በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ላይ እንደ ድብርት እና ጭንቀት ያሉ የአእምሮ ጤና እክሎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መሆኑን የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሰላማዊት ዳሮታ ተናገረዋል።
ይህ እያደገ የመጣው አዝማሚያ በተለይ በአንደኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ በግልጽ እየታየ ሲሆን፣ ለችግሩ መባባስ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሱት የሱስ ተጋላጭነት እና የማህበራዊ ሚዲያ የሚያሳድሩት ስነ-ልቦናዊ ጫናዎች ናቸው።
ምንም እንኳን አሁን ላይ ስለ አእምሮ ጤና ያለው ግንዛቤ እና ወደ ባለሙያ የመሄድ ልምድ እየተሻሻለ ቢመጣም፣ የችግሩ ውስብስብነት ከባዮሎጂካዊ ሁኔታዎች እና ከዘመናዊው የኑሮ ዘይቤ ጋር ተዳምሮ እየጠነከረ መጥቷል።
የአእምሮ ጤና እክሎች መጨመር ከተለያዩ የሱስ አይነቶች ተደራሽነት እና መስፋፋት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ቀደም ሲል ከነበሩት እንደ ሲጋራ፣ ጫት እና አልኮል በተጨማሪ አሁን ላይ በወጣቶች ዘንድ በመርፌ የሚወሰዱ እጾች እና ካናቢስ በስፋት ጥቅም ላይ መዋላቸው አሳሳቢ ሆኗል።
እነዚህ ሱሶች እንደ ዶፓሚን እና ሴሮቶኒን ባሉ የአእምሮ ውስጥ ኬሚካሎች ላይ መዛባትን በመፍጠር ለከባድ ድብርት፣ ለጭንቀት፣ ለስኪዞፍሬንያ እና ለባይፖላር ህመሞች መነሻ ይሆናሉ።ከሱስ በተጨማሪ ዲጂታሉ ዓለም በወጣቶች የአእምሮ ጤና ላይ የራሱን አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ማህበራዊ ሚዲያዎች ብዙ ጊዜ ፍፁም እና የተዋቡ የሚመስሉ ህይወቶችን ብቻ የሚያሳዩ በመሆናቸው፣ ወጣቶች የራሳቸውን እውነተኛ ህይወት ከእነዚህ ምስሎች ጋር በማወዳደር ዝቅተኛነት እንዲሰማቸው ያደርጋል።
በተጨማሪም የትምህርት ጫና እና ከእነሱ ቀደም ያሉ ታላላቆች ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ መመልከታቸው ተስፋ መቁረጥን ሊፈጥርባቸው እንደሚችልና ይህም በከፋ ሁኔታ ራስን እስከማጥፋት ለሚደርስ አደጋ እንደሚያጋልጥ ዶክተር ሰላማዊት ያስረዳሉ።
የአእምሮ ጤና ችግሮች በታዳጊዎች ላይ በብዛት ቢታዩም፣ ከአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ጀምሮ እስከ ጡረተኞች ድረስ በማንኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝን ሰው ሊያጠቁ ይችላሉ።ባለሙያዋ አክለውም እንደ ራስን ማጥፋት ያሉ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ የዜና ዘገባዎች ጥንቃቄ የተሞላባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህም የሚደረገው ዘገባው ሳያውቁት ድርጊቱን የሚያበረታታ እንዳይሆን ለማድረግ ነው።በህብረተሰቡ ውስጥ የህመሙ ጫና እየጨመረ በመምጣቱ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የባለሙያዎችን ምክር መከተል እና ተገቢውን ህክምና ማግኘት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
ብስራት ሬዲዮ
