኔታ እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ዘመንን ባገናዘበ መልኩ መሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡ ሌላው መሻሻል ያለበት ነገር ደግሞ በተለያየ ጊዜ ሕግ የሚወጣበት መንገድ በደንብ መጠናት አለበት፡፡ መረዳዳት ላይ መሠረት ያደረጉ ሕጎች ሲወጡ ባለሀብቱንም ኢንቨስተሩንም የሚያሳርፉ ይኾናሉ፡፡
——–
ማስታወሻ- ውድ አንባቢያን፣ ከጠበቃ መሠረት ሥዩም ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ ቀሪዉን በሚቀጥለው ቀናት ይዘን የምንመለስ ይኾናል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በጤና አገልግሎት ማስታወቂያዎች ላይ የሕመምተኞችን ምስክርነት መጠቀም ተከለከለ

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ...

ሴቶችን በቤት ውስጥ በማገዝ  መልካም ማህበረሰብ መፍጠር ተጀምሯል

በቤት ውስጥ የሚሠሩ ተግባራትን ተከፋፍሎ በመሥራት ሴቶችና እናቶችን መደገፍ...

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...