
ጌራወርቅ ጥላዬ
ሰውየው ወሎዬ ነው። ወሎዬ ነው ብዬ ገጣሚ ነው ማለት ግን ለሟች ሞቱን ማርዳት እንዳይሆንብኝ ትቸዋለሁ። (ለዚህም የቅኔው ባላባት ጎጃሜው ይመሥክር!) ይህን ማለቴን የሚያነብ ‹ልል› ወሎዬ ካለ ግን ‹‹ገጣሚ ወሎዬ ብቻ ነው›› ይልና በሁዳዴ ይገድፋል። በፋሲካ ይጦማል። ‹‹ቅኔም እኮ በባለቅኔ እንጂ በጎጃሜው ብቻ አትወሰንም›› የሚል ካለም ያስማማኛል። የሆነው ሆኖ ጽሑፌን መቀጠሉ ግን ያዋጣኛል. . .
ሁለት መዋጊያ አለ። ነገርና ጦር። ጉልበተኛ ጦር ያነሳል። ጠቢብ ግን ነገርን ይመርጣል። ኢትዮጵያዊም ሁለቱን ያውቃል። ለአሁኑ ግን ግጥም ይበቃል። ኢትዮጵያዊ በጦር ከመዋጋቱ በፊት በነገር ይወጋል። ለዚያም ነው ‹‹ዘራፍ›› ሲል ቅኔ የሚዘርፍ። ደሞ ‹‹ዘራፍ›› ብሎ ማሸነፍ የሚጀምረው ራሱን ስለሆነ እሱን የሚያሸንፈው የለም።
ይህ ሰው ግጥም ያውቃል። ሥሙ ወንድነት አለው። የወንድነቱ ግዝፈት ደግሞ በግጥም በማሥመሥከሩ ነው። ወንድነት ያለው ወንዱ ደግሞ ወንድዬ ዓሊ ነው። እኔም መጻፌን እቀጥላለሁ። የጻፋቸውንም እቀጽላለሁ። እስካሁን የጻፋቸው ግጥሞች ይጥማሉ። ይህንን ደግሞ እንኳንስ የበላ፥ የቀመሰ ያውቃል። የበላስ ይመሰክራል፤ የቀመሰስ እንዴት ይክዳል? አለመካድ ደሞ የማመን ማተብ ነው። ማተብ ደግሞ የባለአደራነት ምልክት ነው፤ ወንድዬም ቢሆን እንዲህ ብሏል ‹‹የገጣሚውስ ነገር? – እሱማ! የሥነ – ውበት፣ የሕይወት ባላደራ ነው። ባለማተብ ባለአደራ። የዚያች ጥበብ ከራማ ‹‹በል›› ያለውን ነፍስያው ላይ የተሸመነውን መጣፊያ ሳይደረትበት ያለ እንከን ያስተላለፈ፣ ያቀበለ ጊዜ ማተቡን ለዘላለማዊነት የሚያጸና – ባላደራ።››) ወንድዬ ዓሊስ እንዲህ አለ። ስለ ወንድዬ ዓሊስ ምን ተባለ? በግሌ፥ አልያም ለግሌ ‹‹የግጥም ሊቃውንት›› የምለው ሰው ብርሃኑ ገበየሁ እንዲህ ይላል፦
‹‹…ወንድዬ ዓሊን በአማርኛ የሥነ ግጥም ባህል ውስጥ ልዩ ያደርጉታል ብዬ ከማምንባቸው ገጽታዎች አንዱ ምስሎቹን የሚጠልቅባቸው ባሕሮች አያሌነት ነው። ከጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ ከሰሎሞን ዴሬሳና ከዮሐንስ አድማሱ በስተቀር በሌሎች ገጣሚዎቻችን እምብዛም የማይታየውን ዛሬን ከነገ፣ እንዲሁም ዱሮና ዘንድሮን የማተርጓጎም ጥበብ የወንድዬ ሥራዎች ድርና ማግ እየሆኑ የሚመጣባቸው ሥራዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ወንድዬ ለምናቡ ጥልቀት፣ ለግጥሙ ትርጓሜ ሁለንተናዊነት የሚያስገኘው ከቅዱሳን መጻሕፍት በሚዘርፋቸው ዘመንና ቦታ የሚሻገሩ ምስሎችና ሰብእናዎች፣ እንዲሁም ከአደገበት ቃላት የባሕል አውድማ ነው። የገጣሚውን ታላቅነት ለማድነቅ የሚያስገድደን አንድ እውነት የምንጮቹ ብዛት ሳይሆን፣ ከነባርና ዘመን አይሽሬ ውድማዎች የሚስባቸውን ሐሳቦችና ስሜቶች በተራቀቀ የትርጓሜ ስልት ለዘመኑ ሕይወትና እውነት ማሳያነት መገልገሉ፣ በሌላ አበባልም አዲስ ምት(myth)፣ አዲስ እውነት ለማርቀቅና ለማበጀት መቻሉ ይመስለኛል።. . . ›› እያለ ይቀጥላል፣ ‹‹ነፍሱን ይማረውና›› ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገበየሁ፦
‹‹የወንድዬ ሌላው የገጣሚነት ምናብ፣ እንደ ቅዱስ ያሬድ ማኅሌት ሥፍራና ጊዜን ከሚያጥፍ ኪናዊ ዘለአለማዊና ሁለንታዊነት ይወልዳል። በሌላ አበባል፣ ገጣሚው ስለ ግጥምና ኪነት ሲዘምር፣ በቅኔ ሠረገላ ሰማያትን እያሰሰ፣ ከሰማያት ጉዞ ልምዱ ምስልና ሕብር እያረቀቀ በመቅረጽ ነው።. . .
‹‹እንደ ሥነ ግጥም ታሪክ ፀሐፊነታችን ለመመስከር የምንገደደው አንድ ተጨማሪ ጉዳይ ቢኖር፣ ወንድዬ በገጣሚነት ዘመኑ በአገጣጠሙ ስልት፣ በጉዳይ መረጣ፣ በቋንቋና በአገላለጽ ትባት እንዲሁም በአንጓ አወቃቀርና በጽሑፋዊ ምልክቶች አጠቃቀም ረገድ በሁለተኛው መድበሉ ታላቅ ርምጃ ማሳየቱን ነው።›› (መድበለ ጉባኤ፤ ዘመናዊ የአማርኛ ሥነ ግጥም፤ አንዳንድ ነጥቦች።)
፠ ፠ ፠
ወንድዬን ሳውቀው ሆታ አይወድም። (ምናልባት አባት ሆኖ ስለማውቀው ይሆን? ግንስ የገጣሚ ነፍስ ከዜማ እንጂ ከጩኸት ምን አላት።) ጩኸት ስለማይወድ ዝም ይላል። እሱ ዝም ቢልም ግጥሙ ግን ዝም አያስብልም። ሰይጣን ይዞት ጠበል እንደካው ሰው አንባቢን ያስለፈልፋል።
ለሕይወት መውደድ ያለው ሰው፥ ከመሞቱ በፊት ግጥምን ያወቅ ዘንድ ግዴታው ነው። የግጥም ምዕመናን ሆይ ሞትን ላለመፍራት ከትንሣኤ በላይ ግጥምን እወቋት። ማወቅ ብቻም ሳይሆን በሷ ዘንድም ታወቁ። ለዚያም ነው መሰለኝ ግጥምን ያወቃት፥ ብቻ ሳይሆን ግጥም ያወቀችው ወንድዬ ታሞ ይቀልዳል፥ በሞትም ይሥቃል። ምክንያቱም ለሰው ግጥም ካለመውደድ በላይ የበኩር ሞት እንደሌለ ገጣሚው ያውቃል።
ብዙዎቹ ገጣሚ ‹‹ግጥም . . . ግጥም›› ይላሉ። ግጥም ግን ‹‹እውነት፣ እውነት እላቹኋለሁ አላውቃቸውምና እነማን ናቸው?›› ትላቸዋለች። ግጥምን አወቅናት ሲሉ በግጥም ዘንድ ላልታወቁት ገጣሚያን በኪናዊ ኀዘን በማንባት እንቀጥላለን። ግጥምን አውቀው በግጥም ዘንዳም ከታወቁና በልባም አንባቢያን ዘንድ ከተወደዱ ገጣሚያን መካከል ወንድዬ ዓሊ አንዱ ነው። ወንድዬን የማያውቅ የተገለጠ ገጣሚም ካለ ‹‹አይ አለማወቅሽ አገርሽ መራቁ›› መባሉን ብያለሁ።
ወንድዬ ዓሊን በአካል ከማወቄ በፊት የማውቀው በወፌ ቆመች ነው። ወፌ ቆመችን ደግሞ ግጥምን ሲያስተምር ግጥምን ከሚያስወድድ መምህር ከጋዜጠኝነት ትምህርቴ ኮብልዬ በዶ/ር ወንደሰን አዳነ ግጥምን በግጥም ስማር ነው። ይሄኔ ነው ዛዲያ ንስሐ የማልገባባቸው በአንድ ድርጊት ሁለት ኃጢአት የሠራሁ። (ኃጢአት ከተባለ)። እየተመላለስኩ ከማነብበት ቦታ አስነባቢዎች ለወሰድኳቸው መጽሐፍ ደንታ ስላልነበራቸው፣ የሰይፉ መታፈሪያ ፍሬውን ‹‹ውሰጠት››ን እና የወንድዬ ዓሊን ‹‹ወፌ ቆመች››ን ሰርቄ ወሰድኩ። ወደ ማንበቢያው ቦታም መመላለስ አቆምኩ፤ ምክንያቱም የምመላለሰው ለሁለቱ መጽሐፍ ነበርና፤ ዛዲያ መጽሐፍ የሰረቅኩት ሌባ ግን የሰረኳቸውን መጻሕፍት ሳይሆን በሰረቅኳቸው መጻሕፍት ውስጥ ባሉ ግጥም ግን እውኔ ተሰረቅኩኝ። (ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ዛሬ በአጸደ ሥጋ የሉምና ‹‹ነፍስ ሄር›› ወንድዬ ዓሊ ግን አለ፤ እና ‹‹በዕድሜ እስኪጃጅ ከጤና ጋር ያሰንብትልን››)።
ወንድዬን በሥራው አድንቄው፤ በአካል ሳውቀው አድናቆቴን መውደድ አክየበታለሁ። ማለትም ‹‹ምናለ በሩቅ እንዳደነቅኩት ቢቀረብኝ ኖሮ›› አላስባለኝም። ለዚህም ነው በ‹‹እናርጅና እናውጋ›› በምሥጋና ገጽ ላይ እንዲህም አልኩ፦
‹‹ቃሉና ግብሩ ያልተነጣጠለ
ወንድዬ እላለሁ ጥሩ ከተባለ።››
ወንድዬ በጽሑፍ በሩን ላንኳኳ ይከፍታል። ጥሩ የጻፈን ‹‹ግሩም – ሸጋ›› ብሎ ያጸናል። ጥሩ ያልጻፈን ደሞ ‹‹ይህማ አዛባ እንደመዛቅ ነው›› ብሎ ይሸኛል። (ወንድዬ ዝም ብሎ ግሩም ወሸጋ ነው! አይልም እንጂ ወንድዬ ‹‹ግሩም ነው›› ያለውን ጥሩ ነው ያለማለት መብት ግን በውዴታና በምክንያት የተከበረ ነው።)
ወንድዬ ሁለት ልጆች አሉት (ማኀተመ እና ማኅደረ)፤ ሁለት የግጥም መድበሎች አሉት(ወፌ ቆመች እና ሕይወትና ውበት)፣ ከአርትኦት ጋር ተዳምሮ የታተሙ ዐሥር የግለሰቦችና ሁለት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጻሕፍት አሉት። እሱም የቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን አማኝ ሰው ነው። የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን አማኝ እንደሆነ ያወቅኩኝ ለታ ገረመኝ። ምናልባት የተገረምኩት ስላልገመትኩና የእሱን መሳይ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሲሰብኩ እንጂ ሲገጥሙ ስለማላውቅ ይሆን? (መግጠም ሲባል የነጠረ ግጥም)።
፠ ፠ ፠
‹ወንድዬ ዓሊ ስለምን ግን? ፀሐይ የሚያስሞቅ፣ ባገሬው የሚያሳውቅ ሥራ እያለው፤ ለምን ገናነቱ ሥራውን ለመረመረው ብቻ ሆነ?› ብዬ ሳስብ መልስ ከሚሆኑኝ ምላሾች መካከል አንደኛ የክት ሰው መሆኑ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ባንድ እየዋሉ፣ ባንድ እየበሉ፣ ሥራዎቻቸው በሜካፕ አንድ ዐይነት እንደሆኑ ሴቶች የተመሳሰለ ሆኖ ሳለ፤ ከእኛ በላይ የግጥምን ዓላማ ሰቃይ፥ ሰንደቅ የለም፣ አይገኝም፤ እያሉ መጣፍ ሲገባቸው እንደሚጽፉቱ ግና ግጥሞቻቸውና ገጣሚነታቸው ሲታይ ግን ድንግልናዋን በውዴታ እንደቀባሪ ለወደደችው ከሸኘች በኋላ የወደዳትን በተክሊል እንዳገባች ደፋር ሴት ዓይነት ሆነው እንደሚገኙት ስጥ-አዊያን(አደባባያዊያን) ገጣሚ መሆን አለመሻቱምና መጸየፉ ይመስለኛል። ለዚህምስ አይደል፦
‹‹ አያ መድረክ ብርቴ!
ጋሽ ራስ አያውቄ!. . .
ይሄው ቀደዱልህ
ባምሮትህ ተኮፈስ – በቲቪ ጋዜጣው፣
ንገሥ ባ’የራቱ – በነፃው ባል-ነፃው…፤›› ሲል በሚቀጥለው ግጥሙ፥ የሚለው። ወንድዬ የመድረከኛ ሆኖ በሥም ከብዶ፤ በሥራ መቅለልን ባለመሻቱ፣ በጓዳው በዝቶ በአደባባይ (‹‹ለሰፊው ሕዝብ››) ጥቂት እንዲሆን አድርጎታል።
፠ ፠ ፠
በታሪክ ተጽፎ፤ በግጥም ተገጥሞ፤ በቴአትር ተተውኖ፤ በመነባንብ ተነብንቦ፤ በሙዚቃም ተሞዝቆ፤ የምናውቀው ጀግናው፣ ሀገር ወዳዱ፣ ቁጡው፤ ኩሩው፣ ቆፍጣናው፣ ጨካኙ፣ ባተሌው፣ አጤ ቴዎድሮስ እንዳባት፥ ባባት ቃል፥ የሚያባባ ሐሳብ ይዞ፥ በሚያላውስ ኀዘን እንባ ድምጸት፥ ወንድዬ በዕዝነ ሕሊናው ወደኋላ ሄዶ ‹‹ሥማ ዓለሜ›› በሚል ርዕስ፥ አጤ ቴዎድሮስ ‹‹ከዓለም ካሉት ጥሩ ሽታዎች ሁሉ የልጄን ጠረን እወዳለሁ›› ሲል፥ ከውጊያ መልስ፣ ከዘመቻ፥ ትጥቁን በቅጡ ሳይፈታ ልፊያ ከሚጀምረው ከሚወደው ከልጁ ጋር…፦ ድካም፣ መኳተኑን፣ መውደቅ መነሳቱን፣ መውደድ መናፈቁን፣ ማጣት ሰቀቀኑን፤ ቋያ በሆነ በሀገርና በልጅ ፍቅር ሲንገበገብ መኖሩን። ዳሩ ግን አንዱን ላንዱ መሥዋዕት ማድረግ ስለሚያሻ ለልጁ የሚሰጠውን ፍቅር ለሀገር በመሥጠቱ ለልጁ ለምን ፍቅር፣ ጊዜ፣ ትኩረት እንዳልሰጠው በፀፀት ንግግር የልጁን ፍቅሩ ተሻሚ ኢትዮጵያ እንደሆነች ለልጁ የሚነግርበት ወዲህም ላገር ሲል መክፋቱን፣ መከፋቱን፣ ጠባዩ መለወጡን፣ ሥምም መሰጠቱን አጤ ቴዎድሮስ ባዘን እንባ ትካዜ ልጁን (ልዑል ዓለማየሁን) በወንዱ! ወንድዬ ብዕር አማካይነት በእናት አንጀት ‹‹ሥማ ዓለሜ›› እያለ ለልጁ ነገሩን ያጨዋውታል፦
‹‹“አባባ!” ብለህ ስጠራኝ፣ ለቶሎው አለ-መባነኔ፣
ገና ካራ’ስ ቤት ሳትወጣ፣
ትቼህ በየፍልሚያው መባከኔ፣
ተረት ተጫውተህ ሳጠግብ፣
ገና አንደበትህ ሳይተባ፣
ጦር አወራወርን፣ ሰይፍ አሰናዘርን፣
ማውራቴ ነጋ ጠባ፤
ወድጄም አይደል – ዓለሜ
ጠንቶብኝ እንጂ – ሕመሜ።
ልጅነትህ እየራበኝ፣ የአባት ወጉን የነሣሁህ፣
በሣቅህ መጽናናት ስሻ፣ ምላሽ ፈገግታ የነፈግኹህ፣
ለሣቅ ፋታ – እንኳን ሳገኝ፣
ሣቄ ላፍታ – ያልቆየልኝ፤
. . . ኧረ ስንቱ . . . ዓለሜ!
ብርቱ ሆኖ ነው ሕመሜ።
የጧት ሕልሜን ፍች ለማየት፣
በሞት ጥላ ሥር ማለፌ፣
ከስንቱ የጦር ሜዳ…
አያል ጣረሞት ሥዕል ማትረፌ
ለእናት ዓለም ኢትዮጵያ መተኪያ የሌላት ለአንዲቱ፣
የጀግኖቼ ደም አጥንት . . .በየጥሻው መዘራቱ፣
ወኔዬን ባያንበረክክ፣ ቋንቋዬን ለውጦታል፣
ታጠቅ! . . . ብቻ ሆኖ ቀርቷል፤
መዩ! . . . ብቻ ሆኖ ቀርቷል፣
በቀረርቶ ዓይነት – ተገርቷል።
. . .እንጂ – ዓለሜ፣
እንዲህ ቢሆን እንጂ ሕመሜ፤
አላስችል ብሎኝ እንጂ ማለፍ፣
ሳልጠርግ የናት ዓለምን ጉድፍ፤. . .
መች አጣሁበት ነበር፣
እንደ ተርታ ሰው መኖር።
. . .ቢጠፋኝ ቤት ማዋቀሩ፣
ቤቴ ነው፤ ቋራ ገደል ከዱሩ፤
እርፍ መያዙ ቢሳነኝ፣
ጅግራ ማጥመዱ. . . አያቅተኝ፤
የ’ናቴም ሙያ . . .ያበላል፣
ኮሶ መቸርቸር . . . ምን ይገዳል?
ግና ዓለሜ! እናት ዓለም – የምላቱ፣
የደግ እናቴ – ቅርጢቱ፣
የፍቅርህ ጣውንት – እሷ ናት
እናት ዓለም፦ ኢትዮጵያ ናት።››
ይህንን ግጥም ባነበብኩ ቁጥር ሁሌ ልቤን ኀዘን ሲጫነኝ ጊዜ ከወደ ጎንደር የተገኘሁ ሰው ስለሆንኩ ይመስለኝ ነበር። አሁን ግን ሲገባኝ ግጥሙን ሳነብ ሁሌ እንደ ልዑል ዓለማየሁ ራሴን አድርጌ፣ ቦታውን ይዤ ስለማነበው ነው። ያባት መባከን፣ ያባት መብከንከን፣ የአባት እንባ እንደምን አያስነባ?!
፠ ፠ ፠
የአዘቦቱ ሰው አንዲት ዘማዊ ሴትን ልቧን ሳያይ በሩቁ በገላሽ ረከሽ ሲላት፤ ገጣሚ ግን ልባም ነው፥ የልቧን ንጻት እያየ ለገላዋ ጉድፍ ብዕሩን ቃል ያስነባል። ይህንንም ማዘን ወንድዬ በግጥሙ ሙሾ ያረግዳል፤ ጉስቁልናዋን፣ ውድቀቷን፣ የሴትነት ክብሯን ማጣት፣ መክሸፏን፣ የሁሉ ስሜት መሮጫ ሜዳ መሆኗን፣ የስሜት አምሮት መወጫ ሆና መገኘቷን፣ በመብከንከን ስሜት፣ በወቀሳ ግለት ‹‹እብድ የበላው በሶ›› ይላል። ይታሰበን እንግዲህ እንኳን እብድ በልቶት እንዲያውም በሶ እብድ ነው። የማይጨበጥ ተፍረክራኪ።
‹‹የልጅ ቤት፦
የክክ ስጥ – ሆንሽ፣
ሁሉም ዘገነሽ እቴ! . . . ሁሉ ዘገነሽ።
የቡና ቁርስ፦
አፍ መሟሻ፣
የልጅ አዋቂው – የ’ኩል ድርሻ፣
እንጃ – እቴ! – ያንቺን ነገር መዳረሻ።
የእንቅብ ላይ ቆሎ፦
የአለሌ – ማላመጃ፣
የሰፌድ ቆሎ፦
የወጠጤ ራት መፈንጫ። . . . ›› እያለ በሚቀጥለው። ያዛኝ ገጣሚ፣ አሳዛኝ ግጥም አንዲት የባንኮኒት ሴት እየታዘብ፥ ሲያዝንላት፤ የገጣሚ ነፍሱ በእኩል ኀዘን ሲያነባላት ይታያል።
፠ ፠ ፠
ምንም እንኳን ዝምድናዬ በግጥም በኩል ቢሆንም ከጻፋቸው ግለ ታሪኮች ባነበብኩት ባንዱ ግን ‹‹ምናለ የራሱን ግለ ታሪክ ቢጽፍና ባነበብኩት›› ብዬ እንድመኝ አድርጎኛል። ስለ ሥራዎቹ (ስለ ግጥሞቹ) በጽሑፍ አንድ ባንድ በብዙ ማለት የሚቻለኝ ብሆንም አንባቢያን ሥራዎቹን አይተው ትንሽ ይሉ ዘንድ መጠቆሙ ይሻላል በማለት። ብዙ ማለቱን ትቸዋለሁ።
በመጨረሻም እንዲህ ልበል፦ ወንድዬ ዓሊ የግጥምን ባሕል የሚከተል ገጣሚ ነው። ለዚህ ደግሞ ግጥሞቹ ምሥክርና ዋስ ናቸው። መግቢያዬ ላይ ‹‹ሰውየው›› ብዬ ወንድዬን ‹‹ወሎዬ ነው›› አልኩኝ እንጂ ወሎዬስ ሳይሆን ገጣሚ ነው። ምክንያቱም ገጣሚ የቦታ ድንበር፣ የጊዜ ወሰን የለውምና!