በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ዘርፍ እንቅፋቶች እና ምክረ ሐሳቦች

Date:

የናሙና ጥናቶች

በተመረጡ አራት የናሙና ጥናቶች የተሰበሰቡ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ፣ የዚህ ጥናት ዋነኛ ግኝቶች የምግብና የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች በሚከተሉት ነጥቦች ረገድ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ያመላክታሉ፡-

  • ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የስራ እድሎችን መፍጠር፡ በእያንዳንዱ የምግብ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከሚሰሩት አጠቃላይ ሰራተኞች ውስጥ፣ ከ61% እስከ 90% በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የምግብ ኢንዱስትሪዎችም (ከአራቱ መካከል ሶስቱ) ከአጠቃላይ ሰራተኞቻቸው መካከል ግማሽ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ሴቶች ከዚህ ባለፈም በአንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በአመራርና አስተዳደር የስራ መደቦች በማገልግል ላይ ይገኛሉ፡፡
  • የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እገዛ ማድረግ፡ ፊቤላ የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ከመንግስት በሚደረግለት ከፍተኛ ድጋፍ አማካይነት ከፍተኛ ድጎማ የተደረገላቸውን የምግብ ምርቶቹን በማቅረብ ዘይት ከገበያ እንዳይጠፋና የመንግስት የግዢ ስልቶችን በመጠቀም ምርቱ ለBoP ሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲዳረስ እያደረገ ይገኛል፡፡
  • የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመቆጣጠር የስነ ምግብ ይዘትን ማሻሻል፡ ፊቤላ የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ ከዚህ በተጨማሪ የዘይት ምርቶቹን የስነ ምግብ ይዘት ለማሻሻል ዘይቶቹን ቫይታሚን ኤ እና ቫይታሚን ዲን በመሳሰሉ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የማበልጸግ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

የምግብ ማቀነባበር ዘርፍ ምንም እንኳን በመንግስት ፖሊሲ ተቀዳሚ ትኩረት የተሰጠውና የግሉ ዘርፍ የተሳትፎ ፍላጎትም እያደገ የመጣበት የንግድ ዘርፍ ቢሆንም፣ የተለያዩ ማነቆዎች ግን የምግብና የመጠጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ዕድገትና ተወዳዳሪነት እግር ከወርች አስረው አላራምድ ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተመረጡ የምግብና መጠጥ የናሙና ጥናቶች የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ፣ በ የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ዘርፍ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ዋነኛ እንቅፋቶች በዝርዝር ተዳስሰዋል፡፡ በዚህም መሰረት (i) በላይኛው እርከን – የጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት፣ (ii) በመካከለኛው እርከን – ማቀነባበርና አስተሻሸግ፣ (iii) በታችኛው እርከን – ማርኬቲንግ እንዲሁም (iv) በድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶች – መሰረተ ልማትና ፋይናንስ ዋነኛ የዘርፉ እንቅፋቶች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በተመረጡት አራት የምግብና የመጠጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንደ አጠቃላይ የታዩት ሶስት ዋነኛ እንቅፋቶችም (2) የሚከተሉት ናቸው፡-

የላይኛው እርከን – የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እንቅፋቶች

አራቱንም የምግብና የመጠጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንደ አጠቃላይ በምናይበት ጊዜ፣ በሁሉም ዘንድ የሚያጋጥሙት ሶስት ዋነኛ እንቅፋቶች የጥሬ ዕቃዎች እጥረት፣ የጥሬ ዕቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መናር እና በአምራቾችና በአቀናባሪዎች መካከል ያለው የአቅርቦት ሰንሰለት ቅንጅት (ትስስር) ደካማ መሆን ናቸው፡፡ የጥሬ ዕቃዎች እጥረት በዚህ ጥናት ውስጥ ለተካተቱት አራቱም ኢንዱስትሪዎች ዋነኛውና አንገብጋቢው ችግር ሲሆን፣ ለችግሩ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ዋነኛ ጉዳዮችም የሚከተሉት ናቸው፡-

(i) የስጋ ማቀነባበር፡ አነስተኛ ምርታማነት፣ ህገወጥ የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ (በየአመቱ ለወጪ ገበያ ከሚቀርቡት የቁም እንስሳት 80% ያህሉ በህገወጥ መንገድ የሚላኩ ናቸው)፣ ገበሬዎች እንስሳትን ሽጠው ገንዘብ ለማግኘት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ እና የአገር ውስጥ የጥሬ ስጋ ፍላጎት እየጨመረ መምጣት፡፡

(ii) የምግብ ዘይት፡ የምግብ ዘይት (ፓልም ኦይል) ድፍድፍ ከውጭ አገራት ገዝቶ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ አለማግኘት፣ ዘይት ለማምረት በጥሬ ዕቃነት የሚውሉ የአገር ውስጥ የቅባት እህሎች ምርታማነት ዝቅተኛ መሆን እና ጥሬ የቅባት እህሎችን ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች የውጭ አገራት የመላክ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት፡፡

  • የግርጌ ማስታዎሻ – የዚህ አጭር ጽሁፍ ትንተና የሚያተኩረው እንደ አጠቃላይ በዘርፍ ጉዳዮች ወይም በጥቅል እንቅፋቶች ላይ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ (ማለትም ስጋ፣ ዘይት፣ የፍራፍሬ ጭማቂና የተቆላ ቡና) የሚታዩ እንቅፋቶች በዋነኛው ጥናት አጠቃላይ ሪፖርት ውስጥ በዝርዝር ተተንትነው ይገኛሉ፡፡

(iii) የፍራፍሬ ጭማቂዎች፡ ከምርታማነት መቀነስ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የስኳር እጥረት እና አንዳንድ የፍራፍሬ አይነቶች በተወሰነ ወቅት ብቻ በትኩሱ የሚገኙ መሆናቸው፡፡

(iv) የተቆላ ቡና፡ የምርታማነት መቀነስ፣ በዝናብ ላይ የተመሰረተ የምርት ስርዓት፣ ደረጃውን ያልጠበቀ የማድረቂያ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሳቢያ የሚከሰት የምርት ብክነት፡፡ የቡና አቀናባሪዎች ጥሬ ቡና በቀጥታ ከአነስተኛ አርሶ አደሮች መግዛት እንደሚችሉ ህጉ ቢፈቀድላቸውም፣ ወደ አርሶ አደሮች ለመድረስ የሚያስችል በቂ የመሰረተ ልማት አለመኖር፣ ህግን የማስፈጸም ክፍተት እንዲሁም ደላላዎች በተለይ ራቅ ባሉ ቡና አብቃይ አካባቢዎች የሚፈጥሩት ከፍተኛ ተጽዕኖና ጫና መሰል የቀጥታ ግብይት እንዳይከናወን እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ በፍራፍሬው ኢንዱስትሪ ምንም እንኳን በቀጥታ ከአምራቾች ግብይት ለመፈጸም የሚያስችል ምንም አይነት ብሔራዊ የህግ ማዕቀፍ ባይኖርም፣ ዘርፉ (ዘዴይ) ጥሬ ዕቃዎችን የሚያገኘው እያመረቱ ከሚሸጡ አርሶ አደሮች ጋር በሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ መሰል ግብይት በአቀናባሪዎችና በአርሶ አደሮች መካከል ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር የሚያበረታታ እንዲሁም እሴት የሚጨምሩም ሆነ የማይጨምሩ አላስፈላጊ ጣልቃገቦችን በማስወጣት የአቅርቦት ሰንሰለቱን የሚያሳጥር ነው፡፡

የመካከለኛው እርከን – የማቀነባበርና የአስተሻሸግ እንቅፋቶች

የዚህ ጥናት ዋነኛ ግኝት በጥናቱ የተካተቱ የምግብና የመጠጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ከማቀነባበሪያና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ እንቅፋቶች እንዳጋጠሟቸው ያመለክታል፡፡ እንደ አጠቃላይ በዘርፍ ደረጃ የሚታዩት ሶስት መሰረታዊ እንቅፋቶች ለእሴት ጭመራ ትኩረት ለሚሰጡ ኢንዱስትሪዎች ማበረታቻ አለማድረግ፣ በተለያዩ መንገዶች የምርት ብዝሃነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተሻሉ ቴክኖሎጂዎች አለመኖር እንዲሁም ከውጭ አገራት በሚገቡ የማቀናበሪያና የማሸጊያ ቴክኖሎጂዎች ከፍተኛ ጥገኝነት መኖር ናቸው፡፡ የመንግስት ድጋፎችና ማበረታቻዎች ከአገራዊ እሴት ጭመራዎች ይልቅ በአብዛኛው ትኩረት የሚሰጡት ለእርሻ ምርትና ጥሬ የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

የታችኛው እርከን – የማርኬቲንግ እንቅፋቶች

ለምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እንደ አጠቃላይ በዘርፍ ደረጃ የሚያጋጥሟቸው ዋነኛዎቹ ሶስት አንገብጋቢ እንቅፋቶች ከፍተኛ የገበያ ውድድር፣ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ እና የምግብ ደህንነት መስፈርቶች ናቸው፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ ለተካተቱ የዘይትና የፍራፍሬ ኢንዱስትሪዎች ዋነኛው ፈተናና ችግር ሆኖ የተጠቀሰው ደግሞ፣ ከውጭ አገራት ከሚገቡ የምግብ ምርቶች የሚገጥማቸው ውድድር ነው፡፡ ከውጭ አገራት የሚገቡ የፍራፍሬ ጭማቂዎችና የዘይት ምርቶች በአንጻራዊነት በዋጋ አነስተኛና በገበያው ዘንድ ተመራጭ ሊሆኑ የቻሉትም የቀረጥ ዕድሎች ተጠቃሚ ሲሆኑ የአገር ውስጥ ምርቶች በአንጻሩ ከፍተኛ ግብር የሚጣልባቸው በመሆኑ ነው፡፡ በወጪ ንግድ ተወዳዳሪ ለመሆን እንቅፋት የፈጠሩ ተብለው የተጠቀሱት ጉዳዮች ደግሞ በስጋ ኢንዲስትሪው የንጽህናና ሌሎች የምግብ ደህንነት መስፈርቶችን ማሟላት አለመቻል፣ በኢትዮጵያ የተቆላ ቡና ዘርፍ የንግድ ምልክትና ብራንድ አለመኖር ናቸው፡፡

የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶች እንቅፋቶች – መሰረተ ልማትና ፋይናንስ

የመሰረተ ልማት እንቅፋቶች

የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎች ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ያሉባቸው ዋነኛ እንቅፋቶች የሃይል አቅርቦት እጥረት፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የገጠር መንገዶች እና በምግብ ማቀነባበር የእሴት ሰንሰለት የመጀመሪያው ደረጃ የላይኛው እርከን (በማሳ ደረጃ) የእሴት ጭመራን የሚያግዙ መሰረተ ልማቶች አለመኖር ናቸው፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ ለተካተቱ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎች አንገብጋቢው የመሰረተ ልማት ችግር በየጊዜው የሚከሰት ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ነው፡፡ ይህ የጥናት ግኝት የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ባወጣው የግዙፍና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች (LMSMIS) የ2016/17 ሪፖርት ከተጠቀሰው ግኝት ጋር የሚጣጣም ሲሆን፤ ሪፖርቱ አብዛኞቹ ተቋማት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ከኢትዮጵያ የ የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ዘርፍ ዋነኛ እንቅፋቶች አንዱ እንደሆነ መግለጻቸውን ያሳያል (የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ፣ 2018)፡፡

በመስኩ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ከሚያጋጥሟቸው ሌሎች  እንቅፋቶች መካከልም ደካማ የአቅርቦት ሰንሰለት ሎጅስቲክስ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የገጠር መንገድ መስመሮች እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ እሴት ለመጨመር የሚያስችሉ ዘመናዊ አውታሮች ቢያንስ በገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ደረጃ አለመኖር ይጠቀሳሉ (ለምሳሌ፡- የከብት ማድለቢያ፣ የቡና ማጠቢያና ማድረቂያ እንዲሁም የማሸጊያ ቴክኖሎጂ)፡፡ የመሰል ዘመናዊ አውታሮች አለመኖር በምግብ ማቀነባበር የእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ ሌሎች በርካታ ተዋንያን እንዲገቡበት በር የከፈተ ሲሆን፣ አብዛኞቹም ምንም አይነት ተገቢ እሴት የማይጨምሩ ናቸው፡፡ ይህም የአቅርቦት ሰንሰለቱን የበለጠ አራዝሞታል፤ በአርሶ አደሮችና በአቀናባሪዎች ግንኙነት ላይም እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በምግብ ኢንዱስትሪዎች የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መፍጠሩንም በጥናቱ የተሳተፉ መረጃ ሰጪዎች አክለው ገልጸዋል፡፡

የፋይናንስ አቅርቦት እንቅፋቶች

የፋይናንስ አቅርቦት የግሉ ዘርፍ (በአብዛኛው አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት) በግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ዘርፍ ውስጥ እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን ከሚፈጥሩ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በምግብና መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ በተሰሩት የናሙና ጥናቶች የተገኙ ውጤቶች፣ የፋይናንስ አቅርቦት ከግዙፍ ተቋማት ጋር ሲነጻጸር የበለጠ እንቅፋት የሚፈጥረው ለመካከለኛ ተቋማት እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ በተለይ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ አቅርቦት እጅግ ውስብስብና ፈታኝ ነው፡፡ የፋይናንስ አቅርቦቱ አነስተኛ፣ አስቸጋሪ ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች የሰፈኑበትና ረጅም ጊዜን የሚወስድ፣ ተገቢ ያልሆነ የእፎይታ ጊዜ የሚሰጥበት እንዲሁም አስቸጋሪ የክፍያ ሁኔታዎች ያሉበት ነው፡፡

ድምዳሜ እና ምክረ ሃሳቦች

ድምዳሜ

ይህ ሪፖርት በተመረጡ አራት የምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ላይ የተሰሩ የናሙና ጥናቶችን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ዘርፍ ዋና ዋና እንቅፋቶች በአጭሩ ይዳስሳል፡፡ የጥናቶቹ ዋና ዋና ግኝቶች የምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ለሴቶችና ወጣቶች ከፍተኛ የስራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም የአገሪቱን የምግብና የስነ-ምግብ ዋስትና በመደገፍ ረገድ ትልቅ አቅም እንዳላቸው ያመላክታሉ፡፡ ዘርፉ ምንም እንኳን መሰል አቅም ያለውና በብሔራዊ ፖሊሲዎች ውስጥ ከፍ ያለ ትኩረት የተሰጠው እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ወደ ምግብ ማቀነባበር ንግድ የመግባት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም፣ በርካታ እንቅፋቶችና ተግዳሮቶች የዘርፉን ዕድገትና ተወዳዳሪነት እያቀጨጩት ይገኛሉ፡፡

እንቅፋትና ተግዳሮቶቹ በምግብና መጠጥ ማቀነባበር የእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ በየደረጃው የሚታዩ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት (i) በላይኛው እርከን – የጥሬ ዕቃዎች እጥረትና የአቅርቦት ሰንሰለት ትብብር ደካማ መሆን፣ (ii) በመካከለኛው እርከን – ለአገር ውስጥ እሴት ጭመራዎች ድጋፍ አለመደረግ፣ የማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችንና የምግብ ንጥረ ነገሮችን ከውጭ አገራት ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ማጋጠምና ከፍተኛ የገቢ ቀረጥ እንዲሁም የምግብ ምርቶች ብዝሃነት ውስን መሆን፣ (iii) በታችኛው እርከን – የምግብ ደህንነትና የጥራት ደረጃዎች ብሔራዊ ፖሊሲ ካለመኖሩ፣ የምግብ ንጽህናና ሌሎች መስፈርቶችን ካለማሟላትና በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ የተቆላ ቡና ምርቶች የንግድ ምልክት ካለመኖር ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥና በአለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የገበያ ውድድር መኖር እንዲሁም (iv) በድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶች የመሰረተ ልማት አውታሮች መጓደል (ለምሳሌ፡- የገጠር መንገዶች፣ የኃይል እጥረት፣ በማሳ ደረጃ የሚደረግ የመጀመሪያ ደረጃ እሴት ጭመራ) እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት በተለይ ለመካከለኛ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ውስን መሆን በእንቅፋትነት ተጠቅሰዋል፡፡

እነዚህን እንቅፋቶችና ተግዳሮቶች ማስወገድ የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ዘርፍ የንግድ ዕድገትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታል፡፡ ሚና ይጫወታል፡፡ ከዚህ ጥናት የተገኙ ቁልፍ ግብዓቶች ፓን አፍሪካን ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ኤንድ ኢንደስትሪ እና የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ቀጣዩ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ምክክር በጥናቱ ዋና ዋና ግኝቶች ዙሪያ እንዲወያይና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ እንዲስማማ በር የሚከፍት የከፍተኛ ደረጃ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀትና ለማስተባበር እንደ መነሻ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡

ምክረ ሃሳቦች

ይህ ጥናት የደረሰባቸውን ዋና ዋና ግኝቶች እንዲሁም የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ዘርፉን የቆዩ ድርሳናት ክለሳና አገራዊ ልምዶችን መሰረት በማድረግ፣ የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ዘርፍ የንግድ ዕድገትና ተወዳዳሪነት ለማጠናከር የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች ያቀርባል፡፡ በግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ የእሴት ሰንሰለት ዋነኛ ደረጃዎች ላይ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራትም የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡-

በማሳ ደረጃ፡ ጥራቱን የጠበቀ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን የወደኋላ/ የላይኛው እርከን ግንኙነትን ማጠናከር

  • የግብርና ማስፋፊያ ፕሮግራሞችን ለማስፋፋት እና አቀነባባሪዎች በግብርና ምርት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የመሬት ባለቤትነትን የሚያሻሽል የፖሊሲ ድጋፍ ማድረግ፤
  • በአርሶ አደሮች/ የህብረት ስራ ማህበራት እና በአቀነባባሪዎች መካከል ጠንካራ ግንኙነት የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤
  • እሴት ያልተጨመረባቸው ምርቶችን የወጪ ንግድ ባለመበረታታት በአገር ውስጥ የእሴት ጭመራ በግብዓትነት የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎችን አቅርቦት የሚያሳድጉ የፖሊሲና የህግ እርምጃዎችን መውሰድ፤ (i) ድንበር ተሻጋሪ ህገወጥ የቁም እንስሳት ንግድን ለማስቆም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ፣ (ii) የቅባት እህሎች፣ የቁም እንስሳት (ከብቶች፣ በጎች፣ ፍየሎች)፣ ፍራፍሬዎች ወዘተ የመሳሰሉ ያልተቀነባበሩ የግብርና ምርቶችን የወጪ ንግድ እንዳይስፋፋ ማድረግ፡፡

በመካከለኛው እርከን – የማቀነባበር ደረጃ፡ የማቀነባበር ወጪዎችን መቀነስ፡- ዘመናዊ ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችን አቅርቦት እንዲሁም ለአገር ውስጥ የእሴት ጭመራዎች የሚደረጉ ሁሉን አቀፍ ድጋፎችን ማሻሻል

  • ወጪ ቆጣቢ፣ (ii) ከአካባቢ ጋር የሚስማማ፣ (iii) የድህረ ምርት ብክነትን የሚቀንስ፣ (iv) በስፋት ለማምረት የሚመች እንዲሁም (v)  የተለያዩ የግብርና ምርቶችን (እንስሳት፣ ሰብሎች/ፍራፍሬዎች) ለማቀነባበር ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ደረጃቸውን የጠበቀ ዘመናዊ የማቀነባበሪያና የማሸጊያ ቴክኖሎጂ አቅርቦት እንዲያድግ ድጋፍ ማድረግ፤
  • የግብርና ድጋፎችን/ ድጎማዎችን በማሳ ደረጃ (ማለትም ለአርሶ አደሮች) ከመስጠት ባለፈ በአገር ውስጥ እሴት ጭመራ ላይ ለሚሰሩ አቀነባባሪዎችም አስፋፍቶ ማዳረስ፤ የምርት ብዝሃነትንና የንግድ ምልክት አሰጣጥን በሚያሳድጉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ልማት ላይ ያተኮሩ መንግስት መር የምርምር ጥረቶችን ማበረታታት፤
  • የታክስ ስርዓቱን ተቋማት በንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችን እንዲያመርቱና እንዲያስተዋውቁ በተሻለ ሁኔታ የሚያግዝ እንዲሆን ማድረግ፤ ማለትም (i) ምግቦችን ለማበልጸግ የሚስፈልጉ የንጥረ ነገሮችንና የማሸጊያ ቁሳቁስ የገቢ ንግድ ቀረጥን መቀነስ፣ (ii) ተጨማሪ እሴት ታክስ የተጣለባቸውን የምግብ ምርቶች ተጨማሪ እሴት ታክስ ከሚመለከታቸው ዕቃዎች ዘርዝር ውስጥ ማውጣት፣ (iii) የጉምሩክ አሰራሮችን ማሻሻልና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን ማሳደግ፤
  • የምርት ብዝሃነትንና ማበልጸግን እንዲሁም ተገቢ የሆነ የማሸጊያ ቁሳቁስ አቅርቦትን ለመደገፍ፣ በቂና በዋጋው ተመጣጣኝ የምግብ ግብዓቶች አቅርቦት እንዲኖር የፖሊሲ ድጋፍ ማድረግ፤
  • ደረጃቸውን የጠበቁ የተቀነባበሩ ምርቶች ማሸጊያዎችን ወደፊት በአገር ውስጥ ማምረት የሚቻልበትን መንገድ መቀየስ፡፡

በታችኛው እርከን – በማርኬቲንግ ደረጃ፡ የምግብ ምርቶችን ፍላጎትና የገበያ ተወዳዳሪነት ማሳደግ

  • እርካሽ ዋጋ ያላቸው የምግብ ምርቶች ከውጭ አገራት እንዳይገቡ ክልከላ በማድረግ ለአገር ውስጥ ምርቶች ጥበቃ ማድረግ፤ በአገር ውስጥ የተቀነባበሩ የምግብ ምርቶችን በመንግስት የግዢ ስርዓቶች ውስጥ ማካተት፤
  • የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፡ (i) የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥና መደበኛ አለማቀፍ የጥራት መመዘኛዎችን የሚያሟሉ የጥራት መስፈርቶችን ለማውጣት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የህግ ማዕቀፍ ማበጀት፤ (ii) አለማቀፍ ገበያ የብቃት መስፈርቶችን (ለምሳሌ ለስጋ የወጪ ንግድ የንጽህናና ሌሎች መስፈርቶች/SPS) የሚያሟሉ አቀነባባሪዎችን መደገፍ እንዲሁም (iii) አለማቀፍ የንግድ ማዕከል (ITC) እና አለማቀፍ የምግብ ደህንነት ኢኒሺየቲቭን በመሳሰሉ ለጋሾች ድጋፍ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን ማበረታታት፤
  • የተቆላ ቡና የንግድ ምልክትና የመለያ ምልክት ልማትን መደገፍ (የኮሎምቢያና የህንድ ተሞክሮ)፤
  • በአገር ውስጥ የተቀነባበሩ ምግቦችን ፍጆታ ማሳደግ፤ የተቀነባበሩ ምርቶችን የገበያ ክልልና ብዝሃነት ለማስፋፋት ከክልላዊ የእሴት ሰንሰለቶች ጋር ማስተሳሰርን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ፡፡

በግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ኢንዱስትሪው ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶች

  • የገጠር መሰረተ ልማት ስራዎችን ማሻሻል፡ (i) የገጠር መንገድ ትስስሮች እና (ii) በማሳ ደረጃ የመጀመሪያ ደረጃ እሴት ጭመራ የሚከናወኑባቸው መሰረተ ልማቶችና ተቋማት (ማድለብ፣ እንስሳት ማርባት፣ የቡና አጠባና ማድረቅ፣ ደረጃ አሰጣጥ፣ ማሸግና ማጠራቀም፣ ዘመናዊ ትራንስፖርት/ሎጅስቲክስ ወዘተ)፤

የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ኢንዱስትሪው በቀላሉ የገንዘብ ብድር አቅርቦት ማግኘት የሚችልባቸውን ፈጠራ የታከለባቸው የፋይናንስ አቅርቦት መንገዶችን መቀየስ፡፡ የህንድ (3) የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ የምርት ነክ ማበረታቻ ስርዓት ተሞክሮ (ስምንት የማበረታቻ ስርዓቶች – የድጎማ ብድር፣ የቁም እንስሳት የመድህን ዋስትና ወዘተ) እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ (4) የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ድጋፍ ስርዓት (ወጪ መጋራት፣ የገንዘብ ድጋፎች፣ የመድህን ዋስትና ወዘተ)፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!! በክርስቲያኖች ዘንድ ጥምቀት...