የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር በከተሞች ባለው የቤት ግንባታ ላይ የመንግስት ድርሻ 20 በመቶ እንደሚሆን ገልጿል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የቤቶች ፓሊሲ መጽደቁን ለአሐዱ የገለጹት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ናቸው።
ሁሉንም ሰው የቤት ባለቤት ማድረግ አይቻልም ያሉት ወ/ሮ ጫልቱ የቤቶች ፓሊሲውን ተከትለው በሚወጡ መመሪያዎች መንግስት 20 በመቶውን ለአቅመ ደካሞች እና ለሀገር ባለውለታዎች ቤት እንዲሰራ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።
የተቀረውን 80 በመቶ መንግስት ምቹ ምህዳርን እየፈጠረ የግል ባለሀብቱ እንዲሳተፍ በማድረግ አቅም ያለው የቤት ባለቤት እንዲሆን አልያም በገቢው ልክ የኪራይ አማራጭን እንዲያገኝ ማድረግ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የቤት ፓሊሲ እንደሀገር አለመኖሩን አስታውሰው በመንግስት በከተሞች ይሰራ የነበረው የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚንየም ) መንግስት በስፋት የተሳተፈበት መሆኑና የፕሮጀክት አፈጻጸሙ መዘግየትን ጨምሮ ትክክል ያልሆኑ አሰራሮች እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤት አቅም የሌላቸው ዜጎችን ለይቶ ለመጥቀም የታሰበ ቢሆንም ከምዝገባ ስርዓቱ አንስቶ በነበረው ልክ ያልሆነ አሰራር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት “ላለው የሚጨምር እንጂ ቤት የሌላቸው ዜጎችን ለይቶ ችግራቸውን የሚፈታ እንዳልነበር ሲሉ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
(አሐዱ ራድዮ)
